Wednesday, 28 October 2020 00:00

የከሸፈው ውርርድ! - (ወግ)

Written by  ተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(0 votes)

 ጊዜው ማለዳ ነው። እኔና ጋሽ ብሬ የሰፈር ከብቶች ከየበረቱ ተሰባስበው ወጥተው ወደ ግጦሽ ከመሄዳቸው በፊት የሚገናኙበት ዳሪሙ ሜዳ ተገናኝተን እያወራን ነው። እሱ የሚያግዳቸው የአራዳ ሰፈር ከብቶች ብቻቸውን ወደ ኩቾ መጓዛቸውን ቀጥለዋል፡፡ እኔ የሰፈሬን ከብቶች ለመንዳት የአባባ ዲላ ከብቶች እስኪመጡ እየጠበኩ ነው፡፡
“ዛሬ፤ ከኔ (የስደተኛ ሰፈር) በሬዎችና ካንተ (የአራዳ ሰፈር በሬዎች) ማንና ማን የሚጋጠሙ ይመስልሃል?” አልኩት።
“ምን ይላል ይሄ ...! ኃይሌ መውዜሩን እቀልብ መሰለህ እንዴ! እኔ መጪውን በምን አውቃለሁ?” አለኝ። ኃይሌ የሰፈሩ ጠንቋይ ናቸው፤ ጎፈሬያም።
ጋሽ ብሬ ቀጠለ። “የበሬ ልብኮ ሌሊቱን ሞልቶ ነው የሚያድረው። ትናንት የተሸነፈ በሬ ዛሬ እንደ አዲስ ይገጥማል። ማንና ማን እንደሚጋጠምማ ለማወቅ አይቻልም” አለኝ በዱላው መሬቱን እየጠቀጠቀ።
“ለምሳሌ የመቶ አለቃ ተበጀ አይጥማው (መካከለኛ ቁመና እና ቀንደ ረዥም) እና የአባባ ዲላ ዲዶ ጆሮ (ግዙፍ፣ ቀንዱ አጭር በሬ) ቢጋጠሙ የትኛው የሚያሸንፍ ይመስልሃል?”
“እንደሱ በለኛ!” አለ ጋሽ ብሬ። አይበለውና ሁለቱ ከተጋጠሙ የሚያሸንፈው የመቶ አለቃ ተበጀ በሬ ነው።” ኮሾ ሲጋራውን ልምጥጥ አድርጎ ሳበ።
“እሱ አያሸንፍም፤ “እንወራረድ” አልኩት!
“አህያ እንረድ፤ እኔ ጠባሽ አንተ ቀማሽ” ብሎ መልስ ሰጠኝ።
መቼም ጋሽ ብሬ ልጆችን ማጫወት ይችልበታል። ከኔ ጋር መጫወትማ ነፍሱ ነው። የደብተሬን መለበጃ (ጆርናሌ) ወረቀት ሳይቀር ቀድጄ ለትምባሆ መጠቅለያ ስለምሰጠው ይደሰትብኝ ነበር። “አንተ ለሰው አሳቢ ልጅ ነህ። ታያለህ፤ ትልቅ ቦታ ትደርሳለህ” ይለኛል ሲያሞግሰኝ።
“እና ማን ያሸንፋል ነው የምትል?” አለኝ።
“የሚያሸንፈው የአባባ ዲላ ጆሮ ነው” አልኩት።
“አያሸነፍም፤ አበደን! እርም!” በግማሽ ጆርናሌ (የጋዜጣ ወረቀት) እንወራረድ።
እንዴት ልትል ቻልክ?
“እንዴት?  ማለት ጥሩ ነው” አለኝ ጋሽ ብሬ። “እንዴት መሰለህ? ጆሮ ከትናንት ወዲያ ለአውድማ መለቅለቂያ የሚሆን ውሃ ከስደተኛ ወንዝ በበርሜል ሲያመላልስ (ሲጎትት) ነው የዋለው። ደግሞ ከማን ጋር መሰለህ? ከዚያ ከአቶ ሰውላገሩ ዳተኛ ከላድማ በሬ ጋር። አስበው እስቲ ያንን ቀጥ ያለ ዳገት ከአጉል በሬ ጋር እየተጓተተ ሲስብ። ትናንት ደግሞ እስከ ማታ ድረስ ጤፍ ውቂያ ላይ ነው የዋለው። የመቶ አለቃ በሬ ግን ቀን ሳሩን፣ ማታ ማታ የአረቄ አተላውን እየጋፈ እርፍ ብሎ ነው ውሎ ያደረው - ሁለቱንም ቀን። ስለዚህ ሁለቱ ከተጋጠሙ የሚያሸንፈው የእሳቸው በሬ ነው።”
“እንደኔ ግን የሚያሸንፈው ጆሮ ነው” አልኩት። ቀጥዬም፤ “ለምን መሰለህ? ጆሮ የአይጥማውን የውጊያ ስልት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠና መጥቷል። ባለፈው ሳምንት ሲዋጉ በግኛን ነበር የሞከረው የዛሬ ሶስት ቀን ሲጋጠሙ ግን ደፈቃንና በግኛን እያቀላቀለ ነበር። ይህ ተጨማሪ ስልት በጣም ጠቅሞታል” ብዬ ምክንያቴን አብራራሁለት።
“እንዲያውም ተወው ...!” ዛሬ ሁለቱ መጋጠም የለባቸውም” አለ ጋሽ ብሬ። “ግፍ ነው! ግፍ ነው! አይሆንም፤ ውጤታቸው ይዛባል። እንዲጋጠሙ አልፈቅድላቸውም” ብሎ ቁጭ ካለበት ሳር ላይ ዱላውን ተመርኩዞ ተነሳ።
እኔና ጋሽ ብሬ ቆመን እያወራን እያለ አንድ የጎረቤታችን ልጅ ከአባቴ የተላከ መልዕክት ነገረኝ። “ጋሼ፤ ጋሽ ብሬ መጥቶ ከሆነ ከብቶቹን አስረክበውና ከቤት ዘንቢልና ሁለት ብር ይዘህ አድባሩ ድረስ ና ብሎሃል” አለኝ።
“የምን ዘንቢል?” አልኩት ልጁን።
ልጁ ስለኔና ስለ ጋሽ ብሬ ውርርድ የሚያውቀው ነገር ስላልነበረ እንደዋዛ እንዲህ አለኝ “ለቅርጫ ስጋ መውሰጃ ነው። ... የአባባ ዲላ ጆሮ የሚባለው በሬ ታርዷል። ሌሊቱን የሰው ማሳ ውስጥ ገብቶ በቆሎ ሲበላ አድሮ ሆዱ ተቀብትቶ ሊሞት ሲያጣጥር ነው የባረኩት አሉ” ብሎኝ ሄደ። ክው አልኩ። ምክንያቱም የሰፈራችን ከብቶች ከሌላ ሰፈር ከብቶች ጋር ሲጋጠሙ የሚያስከብርልን ጆሮ ነበር። አይ ጆሮ አልኩ… እንባም ሰረሰረኝ።
ጋሽ ብሬ፤  “አዪ! ውርርዳችን ከሰረ!” አለና ሳቀ። መሳቁን አልወደድኩለትም፡፡ የሞተውኮ የኔ ቡድን ወኪል ነው፡፡ ታዲያ እንዴት በኔ ሀዘን ይስቃል? ጭንቅላቱ በሳቅና በሳል ሲግል ወዝ የጠገበ ባርኔጣውን አውልቆ በማጎንበስ ከቀይም ወደ ነጭ ከሚያደላ ልሙጥ በራ ራሱ ላይ ላቡን በእጁ መዳፍ እየጠረገ ሳር ላይ ማንጠባጠብ ያዘ፤ ጋሽ ብሬ። ልክ ነፍሱ መለስ ስትልለት፣ በሳቅ ድምጸት “በቃ ክርክራችን ተቋርጧል፤ ወደየ ጉዳያችን”  ብሎ ርቀው የሄዱ ከብቶቹን ለመከተል ካፖርቱን እያርገፈገፈ ሮጠ። “ደህና ዋል” ብዬ እጄን ለጀርባው አውለብልቤ ሳበቃ፣ እየሮጥኩ ወደ ቤት ሄድኩ።
የሮጥኩት የታረደው በሬ ፊኛ እንዳያመልጠኝ ነው። የትልቅ በሬ ፊኛ በእርጥቡ ሲለፋ እና ሲነፋ ትልቅ የእግር ኳስ መጫወቻ ይወጣዋል። ህይወት ይቀጥላል!
ማስታወሻ - ከበሬዎች ውጊያ መጽሀፌ አንደኛው ምዕራፍ ነው

Read 1621 times