Print this page
Saturday, 07 November 2020 13:58

የጃሉድ አስገራሚ ንግግሮች

Written by 
Rate this item
(9 votes)

   (በተለየ የአዘፋፈን ስልቱ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈው ድምፃዊ ጃሉድ፤ በቃለ-መጠይቆች ላይ በሚሰጣቸው አስቂኝና አስገራሚ ምላሾችም  ይታወቃል፡፡ "የጃሉድ 10 አስቂኝ ንግግሮች" በሚል በዩቲዩብ ላይ ካገኘናቸው ከተለያዩ ሚዲያዎች የተሰባሰቡ ቃለ ምልልሶች መካከል ለጋዜጣ
አቀራረብ ምቹ የሆኑትን መርጠን እነሆ ብለናል - ዘና እንድትሉበት፡፡)



             ጋዜጠኛ፡- ስለ ስራዎችህ እንጂ ስለ ህይወትህ ብዙም እውቀት የለንም። ስለ ትውልድህና እድገትህ ትንሽ ብታጫውተን…….?
ጃሉድ፡- ትውልድ… የተወለድኩት መንገድ ላይ ነው። እዚህ ጎተራ የሚባል ቦታ…። ያው እንግዲህ ምጥ መጣ ተባለና ወደ ሆስፒታል እናትህን ስንወስዳት… ጎተራ ጋ ተወለድክ ነው ያሉኝ።
ጋዜጠኛ፡- አዲስ አበባ ማለት ነው?
ጃሉድ፡- አሁን ቀለበት መንገዱ ማለት ነው፡፡ ፈርጡ እኔ ነኝ መሰለኝ… አላውቅም (እየሳቀ)
አስፋው (ኢቢኤስ)፡- አሜሪካን ሃገር ኮንሰርት ላይ ባገኘሁህ ሰዓት፣ ትንሽ ችግር ላይ ነበርክ መሰለኝ....  ምን ነበር የተፈጠረው በዚያን ወቅት?
ጃሉድ፡- እ….እኔ አልገባኝም…
አስፋው፡- አልጫወትም እስከ ማለት ሁሉ ደርሰህ ነበር?
ጃሉድ፡- እንትን ነው… ልክ ዋንጫው የተወሰደ ቀን…..
አስፋው፡-  የዋንጫው ዕለት!
ጃሉድ፡- እንግዲህ እኔ የማውቀው …..ለሃገሪቱ ኪነ ጥበብ ብዙ መድከሜን ነው… እንጂ ሌላ ነገር አላውቅም። እነሱ ታዳጊ ልጆች ናቸው… መድረክ ላይ መጥተው የሆነ የሆነ ነገር ተናገሩኝ። የብሔር ብሔረሰቦች ሰንደቅ በሙሉ የእኔ ነው…. ከዚህ በፊትም የነበረው የእኔ ነው… የኃይለስላሴም ባንዲራ የእኔ ነው፡፡ ዛሬ ባንዲራ በዝቷል……ባንዲራው በሙሉ የእኔ ነው።
ግን የፈለኩትን ብይዝ ባልይዝ ችግር የለብኝም….. ብዕር ይበቃኛል ለእኔ፡፡ “ለምን ይሄንን  አደረክ… ባንዲራ እንደዚህ ነው… እኛ እንደዚህ እንባላለን” ምናምን ብለውኛል። እኔ ምን አገባኝ… እዚያ ውስጥ! በዚያ የተነሳ ነው ረብሻው የመጣው። እኔ አገሬን እወዳለሁ፡፡ እዚያም ያሉት አገራቸውን አይጠሉም። በመጨረሻ ተያይዘን… ጓዛችንን ይዘን፣ ወደ አገራችን እንግባ አልኩኝ። በቃ ቢቸግረኝ -- እንደዚህ ነው ያልኩት። ሌላ ነገር አልተናገርኩም።
ነፃነት (የቤተሰብ ጨዋታ)፡- ጃሉድ… በጣም የሚያሳስብህ ነገር ምንድን ነው?
ጃሉድ፡- አረ ምንም! (ቆፍጠንና ኮስተር ብሎ)
ነፃነት (በረዥሙ ከሳቀ በኋላ)፡- ምንም አያሳስብህም?
ጃሉድ፡- አይ ምናልባት… አፈር ውስጥ ገብቼ፣ ከላይ አፈር ሲጭኑብኝ… እሱ ብቻ ያሳስበኛል።
እንደው  እንዳላውቀው……እዚያ ጋ ሆኜ እያወቅሁት ከጫኑብኝ…..
ነፃነት፡- ማንም አውቆ አያውቅም።
ጃሉድ፡- አንተ… ገብተህ ታውቃለህ?
ነፃነት፡- ማንም አውቆ አያውቅም፡፡
ጃሉድ፡- አረ? እርግጠኛ ነህ?
ነፃነት፡- አዎ!
ጃሉድ፡- እስቲ (እጁን ይዘረጋና ይመታዋል) በቃ እሱ ብቻ  ነው የሚያሳስበኝ…
ጋዜጠኛ፡- እስቲ ስለ ግል ህይወትህ ንገረን …ትዳር አለህ? ትዳር ላይ ያለህ ስሜት እንዴት ነው?
ጃሉድ፡- አዎ እሷ ነገር ትቀረኛለች መሰለኝ። እሷ ነገር ከተሟላች… ዓለም ለእናንተ ዘጠኝ ናት አይደል… ለእኔ አስር ትሆናለች… አስር ትሞላለች፡፡ እሷ ነገር እስክትስተካከል… ያው ላገባ ነው፡፡ (ይቅርታ አግብቻለሁ ብያችሁ ነበር።) አሁንም እሷም ከሰማችኝ አላውቅም…. አልገረመችኝም፡፡ ሌላ የምትገርም አይቻለሁ…. ከእንደገና ሌላ ላገባ ነው።
ጆሲ፡- አሁን በእኔ በኩል ጥያቄዎቼን ጨርሻለሁ። ጃሉድ… ቀረ የምትለው ነገር ካለ ወይም ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ..…ወይም ምስጋና ማቅረብ የምትፈልግ ከሆነ …. ዕድሉን ልስጥህ…..
ጃሉድ፡- ጆዬ … አንተ ለብዙ ሰው ቤት አሰጥተሃል… መኪና አሰጥተሃል…ህመምተኞች ጤነኛ አስደርገሃል። አሁን ለእኔም እንግዲህ ሁለት የአንበሳ ግልገል አሰጠኝ። በቃ በመጨረሻ የማስተላልፈው መልዕክት ይሄ ነው ጆዬ….
ጆሲ (በሳቅና በድንጋጤ መሃል ሆኖ)፡- ሁለት የአንበሳ ግልገል?
ጃሉድ፡- አዎ ግልገሎች አሰጠኝ…
ጆሲ (አሁንም እየሳቀ)፡- ምን ታደርጋቸዋለህ?
ጃሉድ (ኮስተር ብሎ)፡- በቃ አብሬያቸው እኖራለሁ ...የቤት እንስሳት ማድረግ እፈልጋለሁ።
ፍላጎቴ ነው ጆዬ - ምን ችግር አለው?! ምን ችግር አለው?!  

Read 5673 times
Administrator

Latest from Administrator