Monday, 14 December 2020 18:09

ምን ሙዚቃ አለና!... ራፕ ብቻ ነው

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

"“ለኢትዮጵያ ትክክለኛው መንገድ የእኛ ብቻ ነው” የሚሉዋት ነገር ‘አደብ ገዛች’ ስንል አፈር ምሳ እየተነሳች አስቸገረችንሳ! ለነገሩ መንገድ የብቻም ሆነ የጋራ የሚሆነው መጀመሪያ መንገዱ ሲኖር ነው፡፡
                
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኛማ... በወዲያኛው ዘመን የሆነችና በአለፍ፣ አገደም የምንደግማት ነገር አለች። (በወዲያኛው ዘመን የሚለውን እንደተመቸ ማስላት ነው፡፡) ይህ አንጋፋ ድምጻዊ በቲቪ እየተጠየቀ ነው፡፡ ለተወሰኑ ነገሮች ምላሽ ከሰጠ በኋላ ጋዜጠኛው “ስለ ዓለማቀፍ ሙዚቃ ያለህ አስተያየት ምንድነው?” አይነት ጥያቄ ይጠይቀዋል፡፡ ድምጻዊው ምን ቢል ጥሩ ነው... “ምን ሙዚቃ አለና! ራፕ ብቻ ነው፡፡”
እመኑኝ... “ምን ሙዚቃ አለና! ራፕ ብቻ ነው...” አይነት አስተሳሰብ ለእውቀት ዋጋ እንዳንሰጥ እያደረግን ነው፡፡
ስሙኝማ... አሪፍ ሀሳብ አለችን። አለ አይደል... የጊዜ መባከንን፣ የሰዉን ልፋትን የሚቀንስ አሪፍ ሀሳብ፡፡ በተለይ የወገኖቻችንን የአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ልፋት ለመቀነስ፡፡ ሙሉ አባላቱ በሙሉ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሆኑበት... ‘የሁሉ ነገር የአማካሪዎች ቦርድ’ ነገር የማናቋቁምሳ! አንደኛ ነገር ምን መሰላችሁ፣ በሌላ የውጭ ምንዛሪ የተሸመቱት ካሜራዎች መንገድ ለመንገድ እየተንከራተቱ አቧራ ከመጠጣት ይድናሉዋ! ጋዜጠኞቹም... ዌል እንግዲህ የጋዜጠኞቹን መንከራተትና አለመንከራተትን በተመለከተ በይደር ይቆይማ፡፡ ልክ ነዋ.... ምናልባት የአማካሪው ቦርድ አባላት ከማንም የተሻለ ‘ፈርስት ሀንድ ኢንፎርሜሽን’ ምናምን ነገር ሊኖራቸው ይችላል ብለን ነው፡፡
እኔ የምለው... የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ! በዛ ሰሞን ትረምፕ "እንዳይወድቅባችሁ...” ምናምን ብለው ናላችንን አዙረውን አልነበር! በማግስቱ በእኔ ቤት አራት ኪሎ ላይ ‘ስንጎራደድ’ መሀል ላይ አስቁመህ “ስለ ትረምፕ አስተያየት ምን ታስባለህ?” ያልከኝ የእንትን ቲቪ ጋዜጠኛ፣ ካልጠፋ ሰው ከእሳቸው ጋር ልታገጨኝ የነበርከው... ‘የተነጣጠቅነው’ ነገር አለ እንዴ!  ደግሞ የተቆጡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች “በአዲስ አበባ ነዋሪነት ጭምብል የሚንቀሳቀሱ...” ምናምን ብለው የአቋም መግለጫ ማሟሻ ቢያደርጉኝስ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...የአሜሪካ ሚዲያዎች በዛ ሰሞን በአዲስ አበባ ሚኒባስ ታክሲዎችና በ‘ፉት’ ቤቶች ውስጥ ሰውየው ላይ ይወርድ የነበረውን እርግማን ቢሰሙ ምድረ ‘ሁዋይት ሱፕሬማሲስት’ የዋሽንግተንን ‘ምናምን ስትሪት’ ሀበሻ ሬስቱራንቶችን፣ የእንትን ከተማን ‘ሊትል ኢትዮጵያን’ ባይቀውጡ ነው!
እመኑኝ... “ምን ሙዚቃ አለና! ራፕ ብቻ ነው...” አይነት አስተሳሰብ ለእውቀት ዋጋ እንዳንሰጥ እያደረግን ነው፡፡
እናላችሁ.... ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ’ ነዋሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸው አስተያየቶች ተመሳሳይ እስከሆኑ ድረስ በአማካሪው ቦርድ በአቋም መግለጫ መልክ ማውጣት ይቻላላ! በነገራችን ለይ ንፉግነት በምድሩም፣ በሰማዩም ጥሩ ስለማይሆን...አለ አይደል...የአቋም መግለጫውን ‘ቢቢሲ አማርኛም’ ሌሎቹም ‘የሙያ አጋሮቹም’ (ቂ...ቂ...ቂ...) ከፈለጉ ሊጠቀሙበት ይችላሉ! ‘ቀዶ ጥገናውን’ ግን ለሆስፒታሎች የቀዶ ጥገና ክፍሎች ብቻ ይተዉትማ! ‘የመረጃ ቀዶ ጥገና’ አንድም ቅሽምና ሁለትም ‘ምናምንና’ ይሆናልና፡፡ ሁሉን ተናግረን ሆዳችን ባዶ እንዳይቀር ያህል ነው በ‘ምናምንና’ መልክ’...አለ አይደል...‘ዳሹን ሙሉ’ አይነት ክፍት ቦታ የተውነው፡፡ (ቂ...ቂ...ቂ...)
ስሙኝማ፣ ነገሮች እኮ ‘ወደው አይስቁ’ እየሆኑበን ተቸገርን! ሌላ ሀሳብ አለን......ኮሜዲ ‘የግዳጅ’ና ‘የፍላጎት’ ተብሎ ይከፈልልንማ! “ተመልካቾቻችን፣ ቀጥሎ የሚቀርበው ኮሜዲ የግዳጅ እንደሆነ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በዚህ አጋጣሚም በፈጠራ አክሮባታቸው ወደር የማይገኝላቸውን ‘አስገድደው የሚያስቁን ኮሜዲያንን’ ሳናመሰግን አናልፍም።” አሪፍ አይደል! መፈክርም መጨመር ይቻላል... “ትኩረት የተነፈገው አስገድዶ የማሳቅ የኮሜዲ ዘርፍ ትኩረት እንዲያገኝ በቁርጠኝነት እንሠራለን!” እናላችሁ... ዘጠኝ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ የሆነ ነገር ተጠይቀው አስሩ ተመሳሳይ መልስ ከሰጡ፣ በቃ በቡድን የማይሰባሰቡሳ! ማብራሪያ፡- ከዘጠኝ ወደ አስር ከፍ ያለው አንዳንዴ ጠያቂዎቹ የሙያ ባልደረቦቻችን ራሳቸው ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ’ ስለሚሆኑ ነው።
እመኑኝ... “ምን ሙዚቃ አለና! ራፕ ብቻ ነው...” አይነት አስተሳሰብ ለእውቀት ዋጋ እንዳንሰጥ እያደረግን ነው፡፡
በነገራችን ላይ... ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ...አለ አይደል.. በሚያውቁትም፣ በማያውቁትም፣ ያወቁ በሚመስላቸውም ትንታኔ መስጠታቸው “የዜጎች በጉዳዮች ላይ ጥልቅ ትንታኔ የመስጠት ባህል ምን ያህል እንደዳበረ ማረጋገጫ ነው” የሚል በትንታኔዎች ላይ ትንታኔ እስካሁን ያለመቅረቡ ‘ጥሩ ነገር ማሞገስ’ ብዙ ስለማይመቸን ይሆን አንዴ! 
እንደ ድሮ ሰልፍ ‘ኮምፐለሰሪ’ የሆነችው ‘የሽግግር ቻርተሩን እንደግፋለን’ አይነት እኮ ይቺም ‘ኮምፐለሰሪ’ የሆነች ትመስላለች፡፡ “ለኢትዮጵያ ትክክለኛው መንገድ የእኛ ብቻ ነው” የሚሉዋት ነገር ‘አደብ ገዛች’ ስንል አፈር ምሳ እየተነሳች አስቸገረችንሳ! ለነገሩ መንገድ የብቻም ሆነ የጋራ  የሚሆነው መጀመሪያ መንገዱ ሲኖር ነው፡፡ እናማ... እንዲች አይነት ‘የሽግግር ቻርተሩን እንደግፋለን’ የምትመስል ነገር... አለ አይደል... አሁንም ‘ዶስ’ ነው ምን የሚሉትን ‘ኦፕሬቲንግ ሲስተም’ እንደመጠቀም ነው፡፡ (የመፈላሰፍ መብታችን ይጠበቅልንማ!)
እመኑኝ... “ምን ሙዚቃ አለና! ራፕ ብቻ ነው...” አይነት አስተሳሰብ ለእውቀት ዋጋ እንዳንሰጥ እያደረግን ነው፡፡
እናማ... ምን ለማለት ነው...ከፍተኛ የሆነ የእውቀት እጥረት የገጠመን ሙያና ባለሙያ አልገናኝ ብሎ ነው፡፡ (እርፍ!)
“የህክምና ዶክተር ነው፣”
“የምናምን ዘርፍ ፕሮፌሰር ነች፣” እንላለን፡፡ ልጄ በየ‘የሎው’ ቤቱ ስንቶቻችን ‘ጥይት’ ሁሉን አዋቂዎች-- እንዳለን ቢታወቅ ‘ናሽናል ዳያሎግ’ በተዘጋጀ ነበር፡፡ (ፈረንጅኛ በዛ ልበል!)  
“ስማ ዛሬ ሆስፒታል ሄጄ ነበር፡፡”
“ምን ሆነህ?”
“በቃ ሰሞኑን ሆዴ እየተረበሸብኝ ሥራ መሥራት እንኳን ሲያቅተኝ እንትን ከፍተኛ ክሊኒክ ሄድኩ፡፡””
“እና... ዶክተሩ ምን አለህ?”
“የጨጓራ ባክቴሪያ ነው አለኝ፡፡”
“እነሱ ደግሞ ያለጨጓራ ባክቴሪያና ያለ ታይፎይድ አያውቁም እንዴ!”
“ምን ነካህ....ቢያንስ እኔን ያየኝ የታወቀ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቲ ነው፡፡”
“እና ዳበስ፣ ዳበስ  አደረገህና ጨጓራ ነው አለህ...”
“እንደሱ አይደለም፡፡ ቢያንስ አምስት አይነት ምርመራ ነው ያደረጉልኛ፡፡ ላቦራቶሪያቸው ደግሞ ምርጥ ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡”
“ገንዘብ ለመብላት ነዋ! ስማ ሞኞ፣ እዚህ ሀገር የህክምና ስፔሻሊስት ብሎ ነገር የለም። ሁሉም የቢዝነስ ስፔሻሊስት ነው፡፡”
“ተው እንጂ፣ እንዲህ ዓይነት ነገር ካንተ አልጠበቅም፡፡”
“እኛ ሁሉንም እናውቀዋለን አልኩህ እኮ። ስማ... እንደውም የእኔ አክስት እንዲሁ ዓይኖችህንና ጥፍርህን ብቻ በማየት አይደለም ጨጓራ፣ ኩላሊት ምናምን ምን አይነት ካንሰር እንዳለብህ ሁሉ ልትነግረህ ትችላለች፡፡  
“አትለኝም!”
“ይህን እኮ ነው የምልህ፡፡ እኛ የምናውቀውን እንደማማከር ደም፣ ሽንት ቅብጥርስዮ እያላችሁ ገንዘባችሁን ትከሰክሳላችሁ፡፡”
እመኑኝ... “ምን ሙዚቃ አለና! ራፕ ብቻ ነው...” አይነት አስተሳሰብ ለእውቀት ዋጋ እንዳንሰጥ እያደረግን ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1757 times