Monday, 30 November 2020 00:00

የሽብር ጥቃት ባለፉት 5 ዓመታት በ60 በመቶ ቀንሷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አምና 14 ሺህ ያህል ሰዎች በሽብር ለሞት ተዳርገዋል

             በአለማችን የሚከሰቱ የሽብርተኝነት ድርጊቶች እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ በነበሩት አመታት በ59 በመቶ ያህል መቀነሱን ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው የ2020 አለማቀፍ የሽብርተኝነት ሁኔታ አመላካች ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
የአለማችን ሽብርተኝነት ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ15 በመቶ ያህል መቀነሱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ለሽብርተኝነት መቀነስ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የአሸባሪው ቡድን አይሲስ መዳከምና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ግጭቶችና ውጥረቶች መቀነሳቸው እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡
በመላው አለም በየአመቱ በሽብር ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ለአምስተኛ ተከታታይ አመት መቀነስ ማሳየቱንና በ2019 የፈረንጆች አመት በመላው አለም 13 ሺህ 800 ያህል ሰዎች ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ለሞት መዳረጋቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ሽብርተኝነት በአመቱ በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው ጥፋት 16.4 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሚደርስም ገልጧል፡፡ በአመቱ በ63 የአለማችን አገራት ቢያንስ አንድ ሰው፣ በ17 አገራት ደግሞ ቢያንስ አንድ መቶ ሰዎች በሽብር ጥቃት መገደላቸውን ያስታወሰው ተቋሙ፤ ናይጀሪያና አፍጋኒስታን በአመቱ በርካታ ሰዎች በሽብር ጥቃት ለሞት የተዳረጉባቸው ቀዳሚዎቹ ሁለት የአለማችን አገራት መሆናቸውንና በእያንዳንዳቸው ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውንም አስረድቷል፡፡
በ2019 የፈረንጆች አመት ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ቀዳሚዎቹ አስር የአለማችን አገራት፡- አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ናይጀሪያ፣ ሶርያ፣ ሶማሊያ፣ የመን፣ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ፊሊፒንስ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
በተቋሙ የ2019 ሪፖርት መሰረት በሽብር ጥቃቶች፣ የሞትና የመቁሰል አደጋዎችና የሀብት ውድመት መጠኖች አንጻር ሲታይ፣ 103 የአለማችን አገራት ደረጃቸውን በ2018 ከነበረበት ያሻሻሉ ሲሆን 35 አገራት በአንጻሩ ከነበሩበት ዝቅ ማለታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሽብርተኛው ቡድን አይሲስ በአመቱ በ27 አገራት ለተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች ሃላፊነት መውሰዱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ቡድኑ ወደ አፍሪካ አገራት መስፋፋቱንና በአገራቱ ለሞት የዳረጋቸው ሰዎች ቁጥር በ67 በመቶ ያህል ማደጉንም ጠቁሟል፡፡

Read 2843 times