Saturday, 07 November 2020 13:29

በአንድ ጎጆ ተቃራኒ ፖለቲከኞች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ባል ሆዬ፤ ሪፐብሊካን ነው፡፡ (ኢህአዴግ ነው እንደሚባለው) የለየለት የትራምፕ ደጋፊ ነበር፡፡ ሚስት ደግሞ የትራምፕ ቀንደኛ ጠላት ናት፡፡ ትራምፕ ጎጆአቸውን በፖለቲካ ልዩነት ቢያምሰውም፤ ጥንዶቹ በአንድነት በሚያስተሳስራቸው  ተልዕኮ ላይ ተሰማርተዋል፡፡
ጆን ላውራ ሃንተር ለዓመታት የውሃ ጣቢያዎች በማቋቋም፣ በአሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበር፣ በህገ ወጥ መንገድ አቋርጠው የሚሻገሩ ስደተኞችን ከሞት ሲታደጉ ነው የኖሩት፤ በካሊፎርኒያ፣ የአንዙ በሬጐ  በረሃ ላይ ከሚከሰተው አደገኛ ሙቀት፡፡
 የ65 ዓመቱ አዛውንት ጆን፤ የዛሬ 21 ዓመት አትራፊ ያልሆነውን የውሃ ጣቢያ ቡድን የመሠረቱት፣   ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች፣በውህ እጦት በሚከሰት ድርቀትና በከፋ ሙቀት አቅላቸውን እየሣቱ መሞታቸው ተከትሎ ነው፡፡  
“እኔ እዚህ ነው የተወለድኩት። ታላቅ ነፃነትና ብዙ እድሎች ባሉበት አገር በመወለዴ ዕድለኛ ነኝ; የሚሉት የህክምና ባለሙያው፤ “ከደቡብ የሚመጡ ሰዎች የሚከተሉት የመንግስት ስርዓት፤የተለየ በመሆኑ የኛ ዓይነት እድሎች አይኖሯቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ እኔም እንደ እነሱ ብሆን፤ ወደ ሰሜን መምጣቴ አይቀርም ነበር” ብለዋል።
በሜክሲኮ የተወለደችው ባለቤታቸው ላወራ፤ የውሃ ጣቢያውን በበጎ ፍቃደኝነት የተቀላቀለች ሲሆን ከዓመታት በኋላም ከጆን ጋር በትዳር ቀለበት ተሳስረዋል።
“ሳገባት ዲሞክራት መሆኗን አልነገረችኝም ነበር። በድጋሚ ተታልያለሁ” ሲሉ ጆን ቀልደዋል፤ “ያኔ ስለ ፖለቲካ አናወራም ነበር፤ እዚህ እየመጣን ውሃ ብቻ ነበር የምንቀዳው”  
ከመቼውም የበለጠ ትዳራቸው የተፈተነው ዶናልድ ትራምፕ በ2016 የአሜሪካ ምርጫ፤ ህገ ወጥ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እርምጃ እንደሚወስድ ቀስቅሶ ካሸነፈ ወዲህ ነው። ይሄ በመካከላችን ጥቂት ቅራኔ ፈጥሮ ነበር፤ምክንያቱም ትራምፕን ስጠላው ለጉድ ነው፤ የሚሉት የ73 ዓመቷ ላውራ፤ሰዎችን የሚያወርድበት መንገድ ያስጠላኛል፤በተለይም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ  ድሆችን ” ይላሉ፡፡
 በ2016 ምርጫ ጆን፤ ለትራምፕ ድምጽ አልሰጡም ነበር፤ለምን ቢሉ? ባለቤታቸውን አክብረው፤ለትዳራቸው ቅድምያ ሰጥተው፡፡ የቀድሞ የሪያሊቲ ቲቪ ኮከብ፤ የተለመደው ዓይነት ፖለቲከኛ አለመሆናቸውን ግን አስደስቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
“ራሱን የሆነ ሰው ማግኘት አነቃቂ ነው፤ ምንም እንኳን እንደልቡ ቢናገርም” ብለዋል ጆን፡፡
የውሃ ጣቢያዎቹ የሚደግፉት ፖለቲካውን ወደ ጎን በመተው፣ የነፍሳቸውን ጥሪ በሚከተሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ በጎ ፍቃደኞችና ለጋሾች ነው ተብሏል።
“ሁሉም ሰው የራሱ ሃሳብ የማንጸባረቅ መብት አለው” ይላሉ፤ላውራ። “ሁላችንም ግን አንድ ዓላማ፣ አንድ ግብ ነው ያለን፤ ይኸውም በዚህ አካባቢ ከከፋ ሙቀት ጋር የተያያዙ ሞቶችን ቁጥር ለመቀነስ መትጋት ነው፡፡” የሚቀድመውም እሱ ነው፡፡


Read 1142 times