Tuesday, 24 November 2020 00:00

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የማይተኙ ፖለቲከኞች!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(3 votes)

 የዚህ ጽሑፍ መነሻ ምክንያት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከሁለት ሳምንት በፊት የኪነ ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን እንዲሁም አትሌቶችን ሰብስቦ አገራችን አሁን  ስላለችበት ሁኔታ  የማነጋገሩ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት፣ የጥበብ ሰዎችንና ጋዜጠኞችን እንዲሁም አትሌቶችን  የፈለገው በሕወሓት መሪዎችና እነሱ ባሰማሩት ታጣቂ ኃይል ላይ እየወሰደ ባለው ሕግ የማስከበር እርምጃ፣ እርምጃው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ተደጋፊነት እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ በሙያቸው እንዲያገለግሉ ነው፡፡ ተሰብሳቢዎቹ  ካቀዷቸው ተግባራት አንዱ፣ ሕዝቡ  ለኢትዮጵያ መንግሥት የመከላከያ ኃይል ቀኝ እጁን ደረቱ ላይ በማሳረፍ ‹‹ከልቤ እወድሃለሁ፤ እደግፍሃለሁ›› የሚል ምልክት በማሳየትና በማጨብጨብ  አጋርነቱን እንዲገልጽ ያቀረቡት ሃሳብ ነው፡፡ ይህ ማክሰኞ እለት ከላይ ከቤተ መንግሥት ጀምሮ  ታች እስከ ቀበሌ  ድረስ በተግባር ተገልጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ሥልጣን በያዙ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሕወሓቶች መቀሌ ላይ ስብሰባ ጠርተው፣ ለውጡን እንዴት መታገል እንደሚችሉ እቅድ ሲነድፉ፣ እነ አቶ ኅላዌ ዮሴፍ ‹‹ከደመወዝ ዝርዝር እንጂ ከትግሉ ሜዳ አያወጡንም›› እያሉ ሲዝቱ፣ አቶ ሥዩም መሥፍን ለወጡን ‹‹የቀለም አብዮት›› ብለው ሲያጣጥሉና  ሲደመድሙ፣ ጀኔራል ተክለ ብርሃን ‹‹ለውጡን ጠላት አድርገህ ካልፈረጅከው ልትታገለው አትችልም›› ሲሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ምክትላቸው "ምን እያላችሁ ነው?" ብለው እንዳልጠየቋቸው አስታውሳለሁ፡፡ አንድም የማዕከላዊ መንግሥት ባለሥልጣንም ተቃውሞውን ሲገልጽ አልተሰማም፡፡ ይህን የቅልበሳ ድግስ እያየ  እንዳላየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ  ያለፈው መንግሥት፤ አሁን ‹‹ሰነፍ እረኛ ከሩቅ ይመልሳል›› በሚያሰኝ ቦታ ላይ እንዲቆም መገደዱ  ግልጽ ነው፡፡
እንደ ሕጻን ልጅ እሹሩሩ ሲባል ሁለት ዓመት የደፈነው ሕወሓት፤ በመጨረሻው ሰዓት ብቅ ያለው በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሚሊሽያና  ልዩ ኃይል(ልዩ ጦር ማለት ይቀላል) አዘጋጅቶ፣ ከፊደራሉ መንግሥት ጋር በተቀራረበ ደረጃ ታጥቆ ነው። መንግሥት በማን አለብኝና በትዕቢት የተሞላውን የሕወሓት አመራርና ሠራዊቱን ለመስበር ከሚያደርገው እንቅስቃሴው አንድ ብርቱ ትምህርት እንደቀሰመ  እገምታለሁ፡፡
ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስ፡፡ ደርግ በሥልጣን ዘመኑ በተከተለው ፍልስፍናና እንደ መርህ በወሰደው አሠራር ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን  እንዲዳከሙ አደርጓል። አንደኛው፤ ኢትዮጵያዊያን  የክርስትና፣ የእስልምናም ሆነ ሌላ እምነት ይኑራቸው ‹‹ሰው ባያይ አምላክ ያያል›› ብለው  ስለሚያምኑ፣ እራሳቸውን ከክፉ ሥራ ያርቁ ነበር፡፡ ደርግ "ፈጣሪ የለም፤ ሃይማኖትም የኅብረተሰብ ማደንዘዣና የመንግሥት የአገዛዝ መሣሪያ ነው" ብሎ  በመስበኩ ፈሪሃ አምላክ እየተረሳ በጉልበት ማደር ቀጠለ፡፡
ሁለተኛው ይሉኝ አለማለት ነው፡፡ ይሉኝታ ተራ ቃል አይደለም፡፡ መመስገን እንዳለ ሁሉ መወቀስም አለ፡፡ አንድ ሰው #አንድ ጥፋት ባጠፋ፣ ይህን ያደረገው እሱ ነው እባላለሁ፤ በአደባባይ ልወቀስ ልከሰስ እችላለሁ፤ በእኔ ሥራ የእኔ ልጆች፣ የእኔ ወገኖች የሆኑ ሁሉ ያፍራሉ፤ ስለዚህ እነሱ በየደረሱበት መጠቃቀሻ እንዳይሆኑ እራሴን ከዚህ መጥፎ ሥራ  ማራቅ አለብኝ; ብሎ ከወንጀልና ከጥፋት መሸሽ ነው ይሉኝታ። ይህ አስተሳሰብ፤ ለራስና ለቤተሰብ እንዲሁም ለዘመድ አዝማድ ክብር ማሰብና መጨነቅ ቦታ አጣ፡፡ በፓርቲ አገልጋይነትና ታማኝነት ተተካ፡፡ የፓርቲ ቃል የማይጠየቅ የእግዜር ቃል ሆነ፡፡ የፓርቲ አባልነት ሥልጣን የሚያገኙበት ወንጀል ቢሠሩ የማይጠየቁበት፣ መወጣጫ መሰላል፣ መከላከያ ጋሻና መደበቂያ ዋሻ ሆነ፡፡ የፓርቲ አባልነትና የመንግሥት ሥልጣን የአንድ ሳንቲም ሁለት ፊቶችና የማይነጣጠሉ ሆነው፣ ማንም ምንም ቢያደርግ የማይጠየቅበት ሥርዓት በመዘርጋቱ ፍትሕ እየመነመነች ሄደች፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ለማጥቂያ ዋለ፡፡ ወንጀለኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ለሕግ የማይቀርቡበት በሂስ የሚታለፉበት ወይም ከአንድ ቦታ ተነስተው ወደ ሌላ የሚዛወሩበት አሠራር ተዘወተረ፡፡
አገር በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ደርግን አሸንፎ የመንግሥት ሥልጣን የያዘው በአቶ መለስ ዜናዊ የሚመራው የሕወሓት/ ኢሕአዴግ መንግሥት ፤ የደርጉን ጅምር ፓርቲና መንግሥት የማይነጣጠሉ አንድም ሁለትም ናቸው የሚለውን አሠራር እንዲቀጥል አደረገ፡፡ እንደ ዘመነ ደርግ ሁሉ የፓርቲ አባል መሆን ሥልጣን ማግኛ ብቻ ሳይሆን በመንግሥትም ሆነ በግል ሥራ ሠርቶ ለማደር በየቦታው ይዘው የሚቀርቡት የምስክር ወረቀት ሆነ፡፡ ሁሉም በዘሩ እንዲደራጅ በመደረጉ አንደኛው ፓርቲ ለሌላው አጋርም ሥጋትም ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል  አገር መኖሯን የራሷ መንግሥት እንዳላት ማሰብ የሚቸግራቸው ባለሥልጣናት፣ የመንግሥት ወንበር ይዘው ያለ ኀፍረት ስለ መለያየት መስበክ መቀስቀስን ሥራዬ ብለው ተያያዙት፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ እራሳቸው በአደባባይ ‹‹የአክሱም ሐውልት ለዎላይታው ምኑ ነው?›› ሲሉ ተናገሩ፡፡
 የአክሱም ሐውልትን  ዎላይታው፣ ከፋው፣ አማራው፣ ኦሮሞውና ሌላውም ‹‹የእኔ ነው›› የሚል ስሜት የሚኖረው ኢትዮጵያን አገሬ፣ የትም ቦታ ያለው ሰው  የእኔ ወገን ነው የሚል እምነት ሲኖረው ነው፡፡ ይህን እምነትና ስሜት ለማጥፋት ተዘመተ፡፡ የፓርቲ መሪዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሊገድሉ የታገሉት ይህን መንፈስ እንደነበርና እንደሆነ መካድ አይገባም፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለዚሁ ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጠው አርቲስት ደበሽ ተመስጌን፤ ‹‹ጦርነቱ ተጀመረ ብዬ የማምነው በ1987 ዓ.ም ላይ አንቀጽ 39 በጸደቀ ጊዜ ነው፡፡ ይህ አንቀጽ ሲጸድቅ ኢትዮጵያዊነት እየፈረሰ፣ ልዩነቶች እየሰፉ፣ ጀርባ መሰጣጠት ተጀመረ፡፡ አሁን እየሆነ ያለው የዚያ ውጤት ነው›› ብሏል፡፡ እውነቱም ይሄው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት "ኢትዮጵያ የምትባል አገር በአፍሪካ ካርታ ላይ የት ነው የምትገኘው?" ብለን ብንጠይቅ የሚሰጠን መልስ፣ በምሥራቅ ከሶማሌ፣ በሰሜን ከኤርትራ ወዘተ ትዋሰናለች  ብሎ አይደለም፤ ‹‹የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌደራሉ አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የተወሰነ ነው›› (የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 2) በማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ረግታ እንዳትኖር መፈለጉን በግልጽ የሚያሳይ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ሕገ መንግሥት ይዞ ነው፣ መንግሥት፣ የአገር አንድነት ለማስጠበቅ እንዲሁም የወያኔን አፍራሽ ተግባር ለመታገል፣ የጥበብ ሙያተኞችንና የአትሌቶችን እገዛ የፈለገው፡፡
ስለ አገር አንድነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊያን አብሮ መኖር አስፈላጊነት፣ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ አገሩ ስለመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሕዝብ ስለ መሆናቸው ብዙ ገጣሚያን ጽፈዋል። ብዙ ድምጻዊያን አዚመዋል። ቴዎድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮ)፣ ፀጋዬ እሸቱን፣ ኃይልዬ ታደሰን፣ እጅጋየሁ ሽባባውን፣ ብርሀኑ ተዘራን  መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንዳንድ ድምጻዊያን "ስለ አንድነት ለምን አቀነቀናችሁ?!" ተብለው መታሰራቸውን፣ አገር ጥለው እንዲሰደዱ መደረጋቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
‹‹ሰው ባገሩ መጤ ሆኖ አይታይ፤ በዘር ከፋፍላችሁ አታጨራርሱን›› ብለው የጻፉ፣ አንድነት ኃይልና ትልቅነት መሆኑን ለማሳወቅ የጣሩት ጋዜጦችና ጋዜጠኞች አያሌ ናቸው። የሁሉም የጋራ ችግር የሚሰማ የፖለቲካ አመራር ማጣት ነው፡፡ በፌደራልም ሆነ በክልል በመንግሥት ሥልጣን ይቀመጥ ወይም ተቃዋሚ ነኝ ብሎ ይንቀሳቀስ፣ ችግር ያለው በነዚህ የፖለቲካ ሰዎች አእምሮ ውስጥ ነው፡፡ እነሱ ናቸው ስለ መለያየት በአደባባይ ቆመው የሚሰብኩት፤ እነሱ ናቸው አንዳንድ ጊዜ ተደብቀው ሌላ ጊዜ ፊት ለፊት ቆመው ስለ መጠፋፋት የሚቀሰቅሱት፡፡  ዘመቻው ፊቱን ማዞር ያለበት  ወደ እነሱ ነው፡፡ እነሱ ናቸው ከራሳቸው በስተቀር ሌላውን መስማት የማይፈልጉት፡፡ የእነሱን አእምሮ ነው ከክፉ በሽታ ማጽዳት የሚያስፈልገው። ድምጻዊ ኃይልዬ ታደሰ ስለ ሀገር ካዜመው ልጥቀስ፡-
የኢትዮጵያ አምላክ ይፈርዳል ሳይውል ሳያድር
ይጥልላታል ጠላቷን ከባንዲራው ሥር፤
አይቀር አንድ ቀን መድረሱ ወቅቱን ጠብቆ
ማሪኝ ይላታል ጠላቷ እግሯ ሥር ወድቆ።
አሁን መዘመት ያለበት በፖለቲከኞች ላይ ነው፤ እነሱ ይጥሩ እንጂ  ሕዝብማ ችግር የለበትም፡፡ አገር የቆመችው አብሮ በኖረውና በሚኖረው ሕዝብ መሆኑን ዛሬም እያየን በመሆኑ በሕዝብ ላይ ያለን እምነት የጸና ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ ውስጥ የተንጸባረቀው ሃሳብ የሚወክለው ጸሃፊውን ብቻ መሆኑን እንገልጻለን፡፡


Read 9990 times