Saturday, 14 November 2020 10:54

የዘመን እውነት

Written by  ፊደል ችሎ
Rate this item
(1 Vote)

  "--ዘመን የራሱ ባህል፣ የራሱ እውነት አለው፡፡ ታሪክ እንደሚያስረዳን፤ የሰው ልጅ በለውጥ ሂደት አልፎ ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰፍቶ የሳይንስና የፍልስፍና ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ ዛሬ ነገሮች የሚዳኙት ፍልስፍና ካለ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ነገሮች እውነት ተብለው የሚፀድቁት ወይም ሀሰት ተብለው የሚወገዱት በምክንያት ተመዝነው ነው፡፡--"
                
            በሰው ልጅ የመኖር ታሪክ፣ በየዘመኑ፣ በየባህሉ፣ ሰዎች እንደ ማህረሰብም እንደ ግለሰብም ዓለምን የሚረዱበት መንገድ፣ ችግርን የሚቀርፉበት ብሂል አለ፡፡ ከጥንት የጋርዮሽ ስርአት ጀምረን ብንታዘብ፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮውን ለመተርጎም፣ ኑሮው ዉስጥ ትርጉም ለመፍጠር መኖሩን ሊጠይቅ አንዴ ሐይማኖትን ሌላ ጊዜ ሳይንስን አልያም ፍልስፍናን ይዞ ይታገላል፡፡ የሽምግልና ሂደት፣ እሳትን ከድንጋይ መፍጠር፣ በዋሻ መኖር፣ ጎጆ መቀለስና ወዘተ… የሰው ልጅ ችግሩን ይፈታ ዘንድ እንደየ ዘመኑ መፍትሔ ያላቸው መንገዶች ናቸው፡፡
በየዘመኑ ነገስታት ወይም ትምህርት ቤት የገቡ ግለሰቦች ለውጥ ማለት፣ የመማር ጥቅሙ፣ መጠየቅ ማለት እያሉ የዘመናቸውን እውነት ይበጃል ያሉትን እንዲህ ይሉናል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፣ ባለቅኔዎች፣ አዝማሪዎች፣ ምሁራን፣ የህዝብና የሀገር ችግር ያሉትን በቅኔ ወይም ምሳሌ ሰርተውለት በጉባኤ እንዲህ ይሉታል። ለምሳሌ ብንባል ዘርዐ ያቆብ ፈላስፋን ይዘን፣ ገ/ህይወት ባይከዳኝ አፈወርቅ ገ/የሱስ፣ አለቃ ገ/ሐና እስከ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ድረስ ብንጠቅስ፣ በየዘመናቸው ችግር ያሉትን ከመንቀስ ይበጃል ያሉትን መፍትሔ ከመናገር ወደ ኋላ አላሉም። የገብሬን መረዳት ወይም የመስፍንን አመክንዮ ይዘን የኢትዮጵያን የማህበራዊ እውነቶች ለመፈተሽ ብንነሳ፣ ዛሬም ያኔ ችግር ያሉት ኋላ ቀርነት፣ ዛሬም ያኔ አይበጅም ያሉት የደቦ እውነት እንቅ እንዳደረገን ነው። ዘንድሮም እንደ ድሮው ያንን ጋራ አልፎ እውነት ለማየት የሚፈራ፣ ብቻ እስከ የሚያየው ርቀት የሚለካ የሚቆርጥ ባህል አለን፡፡
ዘመን የራሱ ባህል፣ የራሱ እውነት አለው፡፡ ታሪክ እንደሚያስረዳን፤ የሰው ልጅ በለውጥ ሂደት አልፎ ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰፍቶ የሳይንስና የፍልስፍና ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ ዛሬ ነገሮች የሚዳኙት ፍልስፍና ካለ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ነገሮች እውነት ተብለው የሚፀድቁት ወይም ሀሰት ተብለው የሚወገዱት በምክንያት ተመዝነው ነው። በዘመናት መካከል የሚታይ ልዩነት አለ፤ ከጥንት የአደንና ለቀማ ዘመን ጀምረን እስከ ዘመነኛው ስርአት ማለትም የነፃ ገበያ ርዕዮት  ድረስ ብንቆጥር  ጎላ ያለ ልዩነት፣ አንዳንዴም ጨርሶ የተለየ ባህል እናገኛለን፡፡ ለዚህ ነው ዘመን የራሱ ባህል አለው ከሚለው አተያይ  ለመድረስ ወሳኝ  ምክንያት የሚሆነን፡፡ በአንድ ዘመን ገዳይ የሚወድስበት፣ ጉልበተኛ የሚፈራበት፣ ማሽላ ጠባቂዎች ሳይቀሩ የሚገጥሙለት አለፍ ሲልም የሚመኙት ባህል ነበር፡፡ ቢሆንም  ዛሬ  ዘመናዊነት ዓለምን ከእንዲህ ያለው የባህል ማእቀፍ አውጥቶ ሌላ ስርአት ውስጥ ከቶታል፡፡ ይህ የሰው ልጅ ታሪክ ቢሆንም ዛሬም የሰው ልጅ የደረሰበት፣ የስራው ውጤት፣ የሰራው ስርአት የማይመስላቸው አያሌ  ናቸው፡፡  
ልጅ ከአባቱ የተሻለ ሰፋ ያለ ስርአት የሚሰራበት የለውጥ ስርአት አለ፡፡ ሰብአ ትካት የደረሱትን ብራና ፍቀው ፊደል፤ አለት ቀርፀው ቤተ-መቅደስ አቁመዋል፤ ምን አልባት ራቅ ያላቸውን ተረትና ምሳሌ ሰርተውለት ለቀጣዩ ትተውታል፡፡ ይህ ከሆነ ታሪክን ማስፋት፣ የተጀመረውን ማስቀጠል እንዲሁም ማሻሻል የቀጣዩ ትውልድ ሀላፊነት ይሆናል ማለት ነው፡፡
ዘመን ተራማጅ ነው፤ በርትተው የሚከተሉትን ይፈልጋል፡፡ ይህ ቢሆንም አንዳንድ ማህበረሰባዊ እሳቤዎች እዚያ ምን አለ፣ እዚህ ምን ጎደለ ብለው ከቆሙበት ነቅነቅ ለማለት ፈራ ተባ ሲሉ ይስተዋላል። ኢትዮጵያኖች ሁለት እምነቶች ላይ ትኝት ያሉ ይመስለኛል፤ ትዝታ እና ተስፋ ላይ፡፡ በአንድ በኩል ብዙዎቹ  ስለ ድሮ ተናግረው፣ ስለ ድሮ ፅፈው አይጠግቡም፡፡ ዛሬ ለእነዚህ ሰዎች ወዝ የሌለው ምንችክ ያለ ነው፤ ድሮ ይሻል ነበር ባህል፡፡ ዛሬ የከሰሩትን የጠፋባቸውን የህይወት ጣዕም በትናንቱ በጎ ዘመናቸው ሊጠግኑት ይታገላሉ፡፡ በሌላ በኩል ዛሬን ነገ የተሻለ የሚመኙ፣ ነገ ይነጋል ማለት የሚቀናቸው አሉ፡፡
በሌላ በኩል ነገ የተሻለ የሚመኙ፣ ነገ ይነጋል ባዮች፡፡  
ብዙዎች በተቃራኒያቸው የቆመውን ለመተቸት፣ ሀሰት ለማለት ትንሽ አያዳግታቸውም፡፡ ይህ ዘመን አብዝቶ ከሚነግረን ሀቆች አንዱ ብዝሀነት እንዲሁም የባህልና ባህል መበዳደርን ነው፡፡ በተጨማሪም እንደ ዘመኑ ብልሀት ቢመዘን የማንም ሃሳብ እውነት ሆኖ የሚገኝበት፣ የማንም ሃሳብ ሀሰት ተብሎ የሚወድቅበት አተያይ የለም፡፡ ይልቅስ፣ ያም ይህም ተዋጥተው የተሻለ የሚሰሩበት፣ ሌላ አማራጭ የሚፈጥሩበት ይደገፋል፡፡
በኢትዮጵያ የፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የስርአትና የባህል ለውጥ እንዲመጣ በተጨማሪም የህዝቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ ከዲቀቀ እስጢፋኖስ ጀምሮ ብዙዎች ታግለዋል፡፡ ፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብም ዳርና ዳር የቆሙ እሳቤዎች ይታረቁ ዘንድ፣ ትውልድ ባህሌ ሀይማኖቴ ከሚል እሳቤ ይወጣ ዘንድ አስተምሯል። ፍልስፍናውም የሰው ልጅ ለልቡ ብቻ መገዛት እንዳለበት ታወሳለች፡፡
እንደ ዘርዐያቆብ አስተሳሰብ፤ የልቦናችን መረዳት ከዘፈቀደ ህይወት የሚያወጣን መንገድ ነው። እውነት የምንለው ለልቦናችን የሚገጥም ሀቅ ብቻ ሲሆን ነው፡፡ ለዚያም ነው ፍልስፍናው እንዲህ እያለ ጮሆ የሚናገረው “ወለተሰምየ ምስለ ልብየ”፡፡  
ሰዎች ነን ያጓጓናል፣ እንመኛለን ዘመኑን ብንካፈለው፤ እዚያ ጋ ያለውን እውነት ብናየው ብንሰማው፡፡ እንደ ዘመኑ እውነት የምንሰማ የምናየውን ለምን እንዴት እያልን መዝነን ገንዘብ ብናደርገው እንመኛለን፡፡ ግን አሁንም ዘመኑ የሚፈልገውን ለመሆን፣ አብረን ለመብረር አልቻልንም፡፡ ይህንን ከዘመን ጋር አለመገናኘታችን ገጣሚው እንዲህ ብሎታል፡-
እኛ እኮ ለዘመን ክንፎቹ አይደለንም ሰንኮፍ ነን ለገላው
በታደሰ ቁጥር  የምንቀር ከኋላው
የፖለቲካ አመላከከታችን፣ የችግራችን ስፋት፣ ኢትዮጵያን የምንረዳበት መንገድ የተለያየ፤ ችግራችንም  ያሰብንለት መልስም ጨርሶ የማይገናኝ ይሆናል፡፡ ግን እንዴት የዘመን መገስገሱ አይቆነጥጠንም? እንዴት ከአምናው ለዘንድሮ የሰው ባህሪው የዘመን ጥላው አያጠላብንም፡፡ ብዙዎቻችን እይታችን እንደ ችግራችን ልክ ይወሰናል። አንድ ቲማቲም የቸገረው ነገሮች ሁሉ ከቲማቲም ጋር እንዲያያዙ ይፈልጋል። አለ ደግሞ አዲስ አበባ ብቻ ሀገር መስላ የምትታየው፤ አለ ይቺ ሽሮ ሜዳ ብቻ የለማች መስላ የምትታየው፣  ይቺ ለገጣፎ ብቻ የተጎሳቆለች የሚመስለው፡፡
እኔ እመኛለሁ አንድ የጎጃም ጎበዝ በሸዋ አሳብሮ፣ ወደ አርሲ ዘልቆ፣ ወደ ሀረር አልፎ፣ እስከ ጎዴ ቢያካልል፣ ውሏቸውን ቢውል፣ እዚህ እነማን ይኖራሉ፣ በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች ብሎ ቢያይ! ይህኔ ለጎጃም ብቻ የሚቀኘውን፣ የሚቆጨውን አባይን ተሻግሮ ሀገር፣ አባይን ተሻግሮ ሌላ አለም፣ ሌላ እውነት እንዳለ ይረዳል፡፡
አንድ ሀገር፣ በውስጧ እጅግ የተለያዩ የኑሮ ዘዴዎች፣ እሳቤዎች መያዟ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ እያንዳንዱ ማህበረሰብ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ዓለምን የሚያይበት፣ ተፈጥሮን የሚረዳበት፣ ሲደሰት ሲያዝን ስሜቱን የሚያጋራበት ብሂል የተለያያ ነው። ሆኖም ግን፣ አንዳንዴ ጨርሶ ለመፍትሔ የማይሆኑ፣ ምክንያትን በሩቁ የሚፈሩ ባህሎችም መኖራቸው እውነት ነው፡፡ ብቻ እውነቴ የሚሉት ሀቅ እስከ ባህላቸው ስፋት፣ እስከ አተያያቸው ጥግ ይወሰናል፡፡ አንዳንድ ባህሎች ከዘመን ጋር እንዳንተያይ ያደርጉናል፣ ያንን ጋራ አልፎ ሌላ እውነት እንዳናይ እጥር፡፡
አንድ እሳቤ ሌላ እውነት እንዳለ የሚረዳው ለምን ብሎ የሚጠይቅ ከሆነ ነው፤ ስለዚህ ከዘመኑ ጋር ለመሆን ፈላስፋው ዘርዐ ያቆብ እንደሚያስረዳን፣ እያንዳንዳችን እውቀትን ለማገኘት የልቦናችንን እሳቤ ብቻ ትክክለኛ ነው ብለን ማጠር የለብንም፤ ከምናይ ከምንሰማው እህ እያልን መጠየቅ ይገባል ማለት ነው፡፡

Read 4461 times