Sunday, 29 November 2020 15:23

ሂትለርና ጆሴፍ ጎብልስ በመጨረሻ ተዋርደዋል! (ጽንፈኛው ህወሓትስ?)

Written by  ከወንድወሰን ተሾመ መኩሪያ (የማህበራዊ ሳይንስና የስነልቦና ባለሙያ)
Rate this item
(1 Vote)

 "በወጣትነታቸው ወደ ጫካ የገቡት የህወሓት ጁንታዎች፤ የዚህ የሰብእና ብልሹነት ሰለባ እንደሆኑ ከድርጊታቸውና ከንግግራቸው መገንዘብ አያዳግትም፡፡ በሳይኮፓቲ፤ በናርሲስዝምና በማካቬሊያኒዝም የተመታው ቡድን ሞራል የለሽ፣ ጨካኝ፤ ትዕቢተኛና ጭፍን ጥላቻ አራማጅ ይሁን እንጂ ማሰብ የማይችል ደደብ አይደለም፡፡--"
            
             የናዚ ፕሮፓጋንዳ አለቃ የነበረው ጆሴፍ ጎብልስ፣ የጀርመኖችን አመለካከትና አስተሳሰብ ለመቅረፅና የናዚን ርዕዮተ ዓለም ለማስረፅ የፓርቲው ልሳን የሆኑትን መፅሄቶች፣ ጋዜጦችና ማናኛቸውንም ሃብቶች ይጠቀም ነበር፡፡ ለጆሴፍ ጎብልስ ውሸት ትልቁ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያው ነው፡፡ ይህ በውሸት ላይ የተመሰረተው የስነልቦና ቀረፃ በፖለቲካ ጉዳዮች ብቻ የተወሰነ አልነበረም፤ ሙዚቃውን፤ የልጆች አስተዳደጉን፤ ስፖርቱን፤ ስነፅሑፉን ወዘተ የናዚዎች አስተሳሰብን በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ ተጠቅሞቦታል፡፡ የናዚ ፓርቲ መንግስት በሆነበት ጊዜ እነዚህንና ሌሎች የዜጎች እንቅስቃሴዎችን የፕሮፓጋንዳው ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
ፅንፈኛው የህወኃት ቡድን በፈጠረው ፕሮፓጋንዳ በትልቅ ማሳ ውስጥ (ኢትዮጵያ) ትንንሽ ማሳዎችን (በቋንቋ የተዋቀሩ ክልሎች) ለራሳቸው የሚያጥሩ ጎሳዎችን በመፍጠር በድንበር እንዲጋጩ አድርጓል፤ ዜጎች በተወለዱበት አካባቢ “ከዚያኛው ወገን ነህ” ተብለው ለፖለቲካ ሥልጣን እንዳይወዳደሩ ገድቧል፤ ዜጎች በገዛ አገራቸው “ነዋሪና መጤ” ተባብለው እንዲኖሩ መንገድ ቀድዷል፤ የሁለት ሰዎችን ጠብ የሁለት ብሔሮች ጠብ አድርገን እንድናስብ ተቀርፀናል፤ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲይና እንዳይተማመን ተሰርቶብናል፡፡
የጀርመን ፕሮፓጋንዲስት ጆሴፍ ጎብልስ፤ “ሸክላ” የሆነን ሰው (ተሰባሪውን ሰው) superman እያለ ከሌላው ዘር ብልጫ ያለው ሰው አድርጎ እንደሳለው ሁሉ፣ ህወሓት “አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ” በመፍጠር “ትንሽና ትልቅ” እንድንሆን፤ መብትና ነፃነት “የሚገባንና የማይገባን” (“ባ” ይጠብቃል) አድርጎናል፡፡  በኢትዮጵያ መሬት ውስጥ የብሔር መሬት ፈጥሯል፡፡ ዜጎች በትንንሽ መንደሮች እንዲገደቡና ከመንደራቸው ውጪ እንደ ልብ ተወዳድረው ስራ እንዳያገኙ ግንብ ሰርቷል፤ ለኔ ጎሳ “ብዙ የሥራ እድል”፤ ለአንተ ጎሳ ግን “ትንሽ የስራ እድል” ይበቃሃል የሚሉ የመንግስት ባለስልጣናትን ፈጥሯል (40፤40፡20)፤ አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ እንዲያቄምና የጠላትነት ስሜት እንዲኖረው በስነፅሁፍ ዘምቷል፤ ሃውልት አሰርቷል፡፡ በልህቀት ሳይሆን በእውቂያና በመንደር ልጅነት ሥልጣንንና ሥራን አከፋፍሎ፣ አገሪቷን ከድህነት የማትወጣ የሌቦችና የቀማኞች አገር አድርጓታል፡፡
ሂትለርና ግብረ አበሮቹ በተለያዩ መንገዶች ስድስት ሚሊየን አይሁዳውያንን ጨምሮ 50 ሚሊየን ህዝብ ህይወቱን እንዲያጣ አድርገዋል፡፡ ከሂትለርና ከጆሴፍ ጎብልስ ፊት ለፊት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነበር፤ ትዕቢታቸውና ቅጥ ያጣ አምባገነንነታቸው እስከ ወዲያኛው ላይኖር እነሱም ሊጠፉ ቁርጥ ቀን እየቀረባቸው መሆኑን አይረዱም ነበር፡፡ ለካስ ጊዜ ይጨልማል፤ ለካስ ሄዶ ሄዶ ሰው ብቻውን ይቀራል፤ እንዲሁ ሆኑ፤ ራሳቸውንና አጠገባቸው ያሉትን የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን በገዛ እጃቸው አጠፉ! የኛዎቹስ--?
ፀረ ማህበራዊ  ጠባይ (Anti-social behavior) ከመጠን ባለፈ መልኩ ሌሎችን መናቅና የሌሎችን መብት መጣስ በአብዛኛው ከ15 ዓመት ጀምሮ የሚከሰት ነው፡፡ በወጣትነታቸው ወደ ጫካ የገቡት የህወሓት ጁንታዎች፤ የዚህ የሰብእና ብልሹነት ሰለባ እንደሆኑ ከድርጊታቸውና ከንግግራቸው መገንዘብ አያዳግትም፡፡ በሳይኮፓቲ፤ በናርሲስዝምና በማካቬሊያኒዝም የተመታው ቡድን ሞራል የለሽ፣ ጨካኝ፤ ትዕቢተኛና ጭፍን ጥላቻ አራማጅ ይሁን እንጂ ማሰብ የማይችል ደደብ አይደለም፡፡ በማሰብ ችሎታው ( IQ) ከመካከለኛ ውጤት በላይ የሚያስመዘግብ ነው፡፡ ይህ በወጣትነት የጀመረ የሰብዕና ውልግድና እስከ እርጅና እንደሚዘልቅ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የሌሎችን መብት ይጥሳሉ፤ ተደጋጋሚ ውሸት ይዋሻሉ፤ የሃሰት ስም ይጠቀማሉ፡፡  ለገንዘብ፤ ለወሲብና ለስልጣን ሲሉ የማይከፍሉት ዋጋ የለም፡፡ ርህራሄ የላቸውም፤ ሌላውን ዝቅ አድርጎ ማየት ልማዳቸው ነው፤ “ከኔ በላይ ላሳር!” ይላሉ። ከሌላው ወገን ጋር ያላቸው  የእርስ በእርስ ግንኙነት ለይስሙላ ነው፤ ጥልቅ ግንኙነት አይፈጥሩም፤ በጥቅሉ ጓደኛ አያውቁም። ለጓደኛና ለማያውቁት ሰው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብ አባላት ጭምር ደንታ የላቸውም፡፡
እውነተኛ አዋቂ “ብዙ ባወቅሁ ቁጥር አለማወቄን እገነዘባለሁ” ይላል፡፡ የሦስቱ ስነልቦናዊ ቀውሶች ሰለባዎች ግን ምንም ሳያውቁ “አዋቂ ነን” ይላሉ፡፡ ስለዚህም ሳይማሩት የማስተርስና ፒ.ኤች.ዲ. ባለቤት ይሆናሉ፡፡ ቻርልስ ዳርዊን “አለማወቅ ከእውቀት የበለጠ ደፋር ነው” ይላል፤ ደፋሮች ሆኑ! በድፍረታቸው ምክንያት ያደረጓቸውን ክፉ ነገሮች  ወደፊት ጊዜ ሲገልጣቸው የምንሰማው ይሆናል፡፡
በናርሲስዝም የተጠቁ ሰዎች በሌሎች ላይ ከፍተኛ ቅናት አለባቸው፤ “ሌላ ሰውም በእኛ ላይ ይቀናል” ብለው ያምናሉ፤ ተንኮለኝነት የተጠናወታቸው ናቸው፤ ስሜት አልባ ናቸው (አዝነው አይምሩህም)፤ አታላይነት መገለጫቸው ነው፤ ጠበኞችም ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ፍላጎታቸው ላይ የተመሰረተ ግብ ያስቀምጣሉ፤ ግባቸውን ለማሳካት ህጋዊም ሆነ ህገ ወጥ መንገድን ምንም ሳያቅማሙ ይጠቀማሉ፡፡
ምን እናድርግ? በዜጎቻችን አዕምሮ ላይ የተሰራው አሉታዊ አስተሳሰብ እስኪጠራ ድረስ ጊዜ መውሰዱ አይቀሬ ነው፡፡ እንዲሁ በጊዜ ብዛት የሚጠፋም አይደለም፤ ሥራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ የፖለቲካና ማህበራዊ አስተሳሰቦቹን ከአገራችን ነባር እሴቶች ነጥሎ ለማስነወር ሁሉም በየአቅጣጫው መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ከአገሪቱ ህገ መንግስት ጀምሮ ፖሊሲዎች ሊቀየሩ፤ የተለያዩ ህጎች ሊሻሻሉ፤ አዳዲስ ስልቶች ሊነደፉ ይገባል። አዎንታዊ እሴቶች እንዲዳብሩ፤ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲያንሰራራ፤ አገራዊ እይታ እንዲጎለብት፤ እኩልነትና ነፃነት ለሁሉም ዜጎች እንዲሆን መንግስት፣ ኪነ ጥበቡ፤ ሚዲያው፣ ምሁራንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሌት ተቀን ሊሰሩ ይገባል፡፡
“እኛ የተለየን ነን”፤ “እኛ ከሌላው ብልጫ አለን”፤ The Arayans በሚል ሌላውን የሚንቅ የዘረኝነት አስተሳሰብ አራማጅ የነበሩት የናዚ ፓርቲ መሪዎች፣ በውርደትና በአሳፋሪ ሁኔታ ታሪካቸው ተደምድሞ ዓለም ተገላግሏቸዋል፡፡ የእኛስ super men መጨረሻቸው ምን ይመስል ይሆን?  
ድል ለኢትዮጵያ! ድል ለኢትዮጵያውያን!
ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ ውስጥ የተንጸባረቀው ሃሳብ የሚወክለው የጸሃፊውን ብቻ እንደሆነ  እንገልጻለን፡፡ ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 10585 times