Monday, 23 November 2020 00:00

ማይክል ጃክሰን ከሞቱ የአለማችን ዝነኞች በገቢ ቀዳሚ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በተለያዩ የሙያ መስኮች ታዋቂነትን ያተረፉ ከዚህ አለም በሞት የተለዩ የአለማችን ዝነኞችን ገቢ በማስላት በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ ከቀናት በፊትም የ2020 ሪፖርቱን ያወጣ ሲሆን እውቁ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ማይክል ጃክሰን በ48 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የ1ኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ዝነኞቹ በህይወት በነበሩባቸው ጊዜያት በሰሯቸው ስራዎችና በፈጸሟቸው ቀጣይ የቢዝነስ ስምምነቶች እንዲሁም የፈጠራ ሃብት መብት ገቢዎች አማካይነት እስከ ጥቅምት ወር 2020 ድረስ በነበሩት 12 ወራት ያገኙትን ገቢ በማጥናት ደረጃ የሰጠው ፎርብስ መጽሄት፤ የህጻናት መጽሐፍት ደራሲው ቴዎዶር ሲዩስ በ33 ሚሊዮን ዶላር፣ ቻርለስ ኤም ሹልዝ በ32.5 ሚሊዮን ዶላር የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ፣ አርኖልድ ፓልመር በ30 ሚሊዮን ዶላር የአራተኛ ደረጃን መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡
ታዋቂው ድምጻዊ ኤልቪስ ፕሪስሊ በ23 ሚሊዮን ዶላር የአምስተኛ፣ ከወራት በፊት በሄሊኮፕተር አደጋ ከዚህ አለም በሞት የተለየው ታዋቂው አሜሪካዊ የቅርጫት ኳስ ኮከብ ኮቢ ብርያንት በ20 ሚሊዮን ዶላር የስድስተኛ፣ በ21 አመቱ የተቀጨው ራፐር ጁስ ወርልድ ደግሞ በ15 ሚሊዮን ዶላር የሰባተኛ ደረጃን መያዛቸውም ተነግሯል፡፡
በተወለደ በ36ኛ አመቱ በሞት የተለየው የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌ በ14 ሚሊዮን ዶላር የስምንተኛ፣ ታዋቂው ድምጻዊ ጆን ሌነን በ13 ሚሊዮን ዶላር የዘጠነኛ፣ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ፕሪንስ በ 10 ሚሊዮን ዶላር የአስረኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡

Read 3314 times