Saturday, 07 November 2020 13:10

አገሩን የማያውቅ ሰው መሬት እየረገጠ መሬትን ይረግማል - የአፋር ተረት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 "ለወጣቱ፤ የመንግሥቱ ለማን ግጥም “መርፌ - ትሰራለህን” ማንበብና በዚያ አቅጣጫ መጓዝ የአባት ነው፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ! ወጣቱ በሥነ ምግባር ረገድ፣ የሰውን ፀባይና ችሎታ በሚመረምር መልኩ አዕምሮው መታነፅ አለበት፡፡ ዕውቀትን መሰረት ሳያደርግ ለትግል ብቻ ብናዘጋጀው፣ የፕሮፓጋንዳ ወይም የአጀንዳ ማስተላለፊያ አሸንዳ ቱቦ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ በታሪክም የታየ ነው፡፡"
የሚከተለውን የፃፉልን እጓለ ገብረ ዮሐንስ ናቸው፡፡
“የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ነው፡፡
 በግሪክ ሜቶሎጂ የሚገኝ አንድ ትልቅ ተረት አለ፡፡
(ይህም ስለ ፕሮሚሴቭስ የሚነገረው ነው፡፡ ትልቅ ምሥጢር በውስጡ ደብቆአል፡፡ ፕሮሚሴቭስ በሚል አርእስት የቀድሞውን ተረት መሠረት በማድረግ፣ ኤስሂሎስ የሚባለው ትራጀዲን የፈጠረ ባለቅኔ፣ አንድ ትሪሎጂ - ማለት ሦስት ድራማዎች ጽፎአል፡፡ እሱን በመከተል ሸሊ ባይረን ጌቴ ጽፈዋል፡፡ የፕሮሚሴቭስ መንፈስ በአውሮፓ የመንፈስ ታሪክ ውስጥ መካከለኛውን መሥመር የያዘ ነው፡፡ አሁን የጠቀስናቸው ሰዎች በአውሮፓ የሥነ ጽሑፍ ጠፈር ላይ በጣም ጐልተው የሚታዩ ከዋክብት ናቸው፡፡)
የፕሮሚሴቭስ ተረት እንደሚቀጥለው ነው፡፡ ፕሮሚሴቭስ በከፊል አምላክ፣ በከፊል ሰው የሆነ ሕላዌ ነበር፡፡ በከፊል አምላክ እንደመሆኑ ዐሥራ ሁለቱ የግሪክ አማልክት በኦሉምቦስ ተራራ ሆነው ስለ ሰውና ስለ ዓለም አስተዳደር ሲመክሩ ይሰማ ነበር፡፡ በከፊል ሰው እንደመሆኑ የሰው ሥቃይና መከራ በጣም ያሳዝነው፣ ይጸጽተው ነበር፡፡ ሰው ቤት ንብረት ሳይኖረው በበረሃ፣ በጫካ፣ በዱር፣ በገደል፣ በዋሻ፣ በቁር፣ በሀሩር እንዲኖር ተፈርዶበት ነበር፡፡ ይህ መሆኑ አማልክት መክረው ዘክረው፣ ለሰው የዕውቀት ምንጭ የሆነውን ብርሃንን የሰጡት እንደሆን ከዕለታት ባንድ ቀን ሰጭነታቸውን ክዶ፣ በነሱ ላይ በመነሳት የሚያምፅ መሆኑን በመረዳት፣ ብርሃንን ከሰዎች ደብቀው ከማይደርሱበት ቦታ በመሠወራቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች በጭለማና የርሱ ተከታይ በሆኑት ችግሮች ሥር ሲሰቃዩ ይኖራሉ፡፡
ይህ የሰዎች መራራ ዕድል ወገናቸው በሚሆን በፕሮሚሴቭስ ላይ ርህራሄ አሳድሮበት፣ ብርሃንን አማልክት አርቀው ከደበቁበት ሰርቆ ለሰዎች ወስዶ ሰጠ፡፡ ያን ጊዜ ማናቸውም ነገር ግልጽ ሆኖ ታያቸው። በብርሃን ምክንያት ጥበብና ማናቸውም የዕውቀት ስልት ስለተገለጸላቸው፣ ራሳቸውን ከገዛ ራሳቸው በተገኘው ዘዴ ለማስተዳደር ጀመሩ፡፡
ፕሮሚሴቭስን ግን ለሰዎች ብርሃንን ሰጥቶ፣ በጐ በመሥራቱ አማልክት ቀንተው፣ በብርቱ ስቃይ ይቀጣ ዘንድ አዳኝ ከማይደርስበት ገደል ላይ ከቋጥኝ ድንጋይ ጋር በሰንሰለት ተቆራኝቶ፣ አሞራ ለዘለዓለም እንዲበተብተው ፈረዱበት፡፡
*   *   *
ከፕሮሚሴቭስ ዕጣ -ፈንታ ይሰውረን፡፡ ይህ ፕሮሚሴቭስ የሰውን ዕድል ለማሻሻል የሚታገሉት የዕውቀት ሰዎች፣ የመምህራንና የሊቃውንት ምሳሌ ነው፡፡ እሱ ብርሃንን አማልክት ከደበቁበት ቦታ ወስዶ ለሰው እንዳበረከተ ፣ የዕውቀት ሰዎችም ዕውቀት በመለኮታዊ ምሥጢርነት ከሰው ተደብቃ ስትኖር ሳለ በብዙ ትግል አግኝተው፣ ከገዛ ራሳቸው አሥርፀው የወገኖቻቸውን ዕድል ለማሻሻል ያበረክታሉ፡፡ ዋጋቸውም ሌላ ሳይሆን ስቃይ መከራ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሶክራቲስ በመርዝ ተገድሎአል፡፡ ጆርዳኖ ብሩኖ የጧፍ ቀሚስ ተጐናጽፎ በእሳት ተቃጥሎአል፡፡
እነዚህ ሰዎች እንደ ጧፍ መብራት ማለት ናቸው፡፡ ራሳቸው ነደው ተቃጥለው ያልቃሉ። ለሌሎች ግን ብርሃን ይሰጣሉ፡፡ የፕሮሜሴቭስ ምሳሌ አንድ ትልቅ ሕግ ጉልህ አድርጐ ያሳያል። ይህም “ዕውቀት በሥቃይ የሚገኝ ነው” (Learn through suffering) የሚል ነው፡፡
ልጆቻችንን ይህን ለሌሎች ስንል መታገል፣ መስዋዕት  ማድረግ እንደምን እናስተምር? ብርሃን የሚያመጡ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ዕውቀትን ለሀገር ለማጎናፀፍ የሚጥሩ መምህራን ያሹናል፡፡ የዕውቀት ብርሃን ለመጪው ትውልድ ታትሮ ለማስተላለፍ፣  ልብና ልቡና ይፈልጋል፡፡ አረፍ ብሎ ወዴት እያመራን ነው ብሎ መጠየቅን ግድ ይላል፡፡ ዕውቀት ከትምህርት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ከኑሮአችን፣ ከልምዳችን፣ ከትግላችን እንጂ፡፡ ይህ ወረድ ብሎ አፈሩን መዳሰስን፣ ህዝቡን ማግኘትን፣ የልብ ትርታውን ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ምን ጎደለው? ስለዚህ ጉዳይ ግንዛቤ አለ ወይ? በምን ዓይነት መንገድ የጎደለውን ዕውቀት ለማሟላት እችላለሁ? ማለትን ይጠይቃል፡፡ መንገዱን ካገኙ በኋላም፤ ጧት ማታ ሳይታክቱ መታተርን ይጠይቃል፡፡ ይህን ከልብ ካደረግን አገር መውደድ ገብቶናል፡፡ ያንድ ሰሞን ሞቅ ሞቅ ብቻ አገርን ከገባችበት ማጥ አያወጣትም፡፡ “ኦሆ በሀሊ፣ ያርጓጅ አናጓጅ፣ በደመቀበት ቦታ ሁሉ የሚያጨበጭብ አንድም የተለየ ነገር ለማስገኘት አይችልም” ይላሉ ዶክተር እጓለ፡፡ ሉቃስን በመጥቀስም እንዲህ ይሉናል፡- “ውሰብአ አቴናሰ ወእለ ይነግድ ኲሎሙ ህየ በእደ ትካዘ አልቦሙ ዘእንበለ ዳእሙ ለአፅምኦ ወነቢብ ዘሐዲስ”። አቴናውያን አዲስ ነገር ከመስማት ወይም ከመናገር በስተቀር ሌላ ምኞት አልነበራቸውም። ባለው ላይ ቆሞ አዲስ ነገር ለማግኘት የሚጣጣር ሰው ሁል ጊዜ ወደፊት ይሄዳል - ማለት ነው፡፡
እንደ አቴናውያን፤ በአለው ላይ ቆመን አዲስ ነገር ለማግኘት የምንጣጣር ከሆነ ወደፊት እንሄዳለን። ትምህርትንና ዕውቀትን መሰረቱ ያደረገ ትውልድ ከፈጠርን የራሱን ጥያቄ፣ የራሱን ነገ ራሱ ይወልዳል። የሚኖርበት ቤት ሲጠበው ቤቱን ራሱ አስፋፍቶ ይሰራዋል፡፡ ሁሉን እኛ እናድርግልህ ካልነው - ሁሉን ቀላቢ እንሁንለት ካልን፤ ዞሮ ዞሮ ተቀላቢ ትውልድ ነው የምናፈራው፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት - Spoon – Feeding mentality ይጠቀልለዋል - የአጉሩሱኝ አስተሳሰብ እንደማለት ነው፡፡
ለወጣቱ፤ የመንግሥቱ ለማን ግጥም “መርፌ - ትሰራለህን” ማንበብና በዚያ አቅጣጫ መጓዝ የአባት ነው፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ! ወጣቱ በሥነ ምግባር ረገድ፣ የሰውን ፀባይና ችሎታ በሚመረምር መልኩ አዕምሮው መታነፅ አለበት፡፡ ዕውቀትን መሰረት ሳያደርግ ለትግል ብቻ ብናዘጋጀው፣ የፕሮፓጋንዳ ወይም የአጀንዳ ማስተላለፊያ አሸንዳ ቱቦ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ በታሪክም የታየ ነው፡፡ በማህበራዊ ኑሮው የእያንዳንዱ መብትና ተግባር የሚጠበቅበት፣ “ሰው በንፁህ ተምኔቱ መሰረት በሰላም ተደስቶ የሚገኝበትን ሕግ” ይዞ መጓዝ እንዳለበት ሊረዳ ይገባል፡፡ ህይወት እንደ ጂኦሜትሪ ትምህርት በቀጥታ መሥመር የተሞላና የተለካ አይደለም። ቀላል ሂሳብም አይደለም። እንዴት እንደሚገነባ፣ ከራሱ ህይወት ተነስቶ እንዴት ለማደግ እንደሚችል፣ ትምህርትን ባሰላሰለ መልኩ ማጤን እንጂ “ሳይገሉ ጎፈሬ፣ ሳያረጋግጡ ወሬ” መሆን የለበትም፡፡ እስከ ዛሬ አጭር ተመልካች፣ አጭር ተጓዥ ሳናደርገው (Myopic) አልቀረንም፡፡ አጭር ግቦች አጭር ያደርጉናል!
አንድ ደራሲ እንደሚለው፤
“…የውጪ ጉዳዮችን ካገር ውስጥ ኃይሎች አሰላለፍ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከጥበብ ሽግግርና ከውጪ ርዳታ፣ የቋንቋ መዘበራረቅና ጉራማይሌነትን ከባህላዊ ድቀት፣ የሐሳብ ነፃነትን ከጋዜጣ፣ ራዲዮና አጠቃላይ ውይይት ምህዳር መጥበብ ጋር…” የሚያነፃፅር ወጣትም ሆነ አዋቂ ያስፈልገናል፡፡
ወጣቱ አገሩን ያውቅ ዘንድ ጥልቅ አስተሳሰብ፣ ረዥም ርዕይና በግብረገብ የታነፀ ድፍረትና መስዋዕትነት ያስፈልገዋል፡፡ የሀገራዊነት፣ የወገን አሳቢነት፣ የኢ-ራስ - ወዳድነት፣ የሁሉን - አውድም አስተሳሰብ አለመያዝ፣ ሁሉን - ረጋሚ ያለመሆን አመለካከት፣ ኢ-ፅንፋዊነት ወዘተ እንደ መርህም፣ እንደ ኑሮም ሊሰርፁበት ይገባል። አለበለዚያ አፋሮች እንደሚሉት፤ “አገሩን የማያውቅ ሰው፣ መሬትን እየረገጠ መሬትን ይረግማል” ይሆናል፡፡   

Read 12918 times