Sunday, 29 November 2020 14:55

ግማሽ ሚሊዮን የመቀሌ ነዋሪዎች ለችግር ተጋልጠዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 · 700 ሺ ሰዎች የአንድ ወር እርዳታ አላገኙም

             በትግራይ ክልል የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችን ጨምሮ በአጠቃላይ 700 ሺህ  ያህል የሴፍቲኔት   ተረጂዎች የህዳር ወር እርዳታ እንዳልደረሳቸው ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤በመቀሌ ግማሽ ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች በመሰረታዊ ሸቀጦች  እጥረት ተቸግረዋል ብሏል፡፡
በትግራይ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ በተመለከተ ተቋሙ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፤ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል አስተዳደር (ህወኃት) መካከል በተፈጠረው ጦርነት 41 ሺህ ዜጎች ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ 18 ሺህ ያህሉ ታዳጊ ህፃናት መሆናቸውን ነው ያስታወቀው፡፡
ቀደም ሲል በክልሉ በየወሩ  የምግብ እርዳታ ይቀበሉ የነበሩ 600 ሺህ የክልሉ ነዋሪዎችን ጨምሮ 96 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች፣ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁንና የህዳር ወር እርዳታም እንዳልደረሳቸው ነው ተቋሙ ሪፖርት ያደረገው፡፡
በየወሩ ከተለያዩ በውጭ ከሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው በሚያገኙት ድጎማ ይተዳደሩ የነበሩ ከ250 ሺህ በላይ ዜጎች የባንክ አገልግሎት መስተጓጎሉን ተከትሎ መቸገራቸውን ሪፖርቱ  አትቷል፡፡
በመቶ ሺህ የሚገመቱት የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጨምሮ 2 መቶ ያህል የረድኤት ሰራተኞች አሁን በመቀሌ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ በጭንቅ ውስጥ ከመሆናቸው ባለፈ የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት በመፈጠሩ ለችግር መዳረጋቸውንም ሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በህወኃት ስር በምትገኘው መቀሌ፤ የነዳጅ፣የጥሬ ገንዘብ፣ የምግብና የውሃ እጥረት በከፋ ደረጃ መጋለጡን ሪፖርቱ አትቷል፡፡
ጦርነቱን ሽሽት ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎች ቁጥር ከ41 ሺህ በላይ መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ከእነዚሁ ውስጥ 18 ሺህ ያህሉ ታዳጊ ህጻናት ደግሞ የተሰደዱት ከወላጆቻቸው ጋር ሳይሆን ብቻቸውን መሆኑን ሪፖርቱ አትቷል፡፡ ከእነዚሁ ስደተኞች መካከል 195 ሴቶች ነፍሰ ጡር መሆናቸው ነው የተመለከተው፡፡ 184 የሚሆኑት ህፃናት አስቸኳይ አልሚ ምግብ የሚያስፈልጋቸው መሆኑንም ተመልክቷል።
በአጠቃላይ በዚህ ጦርነት ምክንያት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጦርነቱ በሚፈጥራቸው ጫናዎች በትግራይ አማራና አፋር ክልል  ተጨማሪ 1.1 ሚሊዮን ዜጎች ለተረጂነት ይዳረጋሉ ያለው ሪፖርቱ፤ 79.6 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያስፈልጋል ብሏል ችግሩን ለመቋቋም፡፡

Read 11230 times