Sunday, 08 November 2020 00:00

“የመገንጠል ፖለቲካ መቆም አለበት”-

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

                                                                                   (አቶ ገብሩ አስራት፤ አንጋፋ ፖለቲከኛ)

           እንደ ዜጋ ሁለት ነገሮች በእጅጉ ያሳስቡኛል፡፡ አንዱ ጦርነት ነው፡፡ ጦርነት ሀገርን ያጠፋል፤ ዜጎችን ይበላል፡፡ ዝም ብሎ ጨዋታ አይደለም፡፡ በየትም አቅጣጫ ጦርነት ጎጂ ነው፡፡ አሁን ላይ የምንሰማው “ግፋ በለው” መልካም አይደለም። በትግራይ አስተዳደርና በፌደራሉ መካከል ያለው ጦርነት በፍጹም የሚበረታታ አይደለም። አሁንም ማዕከላዊ መንግስቱ ጉዳዩን በጥበብ ለመፍታት መሞከር ያለበት፡፡ በጦርነት ችግር ለመፍታት መሞከር መቋጫ አይኖረውም፡፡ ቅራኔዎችም እየተባባሱ ነው የሚሄዱት፡፡ ጦርነትን ማንም መደገፍ የለበትም። በጦርነት የሚመጣ ለውጥ  በዚህ ዘመን አይኖርም፡፡  ሁሉም አካል ይህን ሊገነዘበው ይገባል፡፡ በጦርነት የሚመጣ ዲሞክራሲ የለም። ወደ ጦርነት መግባት ማለት ሀገሪቱን ወደማትወጣው አዘቅት መክተት ማለት ነው። ሁለተኛው አሳሳቢ ጉዳይ፣ ይሄ በሃገራችን በየጊዜው እየተነሳ ያለው መገንጠል የሚለው ፖለቲካ ነው። ይሔ የመገንጠል ፖለቲካ ጨርሶ መቆም አለበት፡፡ በተለይ በትግራይ አካባቢ ያለው የመገንጠል እንቅስቃሴ መቆም አለበት። መገንጠል በየትኛውም መንገድ መፍትሄ አይሆንም። የተፈጠረው የፖለቲካ ችግር ነው። ይህ የፖለቲካ ችግር መፈታት ያለበት በጦርነት ሳይሆን በፖለቲካ ውይይት ነው።  ስለዚህ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ መነጋገርን ማስቀደም ያስፈልጋል፡፡
መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ያፈነገጡ ሃይሎች  ችግራቸው ምንድን ነው? ብሎ  መመርመር አለበት፡፡ የሃይል እርምጃ የሚቀጥል ከሆነ አያዋጣም፡፡ በቅድሚያ ችግሩ ምንድን ነው? የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ለመነጋገር ቅድሚያ መስጠት አለበት፡፡ የጦርነት መጨረሻውም ቢሆን፣ ብዙ እልቂት ተፈጥሮ ወደ መነጋገር ነው የሚገባው። አሊያም እልም ያለ መጠፋፋት ነው የሚያስከትለው፡፡ በዚህ ሁኔታ ምርጫውን ዘንድሮ መካሄድ የሚችል አይመስለኝም። የምርጫውን ጉዳይ  ቆም ብለን አይተን፣ የሃገሪቱ ህልውና የሚቀጥልበትን መንገድ ነው ማስቀደም ያለብን፡፡ በመላ ሀገሪቱ ፈጽሞ ሰላም እስካልሰፈነ ድረስ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሁሉም አካላት በሃገሪቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ ሊመሰክሩና ሊነጋገሩ ይገባቸዋል። ንግግር ሲባልም የእውነት መሆን አለበት። መጀመሪያ የጦር መሳሪያ ካነሱት ሃይሎች ጋር ነው መነጋገር የሚያስፈልገው፡፡ የውጭ አሸማጋይ አካላትም ተሳትፈውበት፤ እውነተኛ መፍትሄ መምጣት  አለበት። ጦርነቱ አያዋጣም፤ ሁሉም ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። አሁንም ለሃገሪቱ አጠቃላይ ችግር መፍትሄው እውነተኛ ውይይትና ድርድር ብቻ ነው፡፡ አስተዳደራዊ መፍትሄ ብቻውን ውጤት አያመጣም፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሄም ያስፈልጋል፡፡ ሁሌም በጦርነት የሚሞተው የተላከው እንጂ ላኪው አይደለም፡፡ በጦርነት አንድም ሰው መሞት የለበትም።  

Read 4689 times