Sunday, 25 October 2020 18:55

ኮሚሽኑ ለእርቀ ሠላም ወሳኝ የሆኑ 21 ግጭቶችን እያጠናሁ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የትግራይና ፌደራል መንግስትን ለማስታረቅ አሁንም ጥረት ይደረጋል”

            በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግርግሮችና የሠላም መጥፋት በእንቅስቃሴው ላይ እንቅፋት እንደሆነበት የገለፀው የብሔራዊ እርቀ ሠላም ኮሚሽን፤ ለእርቀ ሠላም ጠቃሚ ናቸው የተባሉ በሀገሪቱ የተከሰተ 21 ግጭቶችን እያጠና መሆኑን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ከትናንት በስቲያ ባለፉት ጊዜያት ሲያከናውን በነበረውና በቀጣይ ሊያከናውን ባቀዳቸው የእርቀ ሠላም ጉዳዮች ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሀገሪቱ ግጭቶችን የመለየት ስራ መሠራቱንና ግጭቶቹን እንዴት መፍታት ይቻላል፣ መንስኤዎቹና ያስከተሉት ጉዳትስ ምንድን ነው? የሚለውን እያጠና መሆኑን ነው የገለፀው፡፡
በሀገሪቱ የተከሰቱ ጠንካራ የተባሉ 21 ግጭቶች መለያታቸውንና ከእነዚህ ግጭቶች መካከል የተወሰኑት አሁንም መልሰው መላልሰው የሚፈጠሩ የግጭት ክስተቶችን እያስተናገዱ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ እነዚህ ለእርቅ ሠላም ወሳኝ ናቸው በተባሉ ግጭቶች ዙሪያም በአንድ ወር ጊዜ ወስጥ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ምክክር እንደሚደረግባቸውም ተገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ በሀገሪቱ የእርቅ ሠላም ስራ በሚያከናውንበት ሁኔታ ዙሪያ ከመንግስት አካላት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሴቶችና ወጣቶች ጋር እየመከረ መቆየቱንም አስታውቋል፡፡
በእነዚህ ምክክሮች ወቅትም በተለይ ከወጣቶች ጋር በተደረጉ ውይይቶች፣ የኢትዮጵያ አስታራቂ ወጣቶች ፎረምን ማቋቋም መቻሉንና የኢትዮጵያ ሴት በጐ ፈቃደኞች የእርቅ መድረክንም ለማቋቋም ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተገልጿል፡፡
በመግለጫው ወቅት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው አለመግባባት ሲሆን ኮሚሽኑ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ የትግራይ ክልል አመራሮች ቅድመ ሁኔታዎችን በማቅረባቸው፣ እስካሁን ቅድመ ጥረቱ እንዳልሠመረ ተመልክቷል፡፡
የኮሚሽኑ ኃላፊነት ሁለቱ አካላት ተቀራርበው እንዲወያዩ መድረክ ከማመቻቸት የዘለለ አለመሆኑን የጠቆሙት የኮሚሽኑ አመራሮች፤ ሁለቱ አካላት አሁንም ለውይይት ፈቃደኛ ከሆኑ አቀራርቦ ለማስታረቅ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ለእርቅ ሠላም ስራዎች እንቅፋት የሆኑ አለመረጋጋትና የሠላም እጦትን በተመለከተም መንግስት ኃላፊነቱን በመወጣት፣ መረጋጋትና ሠላምን ሊያሰፍን ይገባል ብሏል - ኮሚሽኑ፡፡ 

Read 9440 times