Monday, 21 December 2020 00:00

“ካለፈው ያለመማርና በዘር የተቃኘ አስተሳሰብ መጨረሻ”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 (“የቲማቲም ማሳው፣ የማራዶናና የማንዴላ ወጎች”)

            የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ከሰሞኑ የአገራችን ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሚታየውን ጉዳይ አስመልክቶ፣ የተለያዩ ነጠብጣቦችን ማገናኘት (Connecting the dots) የሚለውን ስልት በመከተል፤”ካለፈው ያለመማር”፣ “በዘር የተቃኘ አስተሳሰብ” እና “የውጭ ኃይሎች የሴራ ፖለቲካ” መጨረሻቸው ዕልቂት መሆኑን ማሳየት ነው፡፡
ጉዳዩን በአፄ ኃይለሥላሴ ጀምሬ፣ ስለ ደርግና ወያኔ አንስቼ በእግረ መንገድ ጽሁፉን እያዋዛሁ ለማቅረብ ከቲማቲም ማሳ ጀምሮ፣ ማራዶና፣ ማንዴላ፣ አብርሃም ሊንከለንና አፄ ምንሊክን በተገቢ ቦታዎች ላይ አነሳሳለሁ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጥቅል ሀሳብ፡-
“ማንኛውንም ተግባር ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ እና በማንኛውም ወቅት በትክክል አከናውን” የሚል ነው፡፡
ወደ ዝርዝር ጉዳያችን ለመግባት ትንሽ ወደ ኋላ ሸርተት ብለን የሚከተሉትን ሁነቶች በአጭር በአጭሩ እንቃኝ፡-
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (ጃንሆይ)፡-
1923 ዓ.ም. - 1966 ዓ.ም.  
አፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ እየከዳቸው መሆኑ ቢነገራቸውም እውነታውን ሊረዱት አልፈቀዱም፡፡ በ1953 ዓ.ም በኮሎኔል መንግሥቱ ነዋይና በወንድማቸው አቶ ገርማሜ ነዋይ አስተባባሪነት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደረገባቸው፡፡ ይህ “የታህሣሥ ግርግር” እየተባለ የሚጠራው መንግሥት የመገልበጥ ሙከራ በአጭሩ ቢከሽፍም፣ የንጉሡን የቅርብ ባለሥልጣኖችና የሴራው ዋና ጠንሳሾች የተባሉትን ወንድማማቾች ሕይወት ቀጥፏል፡፡
የ1953 ዓ.ም “የታህሣሥ ግርግር” እንዳበቃ ክቡር አቶ ሀዲስ አለማየሁ (የ"ፍቅር እስከ መቃብር" መፅሐፍ ደራሲ)፣ በንጉሡ በኩል የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች የሚዘረዝር ጽሁፍ ያለ ምንም ፍራቻ አቅርበው ነበር፡፡ ንጉሡ ግን ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ ሀዲስ አለማየሁ አስተዋይ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ ጥሩ ዲፕሎማትና የተዋጣላቸው ደራሲ ብቻ ሳይሆኑ ምርጥ አማካሪ መሆናቸውን ለትውልድ አስተምረዋል፡፡ በአስቸጋሪ ወቅትም ቢሆን የሚያምኑበትን ሃሳብ ለንጉሡ አቅርበዋል፡፡ ንጉሡን ሊያስደስታቸው የሚገባውን ሳይሆን፣ ለአገር ይበጃሉ ያሉአቸውን ጠንከር ጠንከር ያሉ የማሻሻያ ሃሳቦችን አቅርበው ነበር፡፡ የሚሰማውንና የሚያምንበትን በግልፅና በድፍረት፣ ሆኖም ግን በታላቅ ትህትና የሚያቀርብ፣ በርግጥም የመርህ ሰው ይባላል። ጥሩ አማካሪ የሚባለው የዚህ አይነት ሰብዕና ያለው ሰው ነው፡፡ ሀዲስ አለማየሁ የመርህ ሰው ነበሩ፡፡
ጃንሆይ ከመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ በኋላ ሁኔታዎችን ለማሻሻል የሚያስችል ከበቂ በላይ ጊዜ (13 ዓመታት) ቢኖራቸውም ጊዜውን ሳይጠቀሙበት ቀሩ፡፡ መጨረሻቸውም በአሳዛኝና በአሰቃቂ ሁኔታ ተደመደመ፡፡
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም፡-
ከ1966 ዓ.ም - 1983 ዓ.ም
መንግሥት እንደ ቀድሞ መግዛት ሲያቅተው፣ ሕዝብ ደግሞ ለመገዛት ፈቃደኛ ባልሆነ ጊዜ ሥር-ነቀል ለውጥ (አብዮት) ይከሰታል፡፡ በ1966 ዓ.ም በአገራችን የተፈጠረው ይኸው ነው፡፡ መንግሥት አቃተው፡፡ ሕዝቡ በቃኝ አለ፡፡ በመካከሉ የተደራጀ ኃይል ባለመኖሩ መንግሥታዊ ሥልጣን “ሜዳ” ላይ ወደቀ፡፡ የተሻለ አደረጃጀት የነበረው የወታደሩ ክፍል ሥልጣኑን በእጁ አስገባ፡፡ ደርግ በዚህ መንገድ ሥልጣኑን በመያዙ የመጀመሪያው አካባቢ “የጁንታ መንግሥት” እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ ቀለል ባለ አቀራረብ ያን ጊዜ የተፈፀመው ሁኔታ ይህን ይመስል ነበር፡፡
መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሥልጣን ላይ የወጡበትን ዝርዝር ጉዳይ ወደ ጎን ትተን፣ 60 ዎቹን ሰዎች እና ጃንሆይን ያስገደሉበት መንገድ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የደርግም ሆነ የሳቸው እጣ ፈንታ የከፋ እንደሚሆን የሚያሳይ ነበር፡፡ የ60 ዎቹን ሰዎች ግድያ አስመልክቶ በተደረገ ስብሰባ ላይ፣ የደርግ አባል የነበሩት ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ ሁኔታዎቹ በህጉ መሠረት እንዲታዩ ያቀረቡት ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይህንን ዓይነት አስተያየት ያቀረቡት ኮሎኔል ብርሃኑ የመርህ ሰው መሆናቸውን ተግባራቸው ያሳያል፡፡
ይህንን የ60 ዎቹን ግድያ ጉዳይ በተመለከተ “በሸገር 102.1 ራዲዮ ጣቢያ” በእሸቴ አሰፋ ተዘጋጅቶ የቀረበውን የራዲዮ ፕሮግራም መከታተል ይቻላል፡፡ ይህ ለ70 ደቂቃ የሚዘልቅ ታላቅ የአገር ታሪክ የተቀነባበረበት የራዲዮ ፕሮግራም የአቅራቢውን ልዩ ችሎታና ባለሙያነት ከማሳየቱም በላይ ታላቅ የታሪክ ሰነድ ሆኖ የሚቀመጥ ሥራ ነው፡፡
ደርግ በጥሩ ጎኑ የሚነሳለት ነጥብ ቢኖር በጦርነት የተጎዱ ወገኖችን የሚያስተናግድበት መንገድ ነበር፡፡ ለዚህ ሥራው “የሕፃናት አምባ” በመባል የሚታወቀውና በጦርነት ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትና ወጣቶችን ለማሳደግ የተቋቋመው፣ እንዲሁም “የጀግኖች አምባ” በመባል የሚታወቀውና በጦርነቱ ወቅት የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ወታደሮች ለመንከባከብ የተቋቋመው ጥሩ ምሳሌዎች ነበሩ። ወታደሮቹ የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉትና አካለ ጎዶሎ የሆኑት ለአገርና ለሰንደቅ-ዓላማ ክብር በመሆኑ የተቋማቱ አገልግሎት ተገቢና የሚያስመሰግን ነበር፡፡
ደርግ እንደ ቡድን፤ መንግሥቱ ኃ/ማርያም እንደ መሪነታቸው፣ ከጃንሆይ አወዳደቅ ምንም ሳይማሩ ቀሩ፡፡የመጨረሻው ሰዓት በመጣ ጊዜ፣ የደርግ ባለሥልጣናት እጃቸውን ለመስጠት ሲጋፉ ተመለከትን፡፡ መሪው መንግሥቱም “አንድ ሰው - አንድ ጥይት” እስኪቀር እዋጋለሁ የሚለውን መፈክራቸውን እንደያዙ ከአገር ኮበለሉ፡፡
ወያኔ፡- ከ1983 ዓ.ም. - 2010 ዓ.ም.
ባለተራዎቹ ወያኔዎች ለራሳቸው “ተራራውን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የሚል ስም ሰጥተው ብቅ አሉ፡፡ ገና ከመጀመሪያው ለአገሪቱ ሰንደቅ-ዓላማ ክብር እንደሌላቸው ለማሳየት፣ “ጨርቅ” በማለት ገለጡት፡፡ ጦርነትን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ጦርነትን መፍጠር እንደሚችሉና ጥርሳቸውንም እንደነቀሉበት ማውራት የዘወትር ተግባራቸው ሆነ፡፡
የአገሪቱን ሠራዊት “የደርግ ወታደር” በማለት ከአጣጣሉት በኋላ፣ ይባስ ብለው የእግረኛ ጦሩን፣ አየር ኃይሉንና የባህር ኃይሉን ሙሉ ለሙሉ በተኑት፡፡ መሪው አቶ መለስ ዜናዊ የሚመሩትን ህዝብና አገር በተመለክተ፣ ድብቅ ዓላማ ያላቸው መሆናቸውን ኤርትራ እንድትገነጠልና አገሪቱ ወደብ አልባ እንድትሆን በፈቀዱበት መንገድ በግልፅ አረጋገጡ፡፡ በዚህ ወቅት የአቶ መለስን ድርጊት በመቃወም፣ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ ነገሩ ሥርዓት ባለው መንገድ መፈጸም እንደሚገባው አሳስበው ነበር፡፡ እዚህ ላይ ፕሮፌሰሩ የመርህ ሰው መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡
መለስ የሕገ-መንግሥቱ ሰነድ የተደበቀ ዓላማቸው ማጠንጠኛ መሆኑን በድፍረት ይናገሩ ገቡ፡፡ በአገር ውስጥ ከሚመሩት ሕዝብ ማግኘት ከሚገባቸው ክብር ይልቅ፣ የውጪ መንግሥታት የሚሰጧቸው አድናቆት ይናፍቃቸው ጀመር፡፡ የቡድን ስምንት፣ የቡድን ሃያ፣ የኔፓድ፣ የከባቢ ዓየር ብክለት ወዘተ የአፍሪቃ ተወካይ ይሆኑ ዘንድ በምዕራባውያኑ ተቀቡ፡፡ ነጮቹ፣ ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ አሁን ገና “ጥሩ እንግሊዝኛ የሚናገር የበሰለ መሪና ተወካይ” አገኙ ይሉ ጀመር፡፡
ወያኔ የፖለቲካ ሥልጣኑን፤ የኢኮኖሚ አውታሮችንና የማህበራዊ ዘርፍ አገልግሎቶችን በተቀነባበረ መንገድ የተወሰነ ቡድንን ጥቅም እንዲያስከብሩ አድርጎ አዋቀራቸው። በማህበራዊው ዘርፍ የትምህርት ሥርዓቱን ለማዳከም የተሰራው ተንኮል፣ ወጣቱ ትውልድ ላይ የተፈፀመ እጅጉን የከፋ ደባ ነበር፡፡ የውጭ ግንኙነቱ የምዕራባውያንን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ በተለይ የእንግሊዝንና የአሜሪካንን ጥቅም በሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ጭምር ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ በመለስ ዜናዊ አጋፋሪነት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ መለስ የከፋ በደል ከመፈፀማቸው በፊት ፈጣሪ ቀደማቸው። አሟሟታቸው ግልፅ ባልሆነ መንገድ አለፉ፡፡ ከእሳቸው ህልፈት በኋላ “ተራራውን ያንቀጠቀጠው ትውልድ” በተራው መንቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ የሴራ-መሀንዲሱን በማጣቱ ተፍረከረከ፡፡
በ2010 ዓ.ም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና ወያኔ ተፋጠጡ፡፡ ወያኔ ተረታ፡፡ ከኢህአዴግ ወያኔን ቀንሶ አጋር ድርጅቶችን ጨምሮ “ብልፅግና” የሚባል የኢህአዴግ ወራሽ ፓርቲ ተመሰረተ፡፡ ይህም ፓርቲ ጥገናዊ ለውጥ (Reform) እስከሚቀጥለው ምርጫ የምከተለው አካሄድ ነው አለ፡፡ ከደርግም ከወያኔም የተለየሁ ነኝ ማለቱ ነው፡፡ አብዮት ሳይሆን ጥገናዊ ለውጥ ነው ለአገራችን የሚያስፈልጋት የሚል አቋም ያዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ወያኔ ለሌላ ሴራ ወደ መቀሌ ሄዶ መሸገ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ቡድኑ የጁንታ ጠባይ ማለትም የመንግሥትን ሥልጣን በሃይል የመንጠቅ ሙከራ በግልጽ ማሳየት ጀመረ፡፡ ውስጥ ለውስጥም ዝግጅቱን ተያያዘው፡፡
የብልጽግና እና የወያኔ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ ቀጥሎ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ላይ በወያኔ ቡድን ተፈፀመ፡፡ በጦርነቱ መካከል በማይካድራ ከተማ ሌላ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደገመ፡፡ የተፈፀመው ግፍ እንኳን ሊተገበር፣ ሊታሰብ የማይገባው በመሆኑ ሕዝቡ፣ መከላከያ ሠራዊቱና መንግሥት በጋራ በመሆን ወያኔ ላይ የመጨረሻ የጠነከረ በትራቸውን አሳረፉበት፡፡
የሰንደቅ-ዓላማ ክብር የሌለው፣ ከህዝቡ ጋር እልህ የተጋባው የወያኔ ቡድን፤ እንደ ደርግ ባለሥልጣናት ዓይነት ዕድል የሚኖረው አይመስልም፡፡ የፈፀመው ወንጀል ወደ ዓለም አቀፍ ወንጀለኝነት ከፍ በማለቱ ፍርዱም ቅጣቱም ከፍ ይላል፡፡
ወያኔ ከደርግም፤ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ያልተማረ፤ በሰብዕናውም ሆነ በአስተሳሰቡ በጣም የወረደ ቡድን ስብስብ ሲሆን፤ ዋና ዓላማው አገርን ለምዕራባውያን እጅ መንሻ በማቅረብ፣ ሥልጣንና ሃብትን በሞኖፖል መቆጣጠር ነበር፡፡
ወደ ምዕራባውያን ጉዳይ ለመሸጋገር ይረዳን ዘንድ “በቲማቲም ማሳ” በኩል እንለፍ፡-
“የቲማቲም ማሳው ነገር”
ቀደም ባለው ጊዜ ምዕራባውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ለመቀራመት ባወጡት እቅድ መሰረት፤ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይና ቤልጂየም ድርሻ ድርሻቸውን ተካፍለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለጣሊያን ብትመደብም፣ ክብር አድዋ ላይ ለወደቁትና ለአጼ ምንሊክ ይሁንና፣ቅርምቱ በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ፡፡ ቀሪዎቹ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ አገዛዝ ለመውጣት ኢትዮጵያን እንደ ተምሳሌት በመቁጠራቸው፣ የቅርምቱ መሪ እንግሊዝ አገራችን ላይ ከፍተኛ ቂም ያዘች፡፡
የቀጥታ ቅኝ አገዛዝ ዘመን ሲያበቃ፣ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለማካሄድ የሚቻልበት ዘዴ በእንግሊዝ ፊት አውራሪነት ተነደፈ፡፡ ይህ በዘርና በቋንቋ ዙርያ የተጠመደ ጊዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ ቦምብ፣ ዛሬ በብዙ የአፍሪካ አገራት ለሚታየው ከዘር ጋር የተያያዘው ችግር ዋና ምክንያት ነው፡፡ እኛ አገርም በሰነድ ተደግፎ በወያኔ በኩል እንዲገባ የተደረገው “የዘር ፖለቲካ”፣ የዚሁ የእንግሊዝ መሰሪነት ደባ ውጤት ነው፡፡ እንግሊዝን በጭንቅላታችን ይዘን ወደ ቲማቲም ማሳችን እንዝለቅ፡፡
አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች እ.ኤ.አ በ1960 ዎቹ ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ዓላማ በውስጡ የያዘ የልማት ትብብር፤ የእርዳታ ድጋፍ፣ የእውቀት ሽግግር ወዘተ በሚል ሽፋን ብዙ የውጭ ድርጅቶች አፍሪካ ውስጥ እንደ አሸን ፈልተው ነበር፡፡ አሁንም አሉ፡፡
አንድ የምዕራባውያን ድርጅት በአንዲት የአፍሪካ አገር ለሚኖሩ ገበሬዎች፣ እንዴት የቲማቲም ተክልን በተሻለ ሁኔታ ማምረት እንደሚችሉ ሥልጠናና ትምህርት ሰጠ፡፡ “አፍሪካ በጣም ለም መሬት አላት’’፤ “ስላላወቃችሁ ነው እንጂ ይህ መሬት ደግሞ ብዙ የቲማቲም ተክል ለማፍራት የተመቸ ነው”፤ "በሉ እነዚህን ዘሮች እንዝራና እንዴት ፍሬያማ እንደሚሆኑ እናሳያችኋለን" እያሉ፡፡
የቲማቲም ተክሎች አፍርተው ብስል ቀያይ በሆኑ ጊዜ፣ በአቅራቢያው ከሚገኘው ወንዝ ውስጥ የሚገኙ ጉማሬዎች ወጡና የቲማቲም ማሳውን እንዳይሆን አድርገውት ሄዱ፡፡
ፈረንጆቹ፡- (በድንጋጤ) እንዴ ጉማሬዎቹ…?
መንደርተኞቹ፡- (ፈገግ ብለው) በዚህ ምክንያት ነው እኮ እኛ በዚህ አካባቢ ምንም ዓይነት
 የእርሻ ሥራ የማንሰራው፡፡፡
ፈረንጆቹ፡- ታዲያ ለምን በቅድሚያ አልነገራችሁንም?
መንደርተኞቹ፤- መቼ ጠየቃችሁንና!!
የምዕራባውያን አገሮች፤ የልማት ዕርዳታ ድርጅቶችም ሆኑ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዋና ችግር “እኛ እናውቅላችኋለን” የሚለው ፈሊጣቸው ነው፡፡ ጠይቆ መረዳት አይሆንላቸውም፡፡ በዚሁ ወደ ማራዶና ወግ እንዝለቅ፡፡
“ማራዶና እንግሊዝን አሸነፈ”
እንግሊዝና አርጀንቲና ፎክላንድ የምትባለው ደሴት ትገባኛለች በሚል መነሻ ጦርነት ገጥመው ነበር፡፡ እንግሊዝ አሸነፈች፡፡ የእንግሊዝ ሚዲያዎች የጻፉትና የተናገሩት ዕብሪት የተሞላበት ነገር፡ “እውነት ፈጣሪ የለህማ” የሚያሰኝ ነበር፡፡  
ከጦርነቱ ማግስት እ.ኤ.አ በ1986 ዓ.ም ሜክሲኮ ላይ በተደረገው የዓለም ዋንጫ፣ እንግሊዝና አርጀንቲና አንድ ምድብ ተደለደሉ። አርጀንቲናዎች በማራዶና አማካኝነት ግብ አስቆጠሩ፡፡ እንግሊዞች በእጁ ነው ያገባው በማለት ተከራከሩ፡፡ ዳኛውና መስመር ዳኛው ግቡን አጸደቁት፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ማራዶና በድጋሚ አስደናቂ ግብ አስቆጠረ። ይህቺ ግብ በተለያዩ ዓለም ዋንጫዎች ላይ ከተቆጠሩ አስደናቂ ግቦች አንዷ ተብላ የተመዘገበች ስትሆን፤ ማራዶና አራት-አምስት የሚሆኑ ተከላካዮችን በማለፍ ያስቆጠራት ግብ ነች፡፡
በአጠቃላይ ውጤት አርጀንቲና እንግሊዝን 2ለ1 አሸነፈች፡፡ በጦርነቱ አንገቱን ደፍቶ የነበረው የአርጀንቲና ሕዝብ፣ በእንግሊዝ ሚዲያዎች ጩኸትና ፉከራ ተበሳጭቶ የነበረው ሕዝብ፣ ለደስታው ወሰን አልነበረውም፡፡ በዚህ ብቻ ሳይበቃ አርጀንቲና የዓለም ዋንጫውንም በማራዶና አስደናቂ ብቃት በመታገዝ አሸነፈች። በደስታ ላይ ሌላ ታላቅ ደስታ ተጨመረ። የአርጀንቲና ጋዜጦች “ማራዶና እንግሊዝን አሸነፈ” ብለው ጻፉ፡፡ ለእናንተ አንድ ሰው ይበቃችኋል ነው መልዕክቱ፡፡
እንግሊዞች ቂም ቋጠሩ፡፡ የማራዶናን ችሎታ ማጣጣሉን ተያያዙት፡፡ ሥነ፟ምግባር የጎደለው፤ አጭበርባሪ ወዘተ፡፡ ያልተናገሩትንና ያልጻፉትን መጥፎ ነገር መጥቀስ ይቀልላል፡፡ ማራዶና መልስ ሰጠ፡፡ ኳሱ በእጁ ተነክቶ ከነበረ “ይህ እጅ የእግዚአብሔር እጅ ነው” አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ግብዋ “The Hand of God” እየተባለች ትጠራለች፡፡ የአርጀንቲና ሕዝብ እንግሊዝን ለመበቀል ከእግዚአብሔር እንደተሰጠች የበደል ካሳ አድርጎ ይቆጥራታል፡፡
በቅርቡ ማራዶና በተወለደ በ60 ዓመቱ በልብ ሕመም አረፈ፡፡ የዓለም የእግር ኳስ ስፖርት ቤተሰብ ለዚህ ታላቅ የእግር ኳስ አንጸባረቂ ኮከብ የሰላም እረፍት ተመኘለት፡፡ እንግሊዞች በስፖርት ሜዳ የታየውን ሽንፈት እንደ ውርደት በመቁጠር “አጭበርባሪው አረፈ” እያሉ በሞቱ ሊዘባበቱበት ሞከሩ፡፡ የዓለም ስፖርት ቤተሰብ ግን ታዘባቸው፡፡ አርጀንቲናውያንና የዓለም የእግር ኳስ ስፖርት ቤተሰብ ታላቁን እግር ኳስ ተጫዋች በክብር ሽኙት፡፡
እንደገና ወደ አገራችን፡-
የእንግሊዝ ሚዲያዎች በቅርቡ በግፍ የተገደሉትን የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ሞት ከምንም ሳይቆጥሩ፣ በማይካድራ ስለረገፉት ንጹሐን ዜጎቻችን ምንም ሳይናገሩ፤ ጩኸት በለመዱ ሚዲያዎቻቸው የተባበሩት መንግስታት አገራችን ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ሲያስተባብሩ ከረሙ፤ ሆኖም ግን አልተሳካም። በአድዋ አልተሳካም፣ በመቀሌም አልተሳካም። ለማንኛውም እነሱን “በማያገባችሁ አትግቡ” ብለን ወደ ማንዴላ ወግ እንለፍ፡፡
“በማያገባችሁ አትግቡ”፡- ኔልሰን ማንዴላ
ምዕራባውያን አሜሪካንን ጨምሮ አፍሪካውያንን ዝቅ አድርጎ የማየት እብሪት አለባቸው፡፡ ሳይጠብቁት አንድ መልካም ሰብዕና የተላበሰ፣ በመርህ የሚመራ፣ ግርማ ሞገስ ያለው፣ በአስተሳሰቡ የመጠቀ፣ ትሁት ግን በጣም ደፋር፣ በእስር ብዛት አእምሮው ይላሽቃል ብለው ጠብቀውት የነበረ፤ ሆኖም ይበልጥ የሰላ፣ አነጋገሩ የተመጠነ ግን በጠንካራ መልእክት የተሞላ፣ ታላቅ መሪ ብቅ አለባቸው፡፡
ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችን በጥሩ ተምሳሌትነት ያነሳሳል ብለው ስለሰጉ፤ የማሳነስ፣ የማሸማቀቅና የማዋረድ ዘመቻቸው እንደተለመደው ለእንግሊዝ ሚዲያዎች በኃላፊነት ተሰጠ፡፡
ጩኸት አንድ፡-
ጥያቄ፡- ማንዴላ አምባገነኖችንና ሽብርተኞችን ይደግፋል ይባላል፡፡ ለምሳሌ ጋዳፊ፣ ካስትሮ፣ ያሲር አረፋት ወዘተ፡፡
ማንዴላ፡- አዎ እደግፋለሁ፡፡ በአፓርታይድ ስርዓት እንሰቃይ በነበረ ጊዜ የደገፉንን ሁሉ እደግፋለሁ፡፡ እናንተ የምትወዷቸውን የመውደድና የምትጠሏቸውን የመጥላት ግዴታ የለብኝም፡፡ ድጋፋችንም ሆነ ተቃውሞአችን ከአገራችን ጥቅም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በችግራችን ጊዜ የረዱንን በሙሉ ዛሬም እናመሰግናለን፡፡ ስለዚህ “በማያገባችሁ አትግቡ’’፡፡
ጩኸት ሁለት፡-
ጥያቄ፡- የፖለቲካና የኢኮኖሚ መስመራችሁ ካፒታሊዝም ነው ወይስ ሶሻሊዝም? ድርጅታችሁ ኮምኒስት ነው እየተባለ ይታማል…
ማንዴላ፡- ለእኛ ድመቷ ጥቁር ሆነች ነጭ አያሳስበንም፡፡ ዋናው ቁም ነገር አይጥ መያዟ ብቻ ነው፡፡ እናም አገራችንን የምንመራው ከእናንተ በምናገኘው መመሪያ ሳይሆን፣ ለአገራችን የሚያስፈልጋትን የኢኮኖሚ ድጋፍ ከየትኛውም አቅጣጫ ለመቀበል ዝግጁ በመሆን ነው፡፡
ጩኸት ሦስት፡-
“የአፍሪካ አዲሱ ትውልድ ተራማጅ መሪዎችን በመፍጠር ማንዴላን የማሳነስ ሙከራ”
የማንዴላ ተቀባይነትና አካሄድ አሳስቧቸዋል። ፊት ለፊት በሚደረጉ ውይይቶች ማንዴላን ማሳነስና ማጣጣል አልተቻለም፡፡ በመርህ ላይ የተመሰረተ ሃሳብ ይዞ የሚጓዝን ሰው በቀላሉ ማዋከብ አይቻልም፡፡ ዕቅዱ ተራማጅ አስተሳሰብ አላቸው የተባሉ “ወጣት የአፍሪካ መሪዎችን” መፍጠርና ከማንዴላ የተሻሉ እንደሆኑ ማስተጋባት ነበር፡፡ ተራማጅ አስተሳሰብ አላቸው የተባሉት በ1990 እ.ኤ.አ በተቀራረበ ጊዜ ወደ መሪነት ብቅ ያሉ መሪዎች ናቸው፡፡ እነሱም፡- መለስ ዜናዊ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ፖል ካጋሜና ዩዊሪ ሙሴቪኒ ናቸው፡፡
በአውሮፓና በአሜሪካ ስለነዚህ “ወጣት ተራማጅ መሪዎች” ያልተነዛ ፕሮፓጋንዳ የለም። ብዙም ሳይቆዩ መለስና ኢሳያስ አፈወርቂ ጦርነቱ ውስጥ ገቡ፡፡ ካጋሜና ሙሴቬኒ ግጭት ፈጠሩ፡፡ ማንዴላን የማሳነሱ ሙከራ ባይሳካም፤ “ተራማጆቹ መሪዎች” ሲበጣበጡ ነጮቹ ገላጋይ እየሆኑ በመቅረብ መሰሪ አጀንዳዎቻቸውን ለመትከል እረድቷቸዋል፡፡ የዚያን ጊዜ “ወጣት ተራማጅ መሪዎች” አገሮቻቸውን ወደ ሰላሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በመርህ የሚመሩት ማንዴላ ግን ከአምስት ዓመት በላይ በመሪነት መቆየት አልፈለጉም፡፡
አሁን ኢትዮጵያና ኤርትራ ነቅተዋል፡፡ እንደ ማንዴላ “በማያገባችሁ አትግቡብን’’ ማለት ጀምረዋል፡፡ የማዕቀብ ማስፈራራቱ ከነፃነታችንና ከሉአላዊነታችን አይበልጥብንም እያሉ ነው፡፡
የቲማቲም ማሳው፣የማራዶናም ሆነ የማንዴላ ታሪኮች የሚያጠነጥኑት የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት፤ ጥቅማቸው ላይ የተመሰረተ መሆኑንና ለጥቅማቸው ሲሉ ግለ-ሰብንና የአገር መሪን ከመፈታተን ወደ ኋላ እንደማይመለሱ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይህንን ለማክሸፍ የሚቻለው ህዝብና መሪዎቹ በጋራ ሲቆሙ ነው፡፡ መሪዎችም እንደ ማንዴላ በመርህ በመመራት ጠንካራ አቋም ሲያሳዩ ነው።
 “እኔ ባላቆየሁት አገር ልጄ መኖር አይችልም”
ዝግጅቱ በጦር ሜዳ ተገኝተው ለነበሩ ጋዜጠኞች ዕውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ ፕሮግራም ነው፡፡ “ዳዊት መሥፍን” የተባለ ጋዜጠኛ የጦር ግንባር ውሎ ታሪኮችን በንግግር ለታዳሚው አካፈለ፡፡ ንግግሩ በጽሁፍ ሲቀርብ ይህንን ይመስላል፦
“… አንዲት የሴት ወታደር ከውጊያው ከሶስት ዓመታት በፊት አንድ ህጻን ልጅ ትወልዳለች። ደቡብ ከልል ክሚገኙት ቤተሰቦቿ ዘንድ ለስድስት ወራት ያህል ዕረፍት ላይ ከቆየች በኋላ ወደ ምድብ ክፍሏ ትመለሳለች፡፡ የልጇ ናፍቆት ቢያስቸግራት፣ የእናትነት ሆዷ አላስችል ቢላት፣ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ እንደገና ልታየው ሄደች፡፡ አገኘችው፡፡ ናፍቆቱ አልወጣልሽ ስላላት፣ የሦሥት ዓመቱን ህጻን ወደ ምድብ ክፍሏ ይዛው ሄደች፡፡
መጥፎ አጋጣሚ ሆነና የዚያኑ ለሊት ጦሩን በከዱ አባላት ጥቃት ተከፈተ፡፡ ልጇን ምን ታድርገው? ባልደረቦቿ ለአገራቸውና ለሰንደቅ ዓላማቸው በቆራጥነት ለመሰዋት እየተዘጋጁ ነው፡፡ ከውስጧ የሚሰማትን ስሜት ልትቋቋመው አልተቻላትም፡፡ ወታደሮቹ በተከፈተው ድንገተኛ ጥቃት አዛዣቸው እንዳይገደሉ ወይም እንዳይማረኩ ሸፋን ለመስጠትና ክአዛዣቸው በፊት በመውደቅ ቃለ-መሃላቸውን ለመፈጸም በቆራጥነት ውጊያ ጀምረዋል፡፡ ከአገርና ከልጅ፣ ለዚያውም የሶሰት ዓመት ህጻን ለምርጫ የቀረቡላት ወታደር፣ ህጻን ልጇን ብድግ አድርጋ ጀነራሉ ጋር አስቀመጠች። ፊቷን ወደ ኋላ ሳትመልስ ለአገሯ ክብር፣ ለልጇ ብሩህ ህይወት ለመዋጋት ከባልደረቦቿ  ጋር ተቀላቀለች፡፡ የወደቀው ወድቆ ጥቃቱን በመመከት ሰራዊቱ ወደ ማጥቃት ተሸጋገረ፡፡ በመቀጠልም አኩሪ ድል ተቀዳጀ፡፡
ጋዜጠኛው፦ እንዴት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ለመወሰን ቻልሸ?
ወታደሯ፦ መልሷ አጭርና ግልጽ ነበር፡፡ “እኔ ባላቆየሁት አገር ልጄ መኖር አይችልም”
ከድል በኋላ ምን ይጠበቃል?
ከጦርነት በኋላ የድል አጥቢያ አርበኛ ይበዛል፡፡ ስለ ድሉ ማውራት፣ ማን በየትኛው አውደ ውጊያ፣ ምን አይነት ገድል እንደፈጸመ፣ ያልተጻፈ ሁሉ መነበብ ይጀምራል፡፡ የታሪክ ሽሚያ ይጧጧፋል፡፡ የምሁራን ትንተና ይበዛል፡፡ የሚዲያዎች የሰበር ዜና ፉክክር ጣራ ይነካል፡፡ የዚህን ጊዜ በመርህ አክባሪነታቸውና የአመራር ችሎታቸው፣ እንዲሁም በጦርነት ውስጥ በማለፍ ካገኙት ልምድ በመነሳት እንደ አጼ ምኒሊክና አብርሃም ሊኒከለንን ዓይነት መሪዎችን ማስታወስ ጠቃሚ ይሆናል፡፡
ትንሽ ስለ አጼ ምንሊክ፡-
ሕዝብንም ጦርነትንም እንዴት አድርጎ መምራት እንደሚቻል የሚያውቁ ታላቅ መሪ ናቸው፡፡ ምድባቸውም ከነአብርሃም ሊንከንና ከማንዴላ ጋር ነው፡፡ ምንሊክ የሚመሩት ሕዝብ ‘’እምየ” ምኒሊክ እያለ የሚጠራቸው፣ እንዲህ ብለህ ጥራቸው ተብሎ ስለታዘዘ አይደለም። ከተግባራቸው በመነሳት እንጂ፡፡ ምንሊክ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ጥቁር ሕዝቦችም የሚኮሩባቸው መሪ ነበሩ፡፡
ምዕራባውያን በተለይ ጣሊያንና እንግሊዝ የምንሊክ ስም ሲነሳ ያንቀጠቅጣቸዋል፡፡ “በእንግሊዝ የሚመራውን አፍሪካን የመቀራመት ዕቅድ” አድዋ ላይ ቀንዱን የሰበሩት እሳቸው ናቸው፡፡ የእሳቸውን ክብር ለማዋረድ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ተላላኪ የሆነው ወያኔ፣ የቤት ሥራ ተሰጠው፡፡ በምንሊክ ላይ ዘመቻ ጀመረ፡፡ ዘመቻውን ሳያጠናቅቅ እንደ ጉም ተበተነ፡፡
ምኒሊክ የጣልያንን ጦር ድል ከመቱ በኋላ በዕብሪት አልታበዩም፡፡ ይልቁንም ጦርነቱ ከአስከተለው ሰብአዊ ጉዳት በቶሎ ለማገገም ይጥሩ ነበር፡፡ የኢጣልያን ምርኮኞች ያስተናገዱበት መንገድ ታላቅ ሰብእና ያላቸው መሆናቸውን የሚገልጽ ነበር፡፡ ታላቅ መሪ ከድል በኋላ ፍርዱን ለሕግና ለፈጣሪ በመተው፣ ትኩረቱን በጦርነቱ የተፈጠሩትን ቀዳዳዎች መድፈን ላይ ያደርጋል፡፡ መሰራት ሲገባቸው ያልተከናወኑ ተግባሮችን ለመስራት ደፋ ቀና ማለቱን ይቀጥላል፡፡       
ትንሽ ስለ አብርሃም ሊኒከለን፡-
አሜሪካ ካፈራቻቸው መሪዎች ከታላላቆቹ ተርታ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ዝርዝር የሕይወት ጉዞው አስተማሪ ነው፡፡ በፕሬዚዳትነት ዘመኑ አሜሪካ ከ3 ዓመታት በላይ የዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገባች። የባሪያ ንግድ መቆም አለበት፣ በተጨማሪም አሜሪካ አንድ መሆን አለባት በሚሉና የባሪያ ንግድ መቆም የለበትም፣ እንዲያውም ከአንድነቱ እንገነጣጠላለን የሚሉ ወገኖች በሌላ በኩል ተሰለፉ፡፡ አብርሃም ሊኒከለን አገር አትበታተንም፣ የባሪያ ንግድም አይኖርም በሚለው አቋም በመጽናት ጦርነቱን በአሸነፊነት አጠናቀቀ፡፡
አብርሃም ሊኒከለን በጦርነቱ ውስጥ እያለ ካደረጋቸው ንግግሮች ስለ ሕዝብ፣ ስለ መንግስትና የጦርነቱን ማብቃት አስመልክቶ የተናገራቸው ለወቅቱ የአገራችን ጉዳይ የሚጠቅሙ ናቸው፡፡
“ስለ ሕዝብ”   
“…የሕዝብ አስተያየት ከተከተሉ ምንም ዓይነት ውድቀት አይኖርም፤ የሕዝብን ሃሳብ ካልተቀበሉ ግን ምንም ዓይነት ድል ማድረግ አይቻልም፡፡”
ስለ አንድነት
“…የተከፋፈለ ቤት አይፀናም፣ ይህ መንግስት በከፊል ነጻነትን፣ በከፊል ደግሞ ባርነትን እየደገፈ ጸንቶ መቆም አይቻለውም፡፡”
“ስለ ጦርነት”
“…የአገሪቱን ችግር ማከም፤ ጦርነቱን የተዋጉትን ወታደሮች መንከባከብ፤ ባሎቻቸውን ያጡትን ሴቶችና ወላጆቻቸውን የተነጠቁትን ሕጻናት መደገፍ ዘላቂ በሆነ መንገድ ልናከናውናቸው የሚገቡ ዋነኛተግባሮች ናቸው፡፡”
እንደገና ወደ ዋናው ጉዳይ
ከላይ በዝርዝር እንዳየነው አሁን ላጋጠመን ችግር፤ እንደ ዋና ዋና ምክንያቶች የሚቆጠሩት፤ ከአለፉት መንግሥታት ውድቀት ያለመማር፣ በዘር የተቃኘ የፖለቲካ አስተሳሰብና ከውጭ ጣልቃ ገቦች ሴራ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር “ሲያልቅ አያምር” እንደሚባለው፣ በዘር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ሥልጣን መጨረሻው ውድቀትና ኪሳራ ነው፡፡ የሀብትና የዕውቀት ምንጮች “ዘር” አና “ስልጣን” ከሆኑ የሚያስከትሉት እብሪት ህሊናን የመጋረድና ልቡናን የመንሳት አቅም አላቸው፡፡ በጣም ደካማና ሰነፍ የሆኑ ሰዎች “በዘር ጥላ” ስር ተጠልለው የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት አገርንና ህዝብን አደጋ ላይ ይጥላሉ፡፡ ለዚህ ዋና መፍትሔው ካለፉት ሁኔታዎች መማር ነው፡፡
የመጨረሻው መጨረሻ፣
የጦርነቱ ዋና አሸናፊዎች ህዝቡና መከላከያ ሠራዊቱ ሲሆኑ፣ መንግስትም ላሳየው ከፍተኛ ጥረት ተገቢው ክብርና ምስጋና ሊቸረው ይገባል:: ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚረዱ ነጥቦች ውስጥ፤ በመጀመርያ ራስን ማወቅ፣ ቀጥሎ ደግሞ ራስን በሌላው ቦታ አድርጎ ማየት፣ በችግሮቻችን ላይ የሃሳብ የበላይነት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡
የችግሩ ዋና ምክንያት የሆኑት ፖለቲከኞችና የመንግስት ባለስልጣናት፣ ራሳቸውን በግንባር እየተዋደቁ ባሉት (ህዝቡና መከላከያው) ቦታ አስቀምጠው በማየት እኔስ ብሆን ኖሮ? እያሉ ማሰብ ይገባል፡፡ የችግሩ መፍትሄ ክሃሳብና ከጠራ አመለካከት እንደሚገኝ በመረዳት፣ በግል ህይወታቸውም ሆነ የፖለቲካ ተሳትፎአቸው ግልጽ የሆነ መርህ ሊከተሉ ይገባል፡፡
ህዝቡም፦
በመርህ ላይ ተመስርተው፡ “ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ በማንኛውም ወቅት ትክክለኛ አሰራር ተከተል” የሚለውን አስተሳሰብ የሚከተሉና የሚተገብሩ ግለሰቦችን፣ መሪዎችንና ፓርቲዎችን ለይቶ ማወቅ ለትክክለኛ ውሳኔ ይረዳዋል፡፡


Read 10739 times