Sunday, 15 November 2020 00:00

‘ባለ ከባድ ሥራዎች’ ...ተራችሁን ጠብቁ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  "የምር ግን...አለ አይደል...ትረምፕ ሳይታወቃቸው በአንድ በኩል ለዓለም ውለታ ውለዋል...አማሪካን ተፋቀቻ! ስትፋቅ ሌላ ሆና ተገኘቻ! እነኛ በትንሽ ትልቁ በ“ማእቀብ እንጥላለን!” “እርዳታ እናቋርጣለን!” ምናምን እያሉ ጣታቸውን የሚወዘውዙብን የዲሞክራሲ ጡት አባቶች፣ የዲሞክራሲ ክርስትና አባቶች፣ የዲሞክራሲ ነፍስ አባቶች-"
    
           እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የአገልግሎት ክፍያ ማእከል ነው። በርካቶች ቀደም ብለው መጥተው ተሰልፈዋል፡፡ ከመሀላቸው በእድሜ የገፉ እናቶችና አባቶች ነበሩ... በቂ መቀመጫና፣ አረፍ መባያ በሌለበት ስፍራ ማለት ነው፡፡ እናላችሁ... የክፍያው እንቅስቃሴ ተጀምሮ ሰዉ በየተራው ሦስትም፣ አራትም እየሆነ መግባት ጀመረ፡፡
ታዲያላችሁ... ይህን ጊዜ ነው ‘አጅሬው’ የመጣው፡፡ ቀላል ‘አጅሬ’ መሰላችሁ! እንደውም ሀሳብ አለን...ድንገት ጠፍቶ የገባበት ያላወቃችሁት ወይፈን ካለ ይህን ‘አጅሬ’ ማናገር ሳይሻል አይቀርም፡፡ ልከ ነዋ...ሰውየውማ እንደ እኛ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት እያለ ብቻ ‘ናቹራሊ’ እንዲህ ሊሆን አይችልም፡፡ ግዴላችሁም... የወይፈኑን ጉዳይ ማንሳቱ ክፋት አይኖረውም፡፡
ወይፈኔን፣ ወይፈኔን አይልም ወይ ሰው
በአጅሬው መሀል ላይ አፍጥጦ ሲያየው
ቂ...ቂ...ቂ... ገጣሚ መሆን ቢያቅትም መግጠም ይቻላል፡፡ ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ... ችሎታው ላላቸው ስሜቱ፤ ለእኛ ለእኛ ለ‘ጤና ቡድኖቹ’ ደግሞ ድፍረቱ ነው። ለብድርና ለእንግሊዝኛ የሚያስፈልገው ዋናው ነገር ድፍረት ነው እንደሚባለው ነው።
እዚህ ላይ ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... እንግሊዝኛ ስንል የሆነ ነገር አስታውሶኝ ነው፡፡ ሰሞኑን የተለያዩ ክፍሎች መግለጫ እያወጡ ነው፡፡ አብዛኞቹ በአማርኛ ሲሆኑ የተወሰኑት ምናልባት የውጪውን ማህበረሰብ ታሳቢ አድርገው በእንግሊዝኛም ያወጣሉ፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም እንርሳውማ፡፡ ግንማ ... መግለጫዎቻችሁን በእንግሊዝኛ ማውጣት የሚያስፈልጋችሁ ክፍሎች እባካችሁ... እባካችሁ... እባካችሁ...አንድ፣ ሁለት ቋንቋውን በሚገባ መጠቀም የሚችሉ ሰዎች ይኑሯችሁማ! ቢያንስ፣ ቢያንስ መሰረታዊ የሚባሉ ነገሮችን ማስተካከሉ አፍ ውስጥ ከመግባት ያድናል፡፡ አንዳንዴ እኮ እንግሊዝኛው ከእጅ ሙልጭ ብሎ የጠፋ ነው የሚመስለው፡፡  እንዴ... ‘ስፔልቼክ’ በአቅሟ እኮ ብዙ ታገለግላለች! “እንግሊዝኛ የሚፈልገው ድፍረት ነው” የሚለው የሚሠራው እኛ፣ እኛ ዘንድ እንጂ ‘እንደዛ አይነት’ ቦታዎች አይደለም ለማለት ያህል ነው፡፡ (የኮፒራይት ፈቃድ የምጠይቀው የሆነ ወጣት አጠገቤ ስለጣሁ እንጂ “ኸረ ሼም ነው!” ብል ደስ ባለኝ ነበር።)
እናላችሁ...‘አጅሬው’ ልክ እንደመጣ በሰልፍ የተኮለኮልነውን ከመጤፍ ሳይቆጥረን በቀጥታ ወደ በር ሄደ፡፡ (በጭብጨባ ስላላጀብነው ሳይረግመን አልቀረም፡፡ አለ አይደል..ይህ ከእርምጃ እኩል ‘ጨብ፣ ጨብ’ የሚደረገው ነገር ማለት ነው፡፡ የምር ግን እሱን ነገር የሆነ ሰው “መጀመሪያ የፈጠርኩት እኔ ሆኜ ያለ ፈቃዴ እየተጠቀሙበት ነው። የኮፒራይት መብቴ ይጠበቀልኝ!” ብሎ በሩንም፣ መስኮቱንም ክርችም አድርጎ ባረፈና እኔም የአድናቆቴን ጀበና ቡና በጋበዝኩት፡፡)
ታዲያላችሁ... አጅሬው ሰተት ብሎ ሊገባ ሲል የጥበቃ ሠራተኞች ያቆሙታል፡፡
“ወዴት ነው?”
“ልከፍል..." ከአኮርድዮን እጥፋቶች የእሱ ግንባር እጥፋቶች በእጥፍ ይበልጣሉ። (አገላለጼ በእጥፍ የተጋነነ መሆኑ ስለሚታወቅ አባሪ ማያያዝ አላስፈለገም፡፡ ደግሞ ለማጋነን!)
“በተራ ስለሆነ ሰልፍዎትን ይያዙ!”
እንዴት ተደርጎ! እንዴት ተደርጎ ነው ለ‘አጅሬ’ እንዲህ አይነት መልስ የሚሰጠው! ምን የመሰለች ሳምሰንግ ጋላክሲ ሠላሳ ምናምን የምትመስል ሰዓቱን ብልጭ አደርጎ አየት ያደርጋታል፡፡
“በጣም አስቸኳይ ሥራ አለብኝ፡፡”
(ይሄኔ መሀላችን  በነጋም፣ በመሸም ጠብ፣ ጠብ የሚለው ቢኖር ኖሮ “ልብ አድርጉልን! ሥራ ፈቶች እያለ ሲሰድበን ልብ አድርጉልን!” ብሎ ፍትህ በአደባባይ ይጠይቅልን ነበር! መደገፊያ ወዳጅ አያሳጣችሁማ!)
“ጌታው፣ እባክዎን በሩን ይልቀቁት፤ ሰው ይግባበት፡፡” የጥበቃ ሠራተኞቹ እንደ እሱ በጠፋ ወይፈን የመጀመሪያ ተጠርጣሪ የሚያደርግ ሰውነት ባይኖራቸውም፣ ከተሰጣቸው ሀላፊነት ‘ወይ ፍንክች’ ነበሩ። እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ...እኔ የምለው የጥበቃ ሠራተኞች አለባበስ፣ ማለት የዩኒፎርማቸው አለባበስ የሆነ ስርአት አያስፈልገውም እንዴ!? ግማሽ የሸሚዙ ጠርዝ ከሱሪ ውጭ፤ አንደኛው እጀታ መዳፍ ድረስ፣ ሌላኛው ክንድ መታጠፊያ ድረስ፣ አንድ ጫማ ክሩ የታሰረ፣ ሌላኛው ክር እንዳለው እንኳን ወዲያውኑ የማይለይ...ምናምን ነገር፡፡ እኔ የምለው...አለ አይደል...የመሥሪያ ቤቶቹ ቦሶች ይህን፣ ይህን ማየት አቅቷቸው ነው!
‘አጅሬ’ በቀላሉ የሚሄድ አይመስልም፡፡
“ነገርኩህ፣ ከባድ ሥራ ነው ያለብኝ፡፡”
ይህን ጊዜ ምናልባትም ከሀያዎቹ አጋማሽ የማታልፍና ፈርጠም ያለች ወጣት ከት ብላ ትስቃለች፡፡ ጥበቃዎቹ በፈገግታ አጀቧት፡፡ ሰውዬው ዞር ብሎ አፈጠጠባት፡፡
“ምን ታፈጣለህ? የእኔ አይነት ቆንጆ አይተህ አታውቅም እንዴ!” አለችው፡፡ ከፊሉ ሰው ከልቡ፣ ከፊሉ ለመመሳሰል ሳቀ። ‘አጅሬው’ ፊቱን ወደ ጥበቃዎች አዞረ፡፡
“ሥራዬ ላይ ችግር ቢፈጠር እናንተንም መሥሪያ ቤቱንም ነው የምጠይቀው፡፡” (ይህ ዘመን ምን፣ ምን አይነቱን ነው የፈጠረብን እባካችሁ!)
ይህን ጊዜ ከሦስቱ ጥበቃዎች በእድሜ በለጥ ያሉት ፊታቸው ጠየም አለ፡፡ ሁለቱ ከሠላሳዎቹ ያልዘለሉት ግን ሳቁ፣ ያውም ደረታቸውን ነፍተው፡፡ ይህን ጊዜ ያች ወጣት ለጥበቃዎቹ...
“ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ካለ ችግር የለም፣” አለቻቸው ወደተሰለፈው ህዝብ እየጠቆመች፡፡ ይሄን ጊዜ  የነበረው ሳቅ ሚስተር ቢን እንኳን የሚቀናበት ነበር፡፡
“እያስጠነቀቅኋችሁ ነው፡፡ ሥራ ላይ አንድ ነገር...."
ይህን ጊዜ አንደኛው ጥበቃ ኮስተር ብሎ አቋረጠው... “የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ። አሁን ከዚህ የማይሄዱ ከሆነ ፖሊስ እጠራለሁ፡፡” ፈረንጅ ‘ዘ ማጂክ ወርክድ’ እንደሚለው፣ ፈርጅ ‘አጅሬ’ውን ‘በሚገባው ቋንቋ’ አናገረው መሰለኝ፣ የሄደበት ፍጥነት ወደ ሶምሶማ ሊጠጋ ምንም አልቀረው። ‘ዩኒቨርሳል’ የሚሉት ሳቅ ይሄኔ ነበር። ከዚህ በኋላ የሆነው ግን ሳቁን መሀል ላይ ቆረጠው፡፡ ለካስ ሰውየው መኪናውን ማዶ አቁሞ ነበር፤ በሩ አጠገብ ደረሰና ወደተሰለፉት እያየ ሞባይሉን አውጥቶ፣ ንዴት በተቀላቀለበት ሁኔታ እየተወራጨ መናገር ቀጠለ፡፡ ይሄኔ ከተሰለፉት አንዱ ወጣት እዚህ ላይ ሊጻፍ የማይችል ነገር ተናገረና፣ ወደ ሰውየው ሊሄድ ሲል ጎትተው አስቀሩት፡፡ ለካስ ‘አጅሬው’ በእሱ ቤት ማስፈራራቱ ነበር...
“ወንድሜ ፖሊስ ስለሆነ ሁልሽንም አስለቅምሻለሁ፣” እያሉ ሰፈሩን ‘ቴረር በቴረር’ ያደርጉት እንደነበሩት እንትናዬዎች ማለት ነው፡፡
ግራ ግብት የሚላችሁ እኮ እንዲህ አይነት ሰዎች ሌላውን እንዴት ነው የሚቆጥሩት! ልክ ከእነሱ በስተቀር ሌላው ሰው ሁሉ ሥራ የፈታ ያስመስሉታል። ምን መሰላችሁ...በበርካታ ቦታዎች በፈለጋቸው ሰዓት መጥተው ሌላው ተራ እስኪደርሰው ሲጠብቅ ያረፈደውና የዋለው እያለ በመጡበት ሰዓት “ቀይ ምንጣፍ አንጥፉልኝ፣” ለማለት ምንም የማይቀራቸው ‘ባለጉዳዮች’  በተደጋጋሚ  ይገጥሙናል፡፡
ስሙኛማ...እኚህ ትረምፕ የሚሏቸው ሰውዬ በ“ፉርሽ ባትሉኝ” እያመሱት ነው... አይደል! አይ አማሪካን... ያቺ ትልቅ፣ በጣም ትልቅ፣ እጅግ በጣም ትልቅ፣ ከእግዜር በታች ያለነው እኛ ነን በሚሉ ፖለቲከኞች የተሞላች ሀገር፡፡
የምር ግን ...አለ አይደል...ትረምፕ ሳይታወቃቸው በአንድ በኩል ለዓለም ውለታ ውለዋል...አማሪካን ተፋቀቻ! ስትፋቅ ሌላ ሆና ተገኘቻ! እነኛ በትንሽ ትልቁ በ“ማእቀብ እንጥላለን!” “እርዳታ እናቋርጣለን!” ምናምን እያሉ ጣታቸውን የሚወዘውዙብን የዲሞክራሲ ጡት አባቶች፣ የዲሞክራሲ ክርስትና አባቶች፣ የዲሞክራሲ ነፍስ አባቶች፣ የዲሞክራሲ ምናምን አባቶች...ዲሞክራሲያቸውን እያየንላቸው ነዋ! አማሪካን ... ‘ለማያቅሽ ታጠኝ!’ ቂ...ቂ...ቂ...
እናማ... በየአገልግሎት መስጫ በፈለጋችሁት ሰዓት እየመጣችሁ ...“ከባድ ስራ አለብኝ...” ምናምን የምትሉ ሰልፍ ያዙና ተራችሁን ጠብቁማ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1170 times