Monday, 14 December 2020 19:54

የኮሎኔሉ የግጥም ስንኞች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

   በመጀመሪያ ;የግጥም ቃላት፣ ወደዚች ዓለም መግቢያ በሮች (gateaway) ናቸው “ይላሉ፤ ኖርማል ፍሬድማንና ቻርልስ ኤ ለፍሊን፡፡ ዓለም ውስጥ ያለ ሰው በሌላ ቀለም፣ በሌላ ምስል፣ በሌላ ውበት ብቅ እንዲል---የግጥም ዓለም፣ በውኑ ዓለም ላይ የራሱን ዓለም ይፈጥራል፡፡ ምናባዊነት ሙዚቃዊነት፣ እምቅነት፣ እያለ ባላቸው ባህርያት የምናውቀውን የሰው ልጆች ደፓ ወይም የእንስሳትን ዓለም አሊያም ግዑዟን ፍጥረት በዘይቤ እያቀማጠለ፣ በጥበብ እየዘለዘለ--ሊሰጠን ይችላል፡፡
ገጣሚ ደግሞ ሰው ነው፤ ሰው ደግሞ ህይወቱ ባለ ብዙ አንጓና ባለብዙ ፈርጅ ነው። ስለዚህ ጠበቃ ቢሆን፣ ወታደር ቢሆን፣ መምህር ቢሆን መሃንዲስ -- በረዥም አፍንጫው ያሸተተውን፣ በንስር አይኑ የመዘዘውን፣ ከህይወት ማዕድ የቀመሰውን መልሶ በእኛው መሶብ ይፈተፍትልናል፡፡ ቅመሙ፣ ቅባቱ፣ የሞያው ልክ ቢለያይም፣ ያጠቀሱትን ህይወት ከሽኖ ያቀርባል፡፡
በተለይ ወታደሩ የጦር ሜዳውን የጥይት አረር፣ የታንኩ ግሳት፣ የሚጉን መብረቃዊ ምህታት፣ የምሽጉን ዜማ - ለማካፈል ላቅ ያለ ስሜት የሚፈጥርበት ይመስለኛል። በተለይ በጦርነት ዐውድ፣ በነፃነት ምጥ፣ በሉዓላዊነት ትጋት ውስጥ ብዙ ገጣሚያን ይወለዳሉ፤ይህንን ደግሞ ብዙዎች የሩሲያ ገጣሚያን ያሳዩ ይመስለኛል፡፡ እኛ ሃገርም እነ ክፍሌ አቦቸር፣ እነ ሞገስ ሀብቱ፣ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሌሎችም በርካታ ገጣሚያን አሉ፡፡
ሰሞኑን አየሩን የሞላው ወታደራዊ ጠረን፤ የሀገር መከላከያ ተጋድሎ ስለ ሆነ ልባችን ወደዚያ ያዘመመ ይመስለኛል”…….የኔ ልብም ለወትሮም ለወታደሩ የሚሰርቀው አድልዎ፣ የሚቆጭበት አጸድ አለው፡፡ ለብቻ ተወርተው በልብ የሚተኙ ሀሳቦች ብዙ፣ የመለዮ ለባሹ ግን በቁጭት ጥርስ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ነፍሱን የሚሰጥ የሀገር ዘብ!.....
ታዲያ ሰሞኑን እጄ የገባች የአንድ ኢትዮጵያዊ ኮሎኔል የግጥም መፅሀፍ “የት ውይ የት ልደር” በሚል ርዕስ ተፅፎ ሳይ “እኛ ልብ ውስጥ ውለህ እኛ ልብ ውስጥ ውለህ እደር;፤ ያኔ ነገርም ሀገርም ትለወጣለች ብያለሁ፤ በልቤ፡፡ እስቲ ሌተናል ኮሎኔል ተስፋዬ ኤፍሬም ስለ ወታደር ምን ይላል?..... "የወታደር ፍቅር" የሚል ርዕስ በሰጠው ግጥሙ፡-
 ወታደር ለፍቅሩ
ልቡ ላይ ላደሩ
ለብዙሀን ምቾት
በፍቅር በደስታ ምቾቱን የጠላ
ነፍሱን ጭዳ አድርጎ እንደ አልማዝ ያበራ
ምንም ቢሆን ግብሩ
ከብረት የተባን ነጻነት ፈላጊ፣
ግራ ማይጋባ ፅናትን ጠያቂ፣
በህይወቱ መስፈርት ወታደር ለፍቅሩ
በላቀ ጀግንነት በስማዕት ክብሩ
እንደ ሻማ ቀልጦ ሺዎችን አፍርቶ
ሃገርን  የሚያህል
ብርሃን ይሞላዋል ነፃነት አብርቶ፡፡
ኮሎኔሉ ገጣሚ ተስፋዬ ስለ ምሽግም የፃፋት ግጥም አለች፡፡ ምሽግ የወታደር ቤት ናት፤ ጓዳ- ሳሎን- መኝታ ቤቱም፡፡ ስለዚህ ትዝታው የቤትን ያህል ምናልባት ከዚያም የላቀ ሊሆን ይችላል፡፡ ምሽግን ባልኖርበትም ግንባር  ሄጄ፣ በዐይኖቼ ስላየሁት ምስሉ መቼም አይጠፋኝም፡፡
ሻምበል ብርቅነህ ዑርጋ ፡-
በረሃ ነው ቤቴ የቀበሮ ጉድጓድ
ቤተሰቤን ሳላይ ሳይናፍቀኝ ዘመድ
ትጥቄንም አልፈታ ወገቤን አስሬ
ላገሬ ልሰዋ አለብኝ አደራ ያለው -- ለዚህ ይመስለኛል፡፡
ወታደር ስለ ምሽጉ  ትዝታ  ብዙ ሊያወራ ይችላል፡፡ የባለቤቱን ደብዳቤ የፍቅረኛውን ድምፅ የሚሰማበት የእረፍት ክልሉ፣ የትዝታውም ማጠንጠኛ ማማ ልትሆን ትችላለች፡፡
ኮሎኔል ተስፋዬ ”ምሸጌ” በሚል ግጥሙ እንዲህ ይላል፡-
ቅድመ- ድህረ ፍልሚያ ትንፋሽ መሰብሰቢያ
እንዴት ነሽ ምሽጌ የህይወቴ አምሳያ
የገዢ መሬት ቤት
መከታ ምሽጌ
ደረት ሳንባ ጣፊያ ጭንቄ እንዳይመታ
ግቤን ሳላጋምስ  ቶሎ እንዳልረታ
የእኔ እሳተ ጥላ
ምድር ቀውጢ ስትሆን የእሳት መጋረጃ
የሩሄ ማክረሚያ የስጋዬ ግምጃ
ጠላቴ ሳይቀድመኝ በማሽን ገን መፍጃ
እግረ መንገዱንም
የመቃብር ኑሮን በቁም መልመጃ፡፡
ከጦርነት በፊትና በኋላ  ሀሳብ መሰብሰቢያ ፍቃድ ማውጫ ናት፤ ብዙ ጊዜ በወታደራዊ አጠራር ገዢ ቦታ በመባል በሚጠራው ስፍራ ራስን በብቃት ለመከላከል፣ የተመረጠና በጠላት ላይ የበላይነት ለማግኘት የሚያበቃ ስፍራ ነው፡፡ ምሽግ የሚቆፈረውም  እንደዚህ ባለ የተመረጠ ስፍራ ነው፡፡ በረሃ ካልሆነ በቀር ተራራ ላይ በከፍታ ቢሆን ይመረጣል፤ እናም ምሽግ ደረትን ከጥፋት፣ ህይወትን ከሞት ለመጠበቅ --- ይሰውራል። በወታደራዊ አጠራር መከታም ከለላ ከሚሉት መከተቻና መጠለያዎች፣ መከታም ከለላም ሆኖ ያገለግላል፡፡ ስለዚህ ወታደርና ምሽግ ፍቅራቸው የትየለሌ ነው፤ አያምጣው እንጂ በጠላት የበላይነት ጊዜ መቃብርም ትሆናለች፡፡
ወታደር ህይወቱና ሞቱ እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ አፍንጫ ለአፍንጫ እየተሻተቱ የሚኖሩበት ህይወት ነው፡፡ ስራው ሀገርን መጠበቅ ነው፤ ሀገርን ሲጠብቅ ሀገሩን የሚነካ ጠላት ይኖራል፤ያኔ ለሀገሩ ይጋደላል፤ ይህ ተጋድሎ ደግሞ ወኔና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ “ሞተሃል” የሚለው የኮሎኔሉ ግጥም ይህንንም ነካክቷል፡፡ ግጥሙ  በ20008 ዓ.ም ባይደዋ ላይ የተፃፈ መሆኑን የግርጌ ማስታወሻው ይነግረናል፡፡ ስንኞቹን እዋሳለሁ፡-
ቁልቁል ተንከባለህ
ወደ ላይ ተስበህ
ወድቀህ ተጋግጠህ አሳር በልተህ ፍዳ
ስለ መሹለክ አልፈህ በመርፌ ቀዳዳ
የብላጌን ጤዛ የበጋ አፈር ልሰህ
“ይታለፋል ችግር” በማለት  ከተሳነህ
ውስጥህ ተስፋ ቆርጦ ከተልፈሰፈስክ
ሃሞትህ እንደውሃ ወርዶ ከፈሰሰሰ
ያኔ  አብቅቶልሃል
ብለሃል ማለት ነው የተገላቢጦሽ
አህያን ወደ ቤት ውሻን ወደ ግጦሽ
በጦር ሜዳ በመርፌ ቀዳዳ የመሹለክ ያህል ጠባብ ዕድል፤መጋጋጥና ምጥ እንዳለ ከስንኞቹ አውርቶናል፡፡…… እናም በጦር ግንባር ያለው አንድ የድል መንገድ፣ የነፃነት ችቦ መጨበጫ ቀዳዳ፣ ተስፋ ያለ መቁረጥ ነው፡፡ ኮስታራ ሃሞት ሩቅ የሚያዩ አይኖች!
ወታደር ለሀገር ዘብ የሚቆም፤ ነፍሱን ስለ ሌሎች የሚሰጥ ቢሆንም፣ ሰው ነውና ሕይወትን እንደ ሰው ያውቃታል፡፡ በየዕድሜ አንጓው ያለውን ጣም ያጣጥማል፡፡ ወታደር በልጅነቱ ልጅ ነው፡፡ ከባልንጀሮቹ ጋ ልጅ የሆነ ሁሉ የሚያደርገውን አድርጎ ያድጋል፡፡ በወጣትነቱም  ወጣት ሆኖ፣ በትኩስ ስሜት በንቁ አእምሮ እርሻውን ያርሳል፣ ንግዱን ይነግዳል፣ ለጥቆም ስልጠናውን ወስዶ ከሌሎች በተሻለ ንቃትና አካላዊ ብርታት የተሰጠውን ግዳጅና ሃላፊነት ይወጣል፡፡
ታዲያ ወታደር ሰው የሚያሰኘውን ሁሉ ያሰኘዋል፤ ተፈጥሮአዊ ነውና ፆታዊ ፍቅር፣ በልቡ ተወልዶ ያድጋል….. ወታደር አንደኛውን በፍቅር ስሜት ጠውልጎ ሲፈካ አሳድዶ በእጁ ሊያደርግ ይተጋል፡፡…. አንደኛው ይደዋወላል፣ አንደኛው ይናፍቃል፤ አንደኛው ያገባል፤ ይወልዳል፡፡
በፍቅር ይደሰታል፤ በፍቅር ያዝናል… የኮሎኔሉ ግጥሞች የፍቅር ቃናም ያዘለ ሀሳቦች፣ ብርሃንና ጭጋጎች አሏቸው። የወታደር ድል በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በፍቅር ዓለም በናፍቆት እልፍኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ጀግናም ያፈቅራል፡፡ ትልቁን ጄኔራል ናፖሊዮን - ጆሴፊን በፍቅር ጥላው ነበር፡፡ ስታሊንም - ትንሿ ባለቤቱ ማርካው እጁን ሰጥቷት ነበር፡፡
“የት ውየ የት ልደር” የሚለው የሌተናል ኮለኔል ተስፋዬ ኤፍሬም መፅሐፍ ውስጥ “የልብሽ” በሚል ርዕስ የተፃፈው ግጥም ገፀ ሰብ - ሐዘንና ትካዜን፣ ትዝብት ቁጭትን ሲያላምጥ ተደራሲያን  “አጀብ“ እንላለን። ፍቅር አጀብ ያላሰኘው ማናለ? እንዲህ ይላል፡-  
ስለ እውነት ልብሽ፣
ይወደኛል ፍቅሬ ብዬ አልጠይቅሽም
ስላንቺ ለማወቅ
ፆም ፀሎት ሱባኤ ፈፅሞ አያሻኝም
ውዴ ከጉሮሮሽ ወርጄ በልብሽ
ፍፁም እንዳልነበርኩ
ግብዝ ሁለመና፣ ፀያፍ አንደበትሽ
እራሱ ነገረኝ ጣይ የሞቀው ግብርሽ፡፡
ጥያቄ የማያሻው ጥርጣሬ፣ የማያሻማ ፆም ፀሎት ሱባኤ የማያሻው ሀቅ አይኑን አፍጦ ቆሟል፤ ስለዚህ ፍቅሯ ከጉሮሮ ያላለፈ፣ ከምላስ ያልዘለለ፣ ወደ ልቧ ገብቶ ቦታ የተሰጠው፣ ስር የሰደደና ፍሬ ያፈራ እንዳልሆነ የገባው ገፅ ሰብ፤ ነገሩ ሲገባው እንዲህ ሲል ነገሩን ያከፋዋል፡፡
ለካስ!
ልብሸ ላይ ተመትረው ጎጆ የቀለሱ፤
በመልካም ፈቃድሽ ሲመጡ ሲገቡ፤
ውሎ እያደር ገባኝ ወዲህ ነው ነገሩ
የልብሽ መግቢያ በር ነበርኩኝ ጉበኑ፡፡
  ስሜቱ የጠወለገ፤ ልቡ በፀፀት የተገረፈው ተራኪ፣ መንገድ ሆኖ ያሳለፈበትን ዘመን በፀፀት ያኝካል፤ በሰቀቀን ያወጋል፡፡ እንግዲህ ግጥም ለሳቅ ብቻ አይደለም፤ የምስራችም መርዶም፤ ሙሾም መወድስም፤ ቀረርቶም------- ነው፡፡
ሀገራችን በጀግኖች ልጆቿ መስዋእትነት ከጥፋት ባመለጠችበት በዚህ ሰሞኗ ሁኔታ፣ የሌተናል ኮሎኔል ተስፋዬ ኤፍሬም መጽሐፍ እንደ ማስታወሻ ብቅ ስላለች፣ በቆፍጣና ስሜት ውስጥ ታዘልቀናለች፡፡
ለወደፊትም ገጣሚው ተሰጥኦውን ጠብቆ፣ ንባብ ጨምሮ፣ ጉድለቶቹን ቀንሶ ቢፅፍ፣ የጀግንነት ዐውድ፣ የጦር ግንባር ሕይወትና ዓለምን በተሻለ ሁኔታና አቅም ሊያሳየን ይችላል፡፡  Read 1940 times