Print this page
Tuesday, 15 December 2020 00:00

ብልጽግና ውስጥ የመሸጉ “ግልገል ጁንታዎች” - ዶ/ር ዐቢይይ ሆይ፤ ጽናቱን ይስጥዎ!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል
Rate this item
(2 votes)

ለአርባ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያና የትግራይ ህዝብ ራስ ምታት የነበረው ህወሓት የግፉ ጽዋ ሞልቶ፣ የማይነካውን ቀፎ ነክቶ በተወሰደበት ወታደራዊ እርምጃ ከመንበረ ስልጣኑ መነሳቱን ከሰማሁ በኋላ “ከእንግዲህ በፖለቲካ ጉዳይ አልጽፍም” ብዬ “ብዕሬን ሰቅዬ” እንደ ማንኛውም ዜጋ በግል ጉዳዬ ታጥሬ፣  የራሴን  ኑሮ እገፋለሁ የሚል ውሳኔ ላይ ደርሼ ነበር - ሰሞኑን፡፡
ለትግራይም፣ ለኢትዮጵያም ብሎም ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አደገኛ “መርዝ” የነበረው ህወሓት መወገዱ በርግጥም የእፎይታ ጅማሮን ያመላከተ ቢሆንም፤ የአማራና የኦሮሞ ማህፀን ያፈራቸው፣ ብልጽግና ውስጥ የመሸጉ “ግልገል ጁንታዎች” በድል ሰክረው፣ማህበራዊ ሜዲያ መደንፋት መጀመራቸውን ሳይ፣ ራሴን ይዤ “ዶ/ር ዐቢይ ሆይ፤ ጽናቱን ይስጥዎ!” አልኩ፡፡ “ዶ/ር ዐቢይ ሆይ፤ ጽናቱን ይስጥዎ!” ከማለትም አልፌ አፎቱ ውስጥ የከተትኩትን ብዕር በማንሳት ይህቺን ማስታወሻ ከመክተብ ተነሳሁ፡፡
ሰሞኑን መገናኛ ብዙሃን እንደነገሩን፤ ትምክህት ልባቸውን የደፈነው፣ ማስተዋል የተሳናቸው፣ የህወሓት ቆሞ ቀሮች በቀሰቀሱት ጦርነት በዳንሻ፣ በማይኻድራ፣ በትግራይ ልዩ ልዩ ስፍራዎችና በራያ አካባቢዎች ንፁሃን ወገኖቻችን እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡ ተጨፍጭፈዋል። ተርበዋል፣ ተጠምተዋል፡፡ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል፣ ሀገር ጥለው ተሰደዋል፡፡ እናም ይህ ወቅት የሞቱትን የምንቀብርበት፣ እርማችንን የምናወጣበት፣ በኀዘን አንገታችንን የምንደፋበት ጊዜ መሆን ሲገባው፤ ይህ ወቅት የተሰደዱትን ወደ ቀያቸው የምንመልስበትና የምናቋቁምበት ጊዜ መሆን ሲገባው፤ ይህ ወቅት የፈራረሱ መሰረተ ልማቶችን የምንጠግንበት ጊዜ መሆን ሲገባው፤ የኀዘን ድንኳኑ ሳይነቀል በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የመሸጉ “ግልገል ጁንታዎች” በህዝብ ስም በመማልና በመገዘት እንደገና ሰላማችንን ለማደፍረስ ያላቸውን “ቁርጠኛነት” እያሳዩን ነው፡፡
እነዚህ ብልጽግና ውስጥ የተሰገሰጉ “ግልገል ጁንታዎች”፤ የህወሓትን ፋሽስታዊ መስመር ተከትለው የበቀሉ፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ከፋፋይና ዘረኛ ጥንስስ እየተጋቱ ያደጉ ናቸው ይላሉ- አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ እነዚህ ሰዎች በብልጽግና ህብረ ብሄራዊ “የመደመር ጠበል” ቢጠመቁም በደም በአጥንታቸው የሰረፀው አደገኛ የዘር “መርዝ” እንዲህ በዋዛ፣ በአጭር ጊዜ የሚለቃቸው አለመሆኑን ርቀው ሳይሄዱ፣ ህወሃት ላይ ገና አፈር ሳይመለስ  እያስተዋልን ነው፡፡ ህብረ ብሄራዊነቱን ከምር አምነውበት “የተደመሩ” ባለመሆናቸው አንዳንዶቹ “እርስት እናስመልሳለን” ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ የመብት ጥያቄ ያነሳውን ሁሉ “አሃዳዊ” የሚል ታርጋ ለጥፈው በ“ኬኛ ፍልስፍና” ሁሉን ነገር ለመጠቅለል ሲራወጡ ይታያሉ - ይሄ ሁሉ የሚሆነው የሞቱትን ሳንቀብር ነው…
የፖለቲካ ፓርቲ ዋነኛ ተግባር በየደረጃው ሀገር የሚመሩ ሰዎችን ማፍራት ነው፡፡ እናም የፖለቲካ ጨዋታ የሀገር መሪዎች ፉክክር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይሁንና ይህ ፉክክር የ“ጨዋታ” ህጎችም አሉት። ባደጉና በሰለጠኑ ሀገሮች እንደሚታየው፣ የፖለቲካ ጨዋታው በአደባባይ በህዝብ ፊት የሚከናወነው በምርጫ ወቅት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በተገኘው አጋጣሚ በየማህበራዊ ሜዲያው እሰጥ - አገባ የለም፡፡ የኛዎቹ የብልጽግና ልዑላን ግን የሞቱ ወገኖቻቸው አስከሬን በየጥሻው ወድቆ፣ ህፃናት - እናቶችና አረጋውያን ቤት ቀያቸውን ጥለው ተሰደው፣ የከተማ ነዋሪዎች በውሃ - በመብራትና በሌሎች የእለት ከእለት ፍጆታዎች እጦት እየተሰቃዩ፣… እነሱ በፌስቡክ ጎራ ለይተው ይዘላለፋሉ - ይሄ ሁሉ የሚሆነው የሞቱትን ሳንቀብር ነው…
እንዲህ ያለው ሁኔታ ይሉኝታ ቢስነት ነው። ቀድሞ ነገር ብልጽግና ፓርቲ “ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ነው” ከተባለ “የአማራ ብልጽግና፣ የኦሮሞ ብልጽግና፣ የሱማሌ ብልጽግና፣…” በሚል ስም መግለጫ ማውጣት ህጋዊነት አለው ተብሎ አይታመንም፡፡ እንዲህ ያለ አደረጃጀት ሊኖርም አይችልም፣ አይገባም። ስያሜያቸው እንደሚያመለክተው፤ በየክልሉ ያሉት ቅርንጭፍ ጽ/ቤቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ በህብረ ብሄራዊነት ካባ የሚካሄድ ብሄርተኛነት ነው። በብልፅግና ቅርንጫፍ ስም አክራሪና ፅንፈኛ ብሄርተኛነት እየተፈጠረ ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ ይሉኝታ ባይኖራቸው ነገ ለምርጫ ፊቱ የሚቀርቡትን ህዝብ ማሰብ ተገቢ ነው። “ብልጽግና” የሚባል ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ መስርቶ፣ ብሄርተኛ አቋም ማራመድ ወይ ድንቁርና ነው ወይ አጭበርባሪነት ነው። የፖለቲካ አጭበርባሪነት ደግሞ እንደ ህወሓት ያስወግራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጓዳ ጉዳያችሁን በጓዳ መጨረስ ሲገባችሁ፣ አንጃ ግራንጃ ይዞ ወደ አደባባይ መውጣት፣ ከማደናገር አልፎ ህዝብን መናቅ ከመሆን የዘለለ ትርጉም ያለው ሆኖ አይታየኝም። ጎምቱዎቹ የክልል መሪዎች ጭምር የሚሰጡት መግለጫ ውሎ አድሮ፣ ነገ ከነገ ወዲያ ወደ ጦርነት የሚገቡ ነው የሚመስለው። ተከታዮቻቸው ጎራ ለይተው በፌስቡክ ጦርነቱን ተያይዘውታል - ይሄ ሁሉ የሚሆነው የሞቱትን ሳንቀብር ነው…
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ጥናቱን ይስጥዎ፡፡ እነዚህን ልበ ድፍን ፖለቲካ ያልገባቸው ድሁራን ይዘው ብልጽግና ማምጣት ቀርቶ አንድ ወንዝ ማሻገር የሚችሉ መስሎ አይታየኝም። እንደኔ እንደኔ መፍትሄ ሆኖ የሚታየኝ አንድም የፓርቲ ዲሲፕሊን በጥብቅ እንዲከበር ማድረግ፤ ሁለትም እንደልባቸው የሚፏልሉ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ “ውርዴ” የተጠናወታቸው የህብረ ብሄራዊነት ካባ የደረቡ ብሄርተኛ ተኩላዎችን ማራገፍ ነው። ሌላው በረጅም ጊዜ መታየት የሚገባው መፍትሄ ሊያጠፋን የተነሳውን የብሔር/የጎሣ ፖለቲካ ሳያጠፋን ማጥፋት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በብሔር/በጎሣ መደራጀትን በህግ ማገድ አማራጭ የሌለው አማራጭ ነው፡፡
ብእሬን ካነሳሁ አይቀር… ለህወሓት አባላት፣ ደጋፊዎችና ግልገል ካድሬዎች አንዲት መልእክት ልጨምር… የህወሓት ደጋፊዎች ዛሬም ሲወራጩ ይስተዋላሉ። “እኛ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እኛ ገዢ፣ እኛ ፈላጭ ቆራጭ… ካልሆንን”…… ብላችሁ ትግራይን እየገደላችኋት ያላችሁት፣ ህዝቡን እየጨፈጨፋችሁ ያላችሁት እናንተው ራሳችሁ ናችሁ፡፡ ማንንም መወንጀል አትችሉም፡፡ በ45 ዓመታት ውስጥ የትግራይን ህዝብ በሦስት ትልልቅ ጦርነት ማገዳችሁት፡፡ ከደርግ ጋር፣ ከኤርትራ ጋር፣ አሁን ደግሞ ከሀገሪቱ መከላከያ ጋር ተዋጋችሁ፡፡ ህዝቡን ፈጃችሁት፣ አስፈጃችሁት፡፡ የፖለቲካ ጥያቄያችሁን በሰለጠነ መንገድ ማቅረብ፣ መታገል ሲገባችሁ ይህንን ህዝብ የእሳት እራት አደረጋችሁት፡፡ እናንተ ከታሪክ የማትማሩ ግትሮች፣ ጉረኞች፣ ትምክህተኞች፣… ናችሁ! ጣታችሁን ወደ ሌላ ሰው አትቀስሩ፡፡ ችግሩ ያለው እናንተው ጋ ነው… አለማፈራችሁ ከእናንተ ቡድን ውጪ ያለን ትግራዋይ “ምስለኔ” ትላላችሁ፡፡ ከዚህ በላይ ጉራ፣ ከዚህ በላይ ትምክህት፣ ከዚህ በላይ እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ፣ ከዚህ በላይ እኔ ብቻ ነኝ የትግራይ ጠበቃ ባይነት አለ?
ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም የተቋረጠው የእርስ በርስ ጦርነት ህዳር 19 ቀን 2013  ዓ.ም ተጠናቀቀ፡፡ የእኛ ትውልድ ያን ትውልድ፣ በሰላምም በጦርነትም ሁለት ጊዜ አቸነፈ - በ1997 ዓ.ም በምርጫ ዘረራችሁ! እነሆ ዘንድሮ በ2013 ዓ.ም ደግሞ በፍትሀዊ ህግ የማስከበር ዘመቻ በጠመንጃ ማረካችሁ። ድሉ የትግራዋይና የመላው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እናንተ ብን ብላችሁ ትጠፋላችሁ እንጂ የትግራይ ህዝብ ከእንግዲህ ነፃነቱን ጨብጧል፡፡ ዳግም ወደ እናንተ ባርነት አይመለስም፡፡ አሸባሪዋ ህወሓትም እንደ ኢሠፓ በኢትዮጵያ ምድር ህልውና አይኖራትም፡፡ ቁርጣችሁን እወቁ!


Read 10016 times