Saturday, 02 January 2021 11:07

“ፓርቲያችን ቢሰረዝም ከትግሉ ፈፅሞ አንወጣም” የኢዴፓ ፕሬዚዳንት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ከተመሰረተ የ27 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረውና ብዙ ተግዳሮቶችን ያሳለፈው አንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ (ኢዴፓ)፤ ከሰሞኑ በምርጫ ቦርድ መስፈርቱን አላሟላም ተብሎ ተሰርዟል ህልውናውንም አጥቷል፡፡ ኢዴፓ የአገሪቱ ጎምቱ ፖለቲከኞች (እነ ዶ/ር ሃይሉ አርአያ፣ ኢ/ር አድማሱ ገበየሁ፣ ልደቱ አያሌው፣ ሙሼ ሰሙ፣ አብዱራህማን አህመዲን፣ አንዷለም አራጌው ወዘተ…) በመስራችነትና በአመራርነት ፓርቲ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኞም እንደ አዲስ መዋቅሩ የሚነገርለትና በቀድሞው የተቃዋሚ ፖለቲካ የሚመራው ምርጫ ቦርድ የህጋዊነት መስፈርት አላሟላም በሚል ሰርዞታል፡፡ እንዴት ሊሆን ቻለ? የፓርቲውን ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሠን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡

                  የቦርዱ ኢዴፓን የመሰረዝ ውሳኔው ተገቢ አይደለም እያላችሁ ነው፡፡ ለምን?
ላለፉት አራት ዓመታት ፓርቲያችን የሕልውና አደጋዎች በተደጋጋሚ እየተጋረጠበትና እየታገለ ነው እዚህ የደረሰው፡፡  የበፊቱ ኢአዴግ ፓርቲውን ለማፈራረስ ሙከራ አደረገ፡፡  የብሄራዊ ም/ቤት አባላት በርካታ ስለነበርን የማፍረስ ሂደቱን አከሸፍን፡፡ ከዚያ በኋላም በወቅቱ ምርጫ ቦርድ ፓርቲያችንን ለአራቱ ግለሰቦች ሰጥቶ ነበር፡፡ ያንንም እየተሟገትን አሸነፍን።
ኢዜማ ሲመሰረት ደግሞ ተብሎ ፓርቲያችንን ለማፈራረስ ተሞከረ፡፡ ነገር ግን ባደረግናቸው በርካታ ጥረቶች ያንንም ታግለን አሸነፍን፡፡ እንደዚያም ሆኖ ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ለኛ ለመስጠት ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ ግን ተደጋጋሚ ጥረቶች አድርገን፣ የፓርቲውን ህልውና ለማስመለስ ሞከርን፡፡ ይህም ሆኖ ግን ኢዜማ ከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ  ወስዶብናል፡፡  ቢሮአችንን ተነጥቀናል፡፡ ይሄ በቦርዱ እየታየ ባለበት ሁኔታ ውስጥ “ከአብሮነት” (ኢዴፓ፣ ኢሃን፣ህብር-ኢትዮጵያ የመሰረቱት) ጋር የነበረንን ግንኙነት ፈጠርን፡፡ አብሮነትን ለማጠናከር ጥረት በምናደርግበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንደገና አብሮነትን ለማዳከም፣ በኢ/ር ይልቃል የሚመራውን ኢሃንን መሰረዝ  እንደ አማራጭ ተወሰደ፡፡ ኢሃን ተሰርዞም ቢሆን መታገሉን አላቆምንም ነበር፡፡ በኋላም የአብሮነት ከፍተኛ አመራር የሆኑትን አቶ ልደቱንና  ኢ/ር ይልቃልን በማሰር፣ አብሮነት ዳግም እንዳይነሳ ለማድረግ ጥረት ተደረገ፡፡ ይህን ድርጊት በአደባባይ ለህዝብ እያሳወቅን ባለበትና ህዝቡም የተፈጸመብንን በደል እየተገነዘበ በመጣበት ወቅት ደግሞ የመጨረሻው የማጥፋት እርምጃ ተወሰደብን፡፡ ፓርቲው በቦርዱ ተሰረዘብን፡፡
ማን ነው እናንተን ለማዳከም የሚሰራው? ለምን አላማ? ክሳቸው በበቂ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ነው?
በምርጫ ቦርድ፣ በመንግስትና በግንቦት 7 የተቀነባበረ ሴራ ነው የተፈጸመብን፡፡ እኛ ህገ-ወጥ የሚያደርገንን  አንዳችም የህግ ስህተት አልሰራንም፡፡ ለምሳሌ ለምርጫ ቦርድ ህጋዊ የሚያደርገንን መስፈርት ሁሉ አቅርበንለት ነበር፡፡ ግን እኛን ምንም ሳያማክር ነው መሰረዛችንን በመገናኛ ብዙሃን የሰማነው፡፡  ሲደርስብን ከነበረው ተከታታይ የማዳከም ሴራ አንጻር እኛን ለማጥፋት ምን ያህል ሴረኞች እንደበረቱብን የሚገነዘበው ይገነዘበዋል፡፡
ፓርቲው የተሰረዘው 10ሺ የመስራቾች ፊርማ ማሟላት ባለመቻላችሁ ነው ተብሏል፡፡ አሟልተናል ነው የምትሉት?
እኛ እንደውም 17 ሺህ ፊርማ ነው ከ6 ክልሎች ያሰባሰብነው፡፡ ከዚያ ውስጥ ወደ 2 ሺህ የሚሆኑት እኛ ራሳችን ያልተሟሉ መረጃዎች ናቸው ብለን ትተናቸው፣ ከ15 ሺህ በላይ ፊርማ ነው ያቀረብነው፡፡ ይህን ካስገባን በኋላ “ይሄ ጎደለ” ተብለን ሳንጠየቅ ነው ተሰርዛችኋል የተባልነው፡፡ ይህ ውሳኔ 27 ዓመት ትግል ሲያደርግ የነበረን ፓርቲ የማፍረስ ሂደቱን የማጠናቀቅ ውሳኔ አድርገን ነው የወሰድነው፡፡
ያቀረባችሁት 15 ሺህ ፊርማ ምን ያህል የተጣራና አስተማማኝ ነበር?
እኛ በሚገባ አጣርተን ነው ያቀረብነው፡፡ እያንዳንዱ የፈረመ አባላችን ሙሉ አድራሻ የተቀመጠበት ነው፡፡ በተጨባጭ ይህን እኛም አጣርተናል፡፡ የተጠራጠርናቸውን ሁለት ሺህ ያህሉን ትተናቸው እኮ ነው፤ እርግጠኛ ናቸው ያልናቸውን 15ሺ ያቀረብነው፡፡
በምርጫ ቦርድ ይህን አሟሉ እንኳ ተብለን አልተጠየቅንም፡፡ ይሄ ለኛ ግልፅ እርምጃ ነው፡፡ ፓርቲውን የማጥፋት ውሳኔ ነው፡፡
እርግጠኛ ነዎት… እንድታሟሉ የተጠየቃችሁት ነገር አልነበረም? ምክንያቱም ምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ ፓርቲዎች የጎደላቸውን እንዲያሟሉ ዕድል ስለመስጠቱ ተናገሯል…
አንዴ ደብረብርሃን ላይ የሁለት ይሁን የሶስት ዓባላት የተሳሳተ የቀበሌ አድራሻ አቅርባችኋል ተብለን… ለሱ ምላሽ ከመስጠት ውጭ ሌላ ምንም የተጠየቅነው ነገር የለም። እኛ እንደውም ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ለቦርዱም አሳውቀን  ስንዘጋጅ ነበር፡፡
መቼ ነበር ጠቅላላ ጉባኤ ልታደርጉ ያቀዳችሁት?
ከጥር 30 በፊት ለማድረግ ነበር ስንዘጋጅ የቆየነው፡፡ ኮሚቴ አዋቅረን ሰፊ እንቅስቃሴ ላይ ነበርን፡፡
ቀጣዩ እርምጃችሁ ምንድነው?
አብዛኞቻችን ኢዴፓ ውስጥ ያለን አመራሮችና አባላት የሰላማዊ ትግል አራማጆች ነን፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገነባ የምናደርገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡  ፓርቲያችን ስለተሰረዘ ማናችንም ከፖለቲካ ትግል አንወጣም፡፡ እንደውም አሁን ያለው ስርዓት ምን ያህል አምባገነን ስርዓት እንደሆነ የተረዳንበት ነው፡፡ እኛ ፓርቲያችን ተሰረዘ ብለን ጉዳያችንን ወደ ፍርድ ቤትም ሆነ ወደ ሌላ አካል ይግባኝ አንልም፡፡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት ስለሌለን ወደዚህ ሂደት አንገባም፡፡ ነገር ግን በቀጣይ ምን መደረግ አለበት የሚለውን እየተመካከርን ነው፡፡ ነገር ግን ፈጽሞ ትግላችንን አናቆምም፡፡
“ኢሃን”  እና “ኢዴፓ” ተሰርዘዋል። የእነዚህ ፓርቲዎች  ጥምረት የሆነው “የአብሮነት” እጣ ፈንታስ?
ይህን ተነጋግረን የምንወስነው ይሆናል፤ ነገር ግን ከትግሉ ሜዳ ፈጽሞ አንወጣም፤ በዚህ እርግጠኞች ነን፡፡


Read 1655 times