Sunday, 29 November 2020 15:52

በአለማችን ታሪክ እንደ ኮሮና በፍጥነት ክትባት የተገኘለት በሽታ የለም ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ክትባቱ ከ4 ዶላር እስከ 50 ዶላር ዋጋ ተቆርጦለታል

              በመላው አለም ከ57 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያጠቃውና ከ1.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ለሞት የዳረገው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፤ በአለማችን የህክምና ምርምር ታሪክ በአጭር ጊዜ ወይም በከፍተኛ ፍጥነት ክትባት የተገኘለት የመጀመሪያው በሽታ መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከሰሞኑ አስታውቀዋል፡፡
ለመንፈቅ ያህል አለምን ጭንቅ ውስጥ ከትቶ ለዘለቀው የኮሮና ቫይረስ በሽታ ክትባትና መድሃኒት ለማግኘት ሌት ተቀን ደፋ ቀና ሲሉ የከረሙ የተለያዩ የአለማችን አገራት የምርምር ተቋማትና ኩባንያዎች ከሰሞኑ እጅግ ውጤታማ የሆኑ ክትባቶችን እንዳገኙ ይፋ ማድረግ መጀመራቸውን ተከትሎ፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ ባለፈው ማክሰኞ በጄኔቫ ባደረጉት ንግግር፣ በታሪክ በዚህ ፍጥነት ክትባት ተገኝቶ እንደማያውቅ በመግለጽ፣ አለም ለዚህ ገዳይ ወረርሽኝ መፍትሄ የሚሆኑ ክትባቶችን ያገኘችበት የተጨባጭ ተስፋ ጊዜ ላይ መድረሷን ተናግረዋል፡፡
ለኮሮና ቫይረስ በዚህ ፍጥነት ክትባት ለማግኘት የተቻለው የምርምር ተቋማትና የሳይንሱ ማህበረሰብ በክትባት ምርምር ላይ አዳዲስ አሰራሮችንና መስፈርቶችን አውጥተው በመስራታቸው እንደሆነ የጠቆሙት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ ክትባቶችን በአፋጣኝ ለማግኘት የተደረገው ርብርብ በቀጣይም ክትባቶችን በፍጥነትና በፍትሃዊነት በማዳረስ ረገድም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችና ለድሃ አገራት በፍትሃዊነት የማዳረስ ጉዳይ ቀጣዩ ፈተና እንደሆነና ያደጉ ሃብታም አገራት ክትባቶችን ቀድመው ለመግዛትና ዜጎቻቸውን ለመታደግ እሽቅድምድም መጀመራቸውና ከመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋር ስምምነት በመፈጸም ላይ እንደሚገኙ እየተዘገበ ይገኛል፡፡
አሜሪካ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ለዜጎቿ መስጠት እንደምትጀምር የአገሪቱ የጤና ባለስልጣናት ከሰሞኑ ያስታወቁ ሲሆን፣ የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የጂ 20 አገራት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ የአለማችን አገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ላያገኙ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው በይፋ መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
ከሰሞኑ እጅግ ውጤታማ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ማግኘታቸውን ይፋ ካደረጉት የተለያዩ አገራት ኩባንያዎችና የምርምር ተቋማት መካከል የአሜሪካው ፋይዘር እና የጀርመኑ ባዮቴክ፣ የቤልጂየሙ ጃንሰን እና አስትራዜኒካ ይገኙበታል፡፡ፋይዘር አንድ ክትባት በ20 ዶላር፣ ሞዴርና ከ10 እስከ 50 ዶላር፣ አስትራዜኒካ ከ4 ዶላር በታች ለመሸጥ ዋጋ መቁረጣቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡


Read 1867 times