Saturday, 14 November 2020 10:46

“እረኛው ሀኪም” መፅሐፍ ተመረቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

የእውቁን የቀዶ ጥገና ሀኪም የፕሮፌሰር ምትኩ በላቸውን ከከብት እረኝነት እስከ ከፍተኛ  የቀዶ ህክምና ፕሮፌሰርነት የሚዘልቅ የሕይወት ውጣ ውረድን የሚያስቃኘው “እረኛው ሀኪም” መፅሀፍ ከትላንት በስቲያ በሂልተን ሆቴል ተመረቀ። መፅሐፉ ከዚህ ቀደም “LE BERGGER DEVENU CHIRURGIEN” በሚል ርዕስ ቤልጀም  ውስጥ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተፅፎ ለንባብ የበቃ ሲሆን መፅሀፍ በአርቲስት አዜብ ወርቁ ልጅ በማሪዮን ኩዋሎ “A Shepherd Became a Surgeon” በሚል ርዕስ እንጊሊዘኛ ወደ ተተርጉሞ ለንባብ በቅቶ ነበር።
ይሁን እንጂ በምእራብ ሸዋ ወንጪ በተራራማ የገጠር ቀበሌ ተወልደው እስከ 12 ዓመት እድሜያቸው በከብት እረኝነት ያሳለፉትና በዓለም ላይ እውቅ ከሆኑ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስች አንዱ ለመሆን የቻሉት ፕሮፌሰር ያሳለፉት የጥንካሬና ስኬት ህይወት በአማርኛ ለትውልዱ መድረስ አለበት በሚል አርቲስት አዜብ ወርቁ “ እረኛው ሀኪም” በሚል ርዕስ ተርጉማ ለምርቃት በቅቷል። መፅሀፉ የፕሮፌሰሩን ህይወት ከእረኝነት እስከ ህክምና ያስቃኛል። በ67 ዓመት ዕድሜቸው በአፍሪካ ትልቁን ከሊማንጃሮ ተራራን የወጡ ሲሆን “ ፓላራስኮፒክ” የተሰኘውን ያለ ህመም ቀዶ ህክምናን ከፈጠሩት የዓለም ሀኪሞችም አንዱ ናቸው።
በምርቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ፕሮፌሰሩ ተገኝተው ልምድ ያካፈሉ ሲሆን የቢጂ.አይ ኢትዮጵያ ለመጽሀፉ ህትመትና ምረቃ አጋር ሆኗል።  የሞሮኮ አምባሳደር በኢትዮጵያ የሆኑት የፕሮፌሰር ምትኩ ባለቤት፣ የመፅሀፉ ተርጓሚ አዜብ ወርቁ፣የቤልጂየም አምባሰደር በኢትዮጵያ፣ የመፅሀፉ አርታኢ ደራሲ  ሃይለ መለኮት መዋዕል፣ የቢጂአይ ኢትዮጵያ አመራሮች፣ መጋቤ ሀዲስ አለማየሁና በፕሮፌሰሩ ህክምና የተደረገላቸው ግለሰቦች ተገኝተዋል። በ11 ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ253 ገፅ የተቀነበበው መፅሐፉ በ250 ብር እና በ21.65 ዶላር ለገበያ ቀርቧል።

Read 3515 times