Print this page
Sunday, 22 November 2020 00:00

ችግሩን ከስሩ ለመንቀል፣ መዋቅራዊ ምንጩን ማድረቅ

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(1 Vote)

  በምህዳራዊ አስተሳሰብ መሰረት፣ በልዩ ልዩ መልኩ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች በተፈጥሮአዊው ምህዳር ውስጥ ያሉ ከመጠን ያለፉ ከባቢያዊ መዛባቶችን ለማስተካከል የሚከሰቱ ተፈጥሮአዊ ሁነቶች ናቸው። ዛሬ በዓለም ዙሪያ በተጠናከረ ሁኔታ እየተክሰተ ያለው ድርቅ፣ ጎርፍ፣ አውሎ ነፋስ (tornedo) እና የባህር ማእበል (hurricane)  ሁሉ ተፈጥሮአዊው ምህዳር የሚደርስበትን ከባቢያዊ መዛባት ለማስተካከል ያሉትን ሂደቶች የሚያመላክቱ ናቸው።  በተመሳሳይ መልኩ፣ ግጭቶችና ጦርነቶች ባንድ ማህበረሰብ ውስጥ ወይም በሀገሮች መካከል ያሉ እና ጥልቅ የሆኑ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቅራኔዎች መገለጫ ናቸው። አብዛኛዎቹን ከባቢያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ቀውሶች፣ በዕውቀትና አስተውሎት ላይ በተመረኮዙ አስተሳሰቦችና አካሄዶች የተፈጠሩ መዛባቶችንና ግጭቶችን በመፍታትና ሚዛናዊ የሆነ አካሄድን በመከተል ወደ ከፋ ጉዳት እንዳያመሩ ማድረግ ይቻላል። ወደ ሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ስንመጣ፣ ለእንዲህ አይነቱ ጤናማ አካሄድ ከትግራይ ክልል መሪዎች በኩል የነበረው ዝግጁነት አናሳ በመሆኑ ዛሬ ለተከሰተው አሳዛኝ ጦርነት ተዳርገናል። አንዳንድ ፖለቲከኞችና ተንታኞች ይህ ጦርነት ህወሓትን በመደምሰስ በኢትዮጵያ ያለውን መሰረታዊ የፖለቲካ ችግር ከስሩ ለመንቀል መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል። በእርግጥም፣ እንዲህ ዓይነት ጦርነቶችና ግጭቶች ወደፊት አላራምድ ያሉ ሁኔታዎችን  በመለወጥ ረገድ የራሳቸውን ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይታመናል። ይህ ሊሳካ የሚችለው ግን፣ ጦርነቱ የሚፈጥረው አጋጣሚ ለምህዳሩ ጤናማነት አስቸጋሪ የሆኑ በጥባጮችን (rogue elements) ከማስወገድ ባሻገር ለእንዲህ አይነት በጥባጮች መፈጠር ምንጭ የሆኑትን መዋቅራዊ ሁኔታዎች መፍታት ሲችል ነው። ይህ ደግሞ፣ ከወታደራዊ ዘመቻው ጎን ለጎን፣ የሰከነ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መፍትሄዎችንም ማፈላለግ ይጠይቃል። እንዲህ አይነት ሁሉን አቀፍ የመፍትሄ አቅጣጫን መከተል ወታደራዊ መፍትሄው የሚጠይቀውን መስዋእትነት ከመቀነሱም በላይ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ችግር የሚፈጠርበትንም ሁኔታ ይቀንሰዋል። ይህ ጽሁፍ፣ ይህንን ለማድረግ የሚያስፈልጉንን የአመለካከት ለውጦችና ሊተኮርባቸው የሚገቡ አበይት መዋቅራዊ ጉዳዮችን ይጠቁማል።
በአሁኑ ወቅት፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ አጋጥሟት የማያውቅ እጅግ ፈታኝ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የሚከፈለው መስዋእትነት ትርጉም የሚኖረው ለዘመናት ተጣብቶን የኖረውን የፖለቲካ ምስቅልቅል ከምንጩ ለማድረቅ ወደሚያስችል ዕድል መቀየር ከቻልን ብቻ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከሁሉ በማስቀደም፣ እንዴት ዛሬ ላለንበት አሳዛኝና አሳፋሪ የፖለቲካ ምስቅልቅልና ጦርነት ልንደርስ እንደ በቃን ሁሉም የፖለቲካ ተዋንያኖች በሃቀኝነት የነፍሲያ ፍተሻ (soul searching) ሊያደርጉ ይገባል። እዚህ ላይ፣ ባሁኑ ሰዓት በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ላለው አሳዛኝ ሁኔታ በዋነኝነት የህወሃት አመራር ባለፉት የሽግግር ዓመታት ውስጥ የተከተለው ግትርና ለውይይትና ሽምግልና ያስቸገረ አካሄድ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ አያጠያይቅም። በመሆኑም፣ በዚህ ግጭትና ጦርነት ለሚፈጠረው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ቀዳሚ ተጠያቂነት ይኖርበታል። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ከሚመራው የፖለቲካ ፓርቲ ጀምሮ ሁሉም የፖለቲካ ተዋንያን ወይ መደረግ የማይገባውን ወቅት ሳይጠብቁ በማድረግ፣ አለበለዚያ ማድረግ የሚገባቸውን በወቅቱ ባለማድረግ (acts of commission or omission) ለሁኔታዎች መባባስ የየራሳቸውን ድርሻ እንዳበረከቱ መረዳት ይጠበቅባቸዋል። ይህንን እውነታ አለመቀበልና ችግሩን በሙሉ ‘ከሰይጣናዊው’ የህወሃት አመራር ጋር በማያያዝ ሁሉም ፈተና ይህንን ድርጅት በማስወገድ ሊጠፋ እንደሚችል አድርጎ ማሰብ ሃገሪቱን ለሌላ ተመሳሳይ ችግርና ጥፋት ለማጋለጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ይህ እንዳይሆን፣ ሰፊውን የትግራይ ማህበረሰብና አጠቃላዩን የኢትዮጵያ ህዝብ ባሳተፈ መልኩ ለመሰል ችግሮች መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን መመርመርና መፍትሄ መሻት ይጠቅማል።
እስከዛሬ ለነበሩትና አሁን ላለንበት ውስብስብና አስቸጋሪ ሁኔታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ አበይት ችግሮች አንደኛው በህገ መንግስታዊ ሥርዓትና በፖለቲካ ፍልስፍና መካከል ያለው የጽንሰ ሃሳብና የተግባር መደበላለቅ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት የትግራይ ክልል መስተዳድር በፌዴራል መንግስቱ ላይ ካሰማቸው ክሶች አስገራሚው የፌዴራል መንግስቱ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ጥሷል የሚለው ውንጀላ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚወጡ በርካታ ትንተናዎች አንድ መሰረታዊ ችግር ይታይባቸዋል። ይህም ህገ መንግስታዊ ሥርዓትን ካንዱ ወይም ከሌላው ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ጋር አዛምዶ የመመልከት ችግር ነው። ይህ ችግር በዋነኝነት በህወሃት እና መሰል የፖለቲካ ድርጅቶች አመራር ውስጥ ገኖ የሚታይ ችግር ነው። በመሆኑም፣ ለህወሃት አመራር ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ማለት በአብዮታዊ ዲምክራሲ የፖለቲካ አስተሳሰብ የተቃኘ መንግስታዊ ሥርዓት ብቻ አድርጎ በመውሰድ፣ ከዚህ የተለየ አካሄድ መከተል ኢ-ህገ መንግስታዊነት አድርጎ ይደመድማል። እንዲህ አይነቱ አመለካከት ባንድ ሃገር ውስጥ ያለን የፖለቲካ ምህዳር አረዳድ የተዛባ ከማድረጉም በላይ የፖለቲካ ድርጅቱ የራሱን ድምጽ የሚያዳምጥበት ሳጥን (echo chamber) ውስጥ ታጥሮ ከገሃዱ እውነታ ጋር እንዲጣላና ወደ ውድቀት እንዲያመራ ያደርገዋል። ይህን መሰል ሁኔታ ዛሬ በህወሃት ብቻ የተከሰተ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት የፖለቲካ ሥርዓቶች ላይ የታየ እና ወደፊትም በሌሎች ላይ ሊታይ የሚችል ችግር ነው። ስለዚህም፣ እንዲህ አይነቱን መደበላለቅ የፈጠሩ እና ወደፊትም ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ከመሰረቱ መረዳትና መፍትሄውንም መሻት አሁን አጋጥሞን ያለውን አይነት ፈተናዎች ለመቀነስ አይነተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአበይትነት ሊነሳ የሚችለው መዋቅራዊ ጥያቄ ባሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ጉዳይ ነው። የማናቸውም ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ዋነኛው መሰረቱ ህገ መንግስቱ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ላይ ልዩ ትኩረት ማድረጉ ተገቢ ነው። ባሁኑ ሰዓት በስራ ላይ ያለው የፌዴራሉ ህገ መንግስት ለማንኛውም ጤናማ  ህገ መንግስታዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ የዜጎችንና የማህበረሰቦችን መብቶች የሚያስከብሩ በርካታ መሰረታዊ የህግ አንቀጾችን የያዘ መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን፣ ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው መደበላለቅ ጋር በተያያዘ ህገ መንግስቱን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቅኝት የሚሰጡ አንዳንድ አንቀጾችም አሉት። ይህ ይዘትም ህገ መንግስቱን ባንዳንድ ሁኔታዎች እርስ በርሱ የሚጣረስ አድርጎታል። እንዲህ አይነቱ የግጭት ይዘት በተለይም የክልል መስተዳድሮች ባጸደቋቸው ህገ መንግስቶች ውስጥ እጅግ ገንነው ይታያሉ። በዚህ ረገድ፣ በፌዴራል ህገ መንግስቱ ውስጥ ያሉ የተቃርኖ ምንጮችን መለየትና የክልሎች ህገ መንግስቶችን ከፌዴራሉ ህገ መንግስት ጋር የማጣጣም ስራ መስራት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው። በተለይም በፌዴራሉ ህገ መንግስት የተከበረውንና ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ግዴታ የገባችባቸውን የዜጎችን በየትኛውም የሃገሪቱ ክልሎች በህይወት የመኖር፣ የመስራት፣ ሃብት የማፍራት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቶቻቸውን ማረጋገጥ ከሁሉም ቀዳሚው ተግባር መሆን ይኖርበታል። እነኝህ መሰረታዊ መብቶች በሚጣሱበት ወቅትም የማንኛውንም ክልል ግብዣም ሆነ ፈቃድ ሳይጠብቅ ህገ መግስቱን ማስከበር የፌዴራሉ መንግስት ግዴታ ሊሆን ይገባል። እነኚህን መሰረታዊ መብቶች ማስከበር በምንም አይነት ሁኔታ በፌዴራል ህገ መንግስቱ የተረጋገጡ የቡድን መብቶችን ሊሸራርፍ ወይንም የሚሸራርፍ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም።
ሌላው ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለው ተቋማዊ ችግር፣ በህግ አውጭው፣ በህግ ተርጓሚውና በህግ አስፈጻሚው መካከል ያለው ቅጥ የለሽ መደበላለቅ ነው። ይህ ሁኔታ፣ በእነኚህ ሶስት ቁልፍ ህገ መንግስታዊ ተቋሞች መካከል ሊኖር የሚገባውን የትብብርና የቁጥጥር ሥርዓቶች ከማመንመኑም በላይ በህገ መንግስቱ የተከበሩ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ክፉኛ እንዲሸረሸሩ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አድርጓል። ባለፉት ጥቂት የሽግግር ዓመታት ውስጥ፣ በተለይ የህግ ተርጓሚውን ነጻነት ለማረጋገጥ በፌዴራል ደረጃ የተወሰዱ አንዳንድ እርምጃዎች መኖራቸው ይታወቃል። ነገር ግን፣ አጠቃላይ የሽግግር ሂደቱን ቀደም ሲል ከነበረው ከፍተኛ መዋቅራዊ መደበላለቅ ለማላቀቅ እጅግ በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩ የሚያመላክቱ በርካታ ሁነቶች ዛሬም ይታያሉ። መዋቅራዊ መደበላለቅን መስመር ለማስያዝ በሚወሰደው እርምጃ ውስጥ ሊካተት የሚገባው ሌላው አቢይ ጉዳይ የህዝብ አስተዳደር (civil service) መዋቅሩን ከፖለቲካዊ መዋቅሩ የመለየት ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን በምርጫ አሸናፊ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት አሸናፊ ያደረጉትን ፖሊሲዎቹን የሚያስፈጽሙለትን መሪዎች በበላይ ሃላፊነት መመደቡ ተገቢ ቢሆንም፣ አጠቃላይ የህዝብ አስተዳደር መዋቅሩን ፖለቲካዊ ቅኝት መስጠት ተጠያቂነትን የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ የአገልግሎት ውጤማነትንና መልካም አስተዳደርን የሚያዳክም ይሆናል። ከሁሉም በላይ፣ እንዲህ አይነቱ መደበላለቅ አሁን በሰሜናዊው የሃገራችን ክፍል ጎልቶ እንደወጣው አጠቃላይ መንግስታዊ ተቋማትን የጥቂት አምባገነን ቡድኖች እስረኛና መጠቀሚያ (captive) እንዲሆን ያደርገዋል። በዚህ ረገድ፣ በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መንግስታዊ ያስተዳደር ተቋማትን ከዚህ አይነቱ ፈተና ነጻ እንዲሆኑ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በቅርቡ በሃገራችን ከተከሰተው አስቸጋሪ ሁኔታ ጋር በጥብቅ የሚተሳሰረው ሌላው መዋቅራዊ ችግር ለዘመናት ሰፍኖ የኖረው የሀገሪቱን የመከላከያ ሰራዊት በየወቅቱ ላሉ የአገዛዝ ሥርዓቶች ጠባቂና አገልጋይ የማድረግ ዝንባሌ ነው። አሁን በስራ ላይ ያለው የፌዴራል ህገ መንግስት፣ የመከላከያ ሰራዊቱ ከማናቸውም ፖለቲካዊ ወገናዊነት ነጻ ሆኖ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ከጥቃት ይጠብቃል ይላል። ይህ ድንጋጌ በአንድ ሃገር ውስጥ የተረጋጋ ህገ መንግስታዊ ሥርዓት እንዲኖር ከሚያደርጉ ቁልፍ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ ነው። ያም ሆኖ፣ ለሃያ ሰባት ዓመታት በሀገሪቱ ሰፍኖ የቆየው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቅኝት ወደ ሰራዊቱ ዘልቆ በመግባት አብዛኛውን የሰራዊቱን አደረጃጀትና አመራር ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው አድርጎት ቆይቷል።  ባለፉት ሁለት የሽግግር ዓመታት፣ ይህንን ሁኔታ ለመቀየርና ሰራዊቱን ከማናቸውም ፖለቲካዊ አደረጃጀት ነጻ ለማድረግ በርካታ የአስተሳሰብ (indoctrination) እና መዋቅራዊ ለውጥ ስራ እንደተሰራ ተነግሯል። ነገር ግን፣ በቅርቡ በሰሜን እዝና በመከላከያ ሰራዊት መዋቅር ውስጥ የተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት በዚህ ረገድ ገና ብዙ ቀሪ ስራ እንደሚኖር አመላክቷል። ስለሆነም፣ መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፖለቲካ ቡድኖች ይህንን ለማስተካከል ከተጃመለ ምልከታ በጸዳ መልኩ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ የሃገር ህልውናን እስከ መፈታተን የደረሰውን የክልሎች የልዩ ኃይል አደረጃጀት ወደ ህገ መንግስታዊ የአደረጃጀት ሥርዓት ማስገባት ሌላው አቢይ ተግባር ነው።    
በመጨረሻም፣ በሰሜኑ እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ ከዚህ ቀደም በተፈጠሩ ሃገራዊ ጥቃቶች ወቅት እንደታየው፣ ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ የአንድነት ስሜት ፈጥሯል። ይህ ከሚያጎናጽፈው መልካም አጋጣሚዎች አንዱ ሃገራዊ መግባባትን ለማጠናከር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ነው። ይህንን መልካም አጋጣሚ በቅጡ በመረዳት የብልፅግና ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሃገሪቱን ወደፊት ሊያሻግሩ በሚያስችሉ አበይት ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ቀጣዩን ምርጫ ነፃና ተዓማኒ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። የዛሬ መሪዎቻቸን ከዚህ ቀደም በእንዲህ አይነት ሁኔታ ተፈጥረው የነበሩ መሰል መልካም አጋጣሚዎችን ባለመጠቀማችን ከገባንበት ቀውስ ተምረዋል የሚል ጽኑ እምነት አለን። ይህ ወቅት፣ የሁሉም ፖለቲካ መሪዎች አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት የሚለካበት ወቅት እንደመሆኑ፤ ሃገራዊ አንድነቱ የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ለህዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ እድገትና ልማት ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ አለመጠቀም ከፍተኛ የታሪክ ተወቃሽነት የሚያስከትል ይሆናል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው  ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።

Read 3270 times