Sunday, 29 November 2020 15:10

“እንዴት ያገሳ ይሆን የተባለው በሬ እምቧ ይላል”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 አንዲት ሴት አንድ አረብ ውሽማ ኖሯታል። ባሏ ለገበያ ራቅ ወዳለ ቦታ በሄደ ቁጥር ልጇን ወደ ዐረቡ ውሽማዋ ትልክና ታስጠራዋለች። ዐረቡም ትንሹ ልጅ ላደረገው የመላለክ “መልካም ተግባር” “በዚሁ ቀጥል” ለማለትና ለማባበያ፣ ብስኩትም እንደ ጉርሻ ይሰጠውና ወደ ቤት ይመጣና።……ከእናትየው ጋር ሲደሰት ይውላል፡፡ አንድ ቀን ባልየው የሄደበት ገበያ አልቀናው ብሎ በጊዜ ይመለሳል፡፡ ዐረቡ ከሚስቱ ጋር ቁጭ እንዳለ የውጪው በር ይንኳኳል። ቤቱ ሳሎኑና ጓዳው የሚተያይ  በጣም ጠባብ በመሆኑ ዐረቡ የት እንደሚደበቅ ግራ ሲገባው፣ መቼም ከሴት መላ አይጠፋምና አንድ ኩምጣ ከረጢት እህል አውጥታ “በል ወፍጮውን ያዝና የምትፈጭ ምሰል” ብላ ብልሃት ትፈጥራለች። ባልየው “አንዴት ዋላችሁ። ገበያው የማይሆን ሲመስለኝ ጊዜ ፈጥኜ ተመለስኩኝ” አላት።
ሚስቲቱም “ደግ አደረግህ። እኔም ሩቅ ቦታ እየሄድክ ስታድር ናፍቆቱ እየበረታብኝ ጭንቅ፣ ጥብብ ሲለኝ ነበር የከረምኩት። ባለፈው ያመጣኸውን አንድ ቁምጣ ስንዴ ይህን አረብ ፍጭ ብየው ይሄው እያስፈጨሁት ነው።”
ወደ አረቡ ዞር ብላ፤ “እኮ ቶሎ በል? ገንዘቤን እኮ ነው የምከፍልህ!”  ዐረቡ ማስመሰል አለበትና ላቡ እስኪንጠፈጠፍ መፍጨቱን ቀጠለ። ባልየው ሚስቱ ባደረገችው በመደሰትና የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ በማሰብ ዐረቡ አጠገብ ወገቡን ይዞ ቆመ፤  “በል ፈጠን ብለህ ጀምበር ሳታዘቀዝቅ ጨርስ” እያለ በቁምጣው ከረጢት ያለውን ስንዴ በሙሉ አስፈጨና ገንዘብ ከፍሎ አሰናበተው። ዐረቡ ላቡን እየጠረገ ሄደ።
ባል ገበያው አይሞቅም እያለ ሁለት ሳምንት ሙሉ እቤት ከርሞ- በመጨረሻ ወደ ሩቅ ከተማ ሄደ። ሴትዮዋ በጥድፊያ ልጇን “ሂድና  አረቡን ጥራው ”ብላ ላከችው።
“አሃ! ባለፈው የፈጨሁት ስንዴ አለቀ! አውቄብሻለሁ በላት። ላንተም ከረሜላ የለም። የሷን ዱቄትም የምፈጭበት አቅም የለም። ሁለተኛ አልሞኝም።”  
*   *   *
በሁለት ቢላዋ መብላት ሁልጊዜ አያዋጣም። በጉርሻ ማታለልም ሁልጊዜ አያበላም። ጨለማ ለብሶ በህገ-ወጥ መንገድ የተለየ ጥቅም ማግኘትም ሁልጊዜ አይሳካም። አንድ ቀን ሁለቱም ቢላ ይደንዛል። እንኳን ቢላው፣ ሞረዱም ሟልጦ ሟልጦ አልሞርድም ይላል። ከረሜላውም ያልቃል። ህገ-ወጡም መንገድ ይነቃል። ያኔ ጭንቅ ይመጣል።
የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለያየ ወቅት አንዴ በፖለቲካው ሳቢያ፣ ሌላ ጊዜ በኢኮኖሚ ሳቢያ፣ አንዴ በህጋዊ መንገድ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በህገ-ወጥ መንገድ ተጽዕኖ ሲደረግበት፣ ሲታገልና ሲበዘበዝ ብዙ እንግልት ሲደርስበት የኖረ ህዝብ ነው። ፖለቲካው ሲደንዝ በኢኮኖሚው፣ ኢኮኖሚው ሲደንዝ በፖለቲካው ሲገፋና ሲገፈፍ የከረመ ህዝብ ነው።
ሁኔታው ሁሉ ገብቶት በንስር ዐይን ያያት  እለት፣ ዐይንህን ተጨፈን ሲባል፣ እንደ እርግብ ልቡን ንፁህ አድርጎ ሁሉን ለእግዜር ሰጥቶ ሲተኛ “ንቃ ታገል” ሲባልና የተኛ ይመስል ሲቀስቀስ፣ በየገፁ ሲጉላላ ብዙ አበሳ የተፈራረቀበት ህዝብ ነው።
አዳዲስ ርዕዮተ-ዓለም፣ አዳዲስ መመሪያ፣ አዳዲስ  ህግጋት በተነደፉ ቁጥርና አዳዲስ አለቆች በተሾሙ ቁጥር “አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ” እንዲሉ፣ፖለቲከኛውም፣ መመሪያ አውጪውም፣ ህግ-አስፈጻሚውም በየፊናው በዚህ ውጣ በዚህ ውረድ ይለዋል።
“አንዴ መብራት ኃይል ለምሰሶ ይቆፍራል፣ እንዴ ቴሌ ለስልክ ይቆፍራል። አንዱ የቆፈረውን ሌላው ይደፍናል። ህዝብ ግራ-መጋባቱን ይቀጥላል እንደተባለው ነው።
ትላንት የተሞካሸው ዛሬ ይወገዛል። ትላንት ጌታ የነበረው ዛሬ ክቡር-እምክቡራን ይባላል። ባልታወቀ ምክንያት የወጣው፣ ባልታወቀ ምክንያት ይወድቃል። ሾላ-በድፍን ቅዱስ የተባለው፣ ሾላ -በድፍንእርኩስ ተብሎ ይቀራል “ብራ ይውላል” ሲሉት እሰየው” “አይዘንብም” ሲሉት “እሰየው አበጀ!” እያለ ይቀጥላል። ደመራው በመጨረሻ ወዴት ይወድቃልን እንጂ መጀመሪያ እንዴት ተደመረ? እንዴትስ ነደደ? ማ ቀደሰ-ማ አለቀስ? አይልም።
ህብረተሰቡ፣ ከዛሬ ነገ ያልፍልኛል ከሚል የህልም ንፍቀ-ክበብ አይወጣም። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለችው ደሀ አገር፣ ህዝብ ዕለት ጉሮሮውን ለመዝጋት ደፋ-ቀና ከማለት የተለየ የህይወት ምርጫ የለውም። የኑሮ ለውጥ የሌለው ህዝብ ደሞ ሞራሉ ይላሽቃል። ሐሞቱ ውሃ ይሆናል። ንቃቱም ይጃጃላል።
“ሞኝ በጥፊ ሊመቱት ሲሰነዝሩ፣ ሊያጎርሱኝ ነው ብሎ አፉን ይከፍታል” እንዲል መጽሐፍ፣ ሁሉ ለእኔ  ጥቅም የተደረገ ይሆን ይሆናል ከማለት ወደኋላ አይልም። ነገር  የሚገባው፣ ከመሸ ነው። “እባብ ያየ በልጥ በረየ” ነውና አንዴ የተዘጋው በር፣ መቼም እሚከፈት ባይመስለው አይፈረድበትም።  አለማወቁን፣ በምን ቸገረኝ ሊያልፈውም ይገደዳል። ለዚህም አንዱና ዋነኛው ችግሩ ተገቢውን ኢንፎርሜሽን በተገቢው ሰዓትና ቦታ አለማግኘት ነው። መንገድ ሲዘጋ በወቅቱ አያውቅም፤ መንገድ ሲቆፈር በወቅቱ አያውቅም። መንገዱም አላሳልፍ ሲለው፣ የትራፊክ መብራቱም ሲያስቆመው፣ ዋጋውንም መክፈል ሲቸግረው ነው ሁሉንም የሚገነዘበው። ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ አልታደለም።…
የዘልማድ ያህል የመጣውን እየተቀበለ፣ ለወደቀው ማንም ይሁን ማን ያዝናል። ብልም የሚያደምጠኝ  ሰሚ ጆሮ የለም ወደ ሚለው ያዘነብላል። መንገድ፣ ቀይ-ምንጣፍም ይኑረው ኩርንችት እሾክ፣ እኔ መንገድ አይደለሁም ብሎ ለወጪ -ወራጁ ይተወዋል። Indifference is the order of the day እንደተባለ ሁሉ። ያም ሆኖ በዚህም አይፈረድበትም። የጎመራ ሲበሰብስ፣ የፈላ ሲፈስ ሲያይ ነው የኖረው። ድርጅት ሆነ ፓርቲ፣ ቡድን ሆነ ግለሰብ፣ በዚሁ ቦይ ውስጥ ሲፈስ ነው ያስተዋለው። ሁሉን እንደተፈጥሮ ሂደትና ክስተት ማየት ከጀመረ ሰንብቷል። በአገሩ ጉዳይ ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነት ፣ከዚያ ወደ ባለቤትነት የማደጊያው መንገድ፣ ገና ብዙ የዲሞክራሲ ጥያቄ፣ ገና ብዙ የፍትሐዊነት  ጥያቄ ተመልሶ፣ ገና ብዙ የሙስናና የፖለቲካ አውጫጭኝ ደርሷል? የኢኮኖሚ ድቀት የት ወርዷል፣ ማሕበራዊው ንቅዘት ምን ያህል ከፍቷል።  የተጀመረው ሁሉ የት ተቀጨ፣ የተጨረሰው ለማን በጀ? የሚለውን በግልጽ የሚነግረው ይሻል።
ያለ ማህበረሰቡ ተሳትፎ እድገት ማምጣት ዘበት ነው።  “ህዝብ አወቀ አላወቀ ምን ያገባውና?” በማለት መገለል የለበትም። ማህበረሰቡ በአካል -በመንፈስ የአገሩ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ መሆን ይገባዋል።
አለበለዚያ ስንት የተወራለት ዲሞክራሲ፣ ስንት የተነገረለት ልማት፣ ብዙ የተሞገሰው የእድገት ጎዳና በወሬ ይቀራል።”እንዴት ያገሳ ይሆን የተባለው በሬ፣ እምቧ ይላል” እንደተባለው የወላይተኛ ተረት መሆኑ ነው።

Read 13051 times