Saturday, 07 November 2020 13:37

4ኛው ጣና ማህበራዊ ሽልማት - “ትኩረት ለጤና፤ ትኩረት ለጣና” አሸናፊዎች ምን ይላሉ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   (ጣናን ከእንቦጭ ለመታደግ ሲሉ ህይወታቸውን የገበሩ ሁለት ግለሰቦች የክብር ኒሻን ተሸላሚ ሆነዋል)

           የዘንድሮ ጣና ማህበራዊ ሽልማት “ትኩረት ለጤና፤ ትኩረት ለጣና” በሚል በእንቦጭ የተወረረውን ጣናን ለመታደግ፣ በኮቪድ-19 ዙሪያ የማህበረሰቡን ግንዛቤ አግኝቶ ራሱን ከአስከፊው ወረርሽን እንዲጠብቅ ሳይታክቱ በማህበራዊ ሚዲያ መረጃ ሲያጋሩ፣ ማህበረሰቡን ሲያነቃቁና ሲያስተምሩ የነበሩ ተቋማትና ግለሰቦች ባለፈው ጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም በጣና ሃይቅ በጣናነሽ በተባለችው  ጀልባ ላይ በአማራ ፖሊስ ማርቺንግ ባንድ በታጀበ ደማቅ ስነስርአት በባህር ዳር ተካሂዷል። በዚህ የሽልማት ስነ-ስርአት ላይ የታደመችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከተሸላሚዎቹ ጥቂቶቹን አነጋግራ እንደሚከተለው አጠናቅራለች።  

              “የፈጠራ ስራዎቼ 34 ደርሰዋል፤ የጣናን ሽልማት ለሁለተኛ ጊዜ አሸንፌያለሁ”

               ኢዘዲን ካሚል እባላለሁ ተወልጄ ያደኩት ወልቂጤ ከተማ ሲሆን  የ12ኛ ክፍል፣ ተማሪ የ19 ዓመት ወጣት ነኝ። ዘንድሮም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉ ነው አሸናፊ የሆንኩት። እውነት ለመናገር ዘንድሮ አሸንፋለሁ ብዬ አላሰብኩም። ምክንያቱም በእኔ ዘርፍ በጣም ትልልቅ ሰዎች ነበሩ የተወዳደሩት። በዚህ ምክንያት አልጠበኩም ነበር።
የፈጠራ ስራዎቼን በተመለከተ  እስከ አሁን 34 አይነት የፈጠራ  ሥራ ሰርቻለሁ። ከነዚህም ውስጥ በፀሃይና በኤሌክትሪክ ቻርጅ የሚንቀሳቀስ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ፣ ፀጥታ ወደ ሚፈልጉ የተለያዩ ስፍራዎች ማለትም ቤተ-ክርስቲያን፣ መስጊድ፣ የስብሰባ ቦታዎች ስንሄድ በመርሳት ወይም በችኮላ ድምፅ አልባ (ሳይለንት) ሳናደርግ ስንገባ ድንገት ይጮህና ይረበሻሉ። ይሀንን የሚረብሽ ነገር ለመቅረፍ የሰራሁት ፈጠራ ሰዎች ወደነዚህ ቦታዎች ሲሄዱ ስልካቸውን በራሱ ጊዜ ድምጽ አልባ የሚያደርግና ከዚያ ሲወጡ ድምጽ እንዲኖረው የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ነው። ሌላው እሳት አደጋ ቤት ውስጥ በሚከሰትበት ሰዓት አምስትና ከዚያ በላይ ለሆኑ የቤተሰቡ አባላት እሳት አደጋ መከሰቱን በአላርም የሚያሳውቅ ነው። እነዚህ ከሰራኋቸው ዋና ዋናዎቹና የቅርቦቹ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በትምህርት ሚኒስቴር “stem power”  በተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ድጋፍ ይደረግልኛል። ስቴም ፓወር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ነው  የሚሰራው። በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ዓመት እውቅና አግኝቻለሁ። ከዚህ ውጪ የተለያ የግል ድርጅቶች እውቅና እየሰጡኝ ነው። ከነዚህ ውስጥ ጣና ማህበራዊ ሚዲያ አንዱ ነው። ይኸው  ወደፊት ለምሰራቸው አዳዲስ ፈጠራዎች ነው። ስለዚህ ማመስገን እፈልጋለሁ።
ለወደፊት ትልቅ ኢንተርፕረነር መሆንና ለብዙዎች የስራ እድል መፍጠር እፈልጋለሁ። ፈጠራዎቼን ወደ ምርት በመቀየር፣ችግር ፈቺ፣ኢኮኖሚ አፍላቂ እንዲሆኑ ማድረግ አላማዬ ነው። ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን የበኩሌን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ። በመጨረሻም የሽልማቱን አዘጋጆች በርቱ ለማለት እወዳለሁ።

_______________


                   “ለሚጥሩ ሰዎች ሽልማት መስጠት መሰልጠን ነው”


             ኦቦንግ ሜቶ እባላለሁ። በጣና ሽልማት በበጐ አድራጐትና ሰብአዊነት ዘርፍ  አሸናፊ ስለሆንኩ ደስ ብሎኛል ። ሃገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ዘርና ፅንፈኝነትን ተፅይፈው ለአገራቸውና ለወገናቸው የሚጠቅም መረጃ የሚያጋሩ ወገኖችን ለመሸለም የተነሳውን ዘመራ መልቲ ሚዲያ ፕሮሞሽን አመሰግናለሁ።
ሰውነት ከዘር በላይ ነው፤ ሰብአዊነት ደግሞ ፈጣሪ የሚደሰትበት ተግባር ነው። በስለዚህ ሁላችንም በአንድነት በፍቅር፣በኢትዮጵያውነት ጥላ ስር ሆነን፤ ሰውነታችን  በበጎ ተግበር እንስራ እላለሁ።ያን ጊዜ ክፉ የሚያስቡ፣ አንድነትን የማይወዱ እየከሰሙ ይሄዳሉ። ዛሬ በዚህ ሽልማት የታጫችሁም… ሆነ የተሸለማችሁ ሁላችሁም  አሸናፊዎችና በጐዎች ናችሁና “እንኳን ደስ አላችሁ” ለማለት እወዳለሁ። ወደ ፊትም በጐ ተግባራችሁን መልካም ስራችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ እላለሁ።
ሽልማቱን የምታዘጋጁትም ብትሆኑ፣ ለአገር ሀሳቢ መሆናችሁን የሚያሳይ ስራ እየሰራችሁ ስለሆነ እናመሰግናለን።የዛሬው እውቅናና ሽልማት ፤ለቀጣይ ስራችን መንገድ ከፋች ነውና የሚያበረታታ ነው እጅግ እናመሰግናለን።

_____________________


             “ሽልማት አገኛለሁ ብዬ አልነበረም መረጃ ሳጋራ የቆየሁት”

            ደመቀ ከበደ በላይ እባላለሁ እንግዲህ ሰው እንደመሆኔ፣ ለሽልማት ስታጭ  ወይ አሸንፋለሁ ወይ እሸንፋለሁ በሚል፣ ሃምሳ ሃምሳ ሃሳብ ይዤ ነው።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የታደምኩት።በመሸለሜ ግን ደስተኛ ነኝ። እንደምታውቂው ማህበራዊ ትስስር ሚዲያ ላይ ረጅም ጊዜ ከቆዩት አንዱ ነኝ።ነገር ግን ስለ ጣና መጻፍ የጀመርኩት ገና ባህርዳር፣ እያለሁ “ከጣና ዳር” በሚል ነበር። ወደ አዲስ አበባ  ከተመለስኩኝ በሃላ የጤናን ጉዳይ ትኩረት አድርጌ እፅፍ ነበረ ።ያንን የማደርገው ወቅቱ የጤና ጉዳይ ጉዳይ የማይጠይቅና በተለይ የኮሮና  ወረርሽኝ ወቅት ስለሆነ እንደ ጋዜጠኛ ብዙ መረጃ የማግኘት እድልና አማራጭ ሰላለኝ፣ ለህብረተሰቡ እኔ በገባኝ ልክ ፈጣን እንዲሁም ግንዛቤን ሊያሰ የሚችሉ መረጃዎችን ከትክክለኛ ምንጮች እየወሰድኩ፣ ለማጋራት ጥረት ሳደርግ ነበር። በተለይ ኮሮና ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ከሆነበትም ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በምችለው አቅም ሁሉ እየጻፍኩኝ ነው።እውነት ለመናገር ስጽፍ የነበርው እሸለማለሁ ብዬ አይደለም። ከሽልማቱ በላይ እጅግ የሚያስደስተኝ ማህበረሰቡ ደመቀ “የሚያመጣቸው መረጃዎች ተዓማኒ ናቸው” በሚል የባህሪ ለውጥ ማምጣቱ  ነው።
ያ ለእኔ ትልቅ ሽልማት ነው። ማስጠንቀቂያዎች ወይም  ዜናዎች  አሊያም አዳዲስ ውሳኔዎች እርምጃዎቹ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን ለማጋራት እየተጋሁ ነበር “የኮሮና ጉዳይ” (ኮሮና ኢሹስ) በተሰኘው በዚህ የቡድን ገጾቻችን ላይ በቀን ቢያንስ ከ4-5 መረጃ እጽፋለሁ። ሰዎች ያንን መረጃ ተጠቅመው ግብረ መልስ ይሰጡናል። እኔ  ስለ ኮሮና በጣም የምፈው ሰው እንዲፈራውና እንዲጠነቀቅ ነበር ስለዚህ ብዙ ሰዎች  “ፈርተናል” ብለው መልስ ሲሰጡ ያስደስተኛል። ያ ጥረት ደግሞ በዚህ የሽልማት ድርጅት እውቅና ሲያገኝ ይበልጥ ያስደስታል።
በአሁኑ ሰዓት “SBS” በተሰኘው የአውስትራሊያ ሬዲዮ የኢትዮጵያ  ኮሮስፖንዳት ሆኜ እየሰራሁ ነው። ከመደበኛ ስራዬ  ጐን ለጐን፣ በማህበራዊ ሚዲያ  መፃፌን መረጃ ማጋራቴን በዚህ አጋጣሚ ዕውቅና የሰጡኝንና የሸለሙኝን አመሰግናለሁ።

______________________


                “የሽልማት ድርጅቱ በመንግስት ጭምር ሊደገፍ ይገባል”


            ሸጋው ማሬ ቢሻው እባላለሁ። የ29 ዓመት ወጣትና የጐንደር ዩንቨርስቲ “የኸልዝ ኢንፎማቲክ” ተማሪ ነኝ። ጣና ማህበራዊ ሽልማት ከተጀመረበት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በጤና መረጃ ዝርዝር በተከታታይ እጩ ነበርኩ አሁን በአራተኛው ዙር፣በጤና መረጃ ዘርፉ፣ጤና መረጃ  በተባው የፌስቡክ ገፄ፣በጤና ዙሪያ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ለማቀበል ተግቼ እሰራለሁ። የፌስቡክ ገፄን ወደ ዌብሳይት አሳድጌው፣ የተደራጀና የተጠናከረ የጤና መረጃ ለማቅረብ እቅድ አለኝ ።
ማህበራዊ ሚዲያን ወደ በጐተግባር  ማምጣት ይቻላል በሚል በጐ እሳቤ በበጐ ፍቃደኛ ወጣትና የዘመራ መልቲ ሚዲያና ፕሮሞሽን መስራች ደምስ አያሌው፣ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረ ሽልማት ነው። ሆኖም በጣም ብዙ ተግዳሮቶች እየተቋቋመ ነው ያለማቋረጥ እዚህ የደረሰው። ስለዚህ ይህ ሽልማት እንዲቀጥል በመንግስት ሳይቀር ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል ባይ ነኝ። የክልሉ ጤና ቢሮ እንኳን ገና ዘንድሮ ነው ድጋፍ ያደረገለት እንጂ ልጁ በግሉ እየኳተነ፣ የድርጅቶችን በር እንኳኳና ደጅ እየጠና ነበር የሚያዘጋጀው። እናም በደንብ ቢታገዝ ሽልማቱን ከዚህ በላቀ፣ ብዙዎችን ባሳተፈና በተጠናከረ መልኩ በመቀጠል ለውጥና ተፅኖ መፍጠር ይቻላል ብዬ አምናለሁ። የሽልማቱን አዘጋጆችና ድምጽ የሰጡኝን አመሰግናለሁ።

____________________


                  “የክብር ኒሻን ሽልማቱ ለአገራቸው ለተሰው ሁሉ መታሰቢያ ይሁንልኝ”

           ራሄል ቀለመወርቅ እባላለሁ። የዲያቆንና ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ ባለቤት ነኝ። በመጀመሪያ በዚህ ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ እንድንገኝ ጥሪ ላደረጉ የሽልማቱ አዘጋጆችና አስተባባሪዎች ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ። በጣም ደስ ብሎኛል።
እናንተም እንደምታውቁት፤ ይህንን ሽልማት በእጁ መቀበል የነበረበት ራሱ ካሳሁን ነበር (ለቅሶ…..) የሚገባው እሱ ነበር፤ ግን ፈጣሪ አልፈቀደም። ይህ ሽልማት ለቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ለአገራቸው ሲሉ በተለያየ መንገድ መስዋዕትነት ለከፈሉ፣ ልጆቻቸውን፣ ቤተሰባቸውን ጥለው ወጥተው የአገርና የሕዝብ ባለውለታዎች መታሰቢያ ይሁንልኝ። እንደሚታወቀው ካሳሁን ስለ ኢትዮጵያ የሚያቀነቅንበት፣ እንቅልፍ የሚያጣበት “አሻም” የሬድዮ ፕሮግራም የስሙ መጠሪያ ማስታወሻ ነው፤ ስለዚህ ለአሻም የሬድዮ ፕሮግራምና በድርጅቱ ስም መስዋዕትነት ለከፈሉት ኢትዮጵያውያን ይሁልንኝ እላለሁ።
ካሳሁን በሬድዮ ፕሮግራሙ ሁሌም የሚያወራው በአራቱም አቅጣጫ ስላለው የኢትዮጵያ ቅርስ፣ ትውፊትና ስለሃገር ሁለንተና ነው። ከካሳሁን የኢትዮጵያ ቅርሶች አንዱ ጣና ነው። ጣና በእምቦጭ መወረሩ በእጅጉ ይቆጨው ስለነበር፣ ባለው አቅም በእውቀትም በጉልበትም ለመታደግ በወጣበት ነው የቀረው። እና ጣና ከእንቦጭ አረም ነጻ ቢሆን ነፍሱ ደስ የምትሰኝ ይመስለኛል። በተረፈ ሽልማቱ በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ደስ ብሎኛል። የእሱን ስራ ለምትወዱ፣ ለምታደንቁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ። የሽልማት ድርጅቱ አስቦ ካሳሁን ይገባዋል ብሎ የክብር ኒሻን ስለ ሸለመው። እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ። ባለቤቴ እርበኛ ተብሏል እኔም የአርበኛ ባለቤት መባሌ ያስደስተኛል ልጆቼም ሲያድጉና ነፍስ እያወቁ ሲሄዱ የአርበኛ ልጅ መባላቸው የሚያኮራቸው ነው የሚሆነው። ስለዚህ ደስተኛ ነኝ። የኔ አርበኛ ነፍስህን፤ ይማረው እላለሁ።


Read 743 times