Saturday, 21 November 2020 10:35

ተስፋ ሰጪ የኮሮና ክትባቶች እየተበራከቱ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በአሰቃቂው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሳር መከራዋን ማየት ከጀመረች አንድ አመት ሊሞላት የአንድ ወር ጊዜ ብቻ የቀራት አለማችን፣ ከሰሞኑ ከዚህ አጥፊ ወረርሽኝ የመገላገያዋ ጊዜ መቃረቡን የሚያመለክቱ ተስፋ ሰጪ ዜናዎችን በማድመጥ ላይ ትገኛለች፡፡
ለወራት ክትባትና መድሃኒት ፍለጋ ደፋ ቀና ሲሉ የከረሙ የተለያዩ የአለማችን አገራት ኩባንያዎችና የምርምር ተቋማት፣ ከሰሞኑ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ፍቱን የሆኑ ክትባቶችን ስለማግኘታቸው ይፋ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡
አሜሪካ፣ ጀርመንና ሩሲያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ኩባንያዎች አስተማማኝነታቸው ከ90 በመቶ በላይ የሆኑ ክትባቶችን ማግኘታቸውን ይፋ እያደረጉ ሲሆን፣ ፋይዘር እና ባዮኤንቴክ የተባሉት የአሜሪካ ኩባንያዎች 92 በመቶ አስተማማኝ የሆነ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ማግኘታቸውን ባስታወቁ በቀናት ጊዜ ውስጥ፣ አሁን ደግሞ ሌላኛው የአገሪቱ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ሞዴርና 95 በመቶ ያህል አስተማማኝ የሆነ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው 30 ሺህ በሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች ላይ ሞክሮ ስኬታማነቱን ያረጋገጠውን ይህን ክትባት በአገልግሎት ላይ ለማዋል ከሚመለከተው አካል በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ፈቃድ ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው ሮይተርስ፣ ለመጀመሪያ ዙር 20 ሚሊዮን ያህል ክትባቶችን ለአሜሪካውያን ለማቅረብ ማቀዱን፣ በሌሎች አገራት ለማቅረብ የሚችልበትን ፈቃድ ለማግኘት እየሰራ እንደሚገኝና በቀጣዩ አመት  1 ቢሊዮን ክትባቶችን ለማምረት ማቀዱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም፤ የወረርሽኙ መነሻ የሆነችው ቻይና እጅግ ስኬታማ የሚባሉ አራት ክትባቶችን በማምረት ላይ እንደምትገኝ የዘገበው ቢቢሲ፣ በተለይም ሲኖቫክ ባዮቴክ በተባለ ኩባንያ የተመረተው ሲኖቫክ የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ክትባት አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን አስታውቋል፡፡
ከማንም ቀድማ የክትባቱን የምስራች ለአለም እነሆ ያለችው ሩሲያ፣ 92 በመቶ አስተማማኝ የሆነ ስፑትኒክ 5 የተባለ ክትባት ማግኘቷን ብታስታውቅም፣ ክትባቱ የምርምር ሂደቱን ያልተከተለና ውጤታማነቱ በገለልተኛ ወገን ያልተጣራ ነው በሚል አሁንም ድረስ እየተተቸ ይገኛል፡፡

Read 2340 times