Saturday, 31 October 2020 12:07

የኮቪድ 19 ጦስ - ከሆስቴል ወደ ድንኳን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአሜሪካ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ፣ ከሞቀ ቤታቸው እየወጡ፣ ጎዳና አዳሪ የሚሆኑ ዜጎች ቁጥር በየጊዜው እያሻቀበ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ምክንያቱ ደግሞ ከሥራቸው እየተባረሩ፣ ለቤት ኪራይ የሚከፍሉት ገንዘብ በማጣታቸው ነው ተብሏል፡፡
 የ34 ዓመቷ ሜሊሳ ኖርማን፣ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ከገጠማቸው አሜሪካውያን አንዷ ናት፡፡  ከምትኖርበት ሆስቴል ወጥታ በቶርኩዌይ ዴቮን አቅራቢያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ድንኳን ተክላ ለመኖር የተገደደችው፣ ለቤት ኪራይ የምትከፍለው ገንዘብ በማጣቷ ነው፡፡
ለአካባቢው አስተዳደር ጎዳና ልትወጣ መሆኑን ማሳወቋን የጠቆመችው ኖርማን፤ ሆኖም የጊዜያዊ መኖሪያ ቤት ፍላጐት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ሳቢያ፣ ከዓመት በፊት ቤት እንደማታገኝ እንደነገሯት ገልጻለች፡፡  
 “ወደ ሆስቴሉ የገባሁት አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች በኮቪድ-19 ሳቢያ ከመዘጋታቸው በፊት ነበር። ከዚያም በወረርሽኙ ሳቢያ የምሰራበት ማክዶናልድ መዘጋቱን ተከትሎ፣ ሥራዬን በማጣቴ፣ የሆስቴሉን ኪራይ እየከፈልኩ መቀጠል አልቻልኩም፡፡” ትላለች፤ ኖርማን።
በማከልም፤ “በድንኳን ውስጥ መኖር ከጀመርኩ ከሳምንት በላይ ሆኖኛል። አስተዳደሩ በተራ ጠባቂ ዝርዝር ውስጥ መሆኔን ነግሮኛል፤ ግን ቤት ለማግኘት እስከ አንድ ዓመት ድረስ ይወስዳል።; ብላለች፡፡
“ቅዝቃዜው እያየለ መጥቷል፤ እስካሁን የክረምት ድጋፍ አልተደረገልንም፡፡ ለወትሮው የመስክ መኝታ (ስሊፒንግ ባግ) እንደ ግላስቶንበሪ ከመሳሰሉ ፌስቲቫሎች እናገኝ ነበር፤ ዘንድሮ ግን ፌስቲቫሎች በመሰረዛቸው ምንም አላገኘንም፡፡"
"ከ16 ዓመቴ ጀምሮ ከሥራ አልተለየሁም፤ ያልከፈልኩት ግብርም የለም፡፡ ይሄ የሚያሳምም ነገር ነው" ስትልም ኖርማን ተናግራለች - እኒህን ሁሉ ዓመታት ሰርታ ጎዳና መውጣቷ እንደሚያበግናት በመግለጽ።
“ጎዳና ልትወጣ ስትል ለቶርባይ አስተዳደር የምትደውልበት ቁጥር አላቸው፤ ነገር ግን አንድ ሰው ጎዳና መውጣትህን እስኪያረጋግጥልህ ድረስ መደወሉ ለውጥ አያመጣም፤ እናም በዚህ መሃል ያ ሰው ጎዳና  ወጥቶ ያርፈዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ አይገኝም፡፡” በማለትም ታስረዳለች፤ ሜሊሳ ኖርማን፡፡  
የአስተዳደሩ ሃላፊ ክርስቲን ካርተር በበኩላቸው፤ “እንደ አብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ በተባባሰው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ፣ በአማራጭ የመኖሪያ ቤቶች አገልግሎታችን ፍላጎት ረገድ፣ ከፍተኛ መጨመር እያየን ሲሆን ቡድናችን ጊዜያዊ ማረፊያዎችን ለሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ ለማቅረብ በርትቶ እየሰራ ነው::” ብለዋል::    
የኮቪድ 19 ጦስ ብዙ ነው፡፡ በቫይረሱ መያዝ ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡ ከሥራ ገበታ ያፈናቅላል፡፡ ገቢ አሳጥቶም ተደጓሚ ያደርጋል፡፡ ከሞቀ መኖሪያ ቤት አስወጥቶ፣ ለጎዳና ኑሮም ይዳርጋል፡፡  አያድርስ ነው!


Read 1451 times