Monday, 26 October 2020 00:00

ኖኪያ ጨረቃ ላይ የሞባይል ኔትወርክ ሊዘረጋ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ታዋቂው የሞባይል ስልኮች አምራችና የኔትወርክ ዝርጋታ ኩባንያ ኖኪያ፤ ከሁለት አመታት በኋላ ጨረቃ ላይ የመጀመሪያውን የሞባይል ኔትወርክ ሊዘረጋ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ እ.ኤ.አ እስከ 2024 ሰዎችን ወደ ጨረቃ ለመላክና ለተራዘመ ጊዜ እንዲቆዩ ለማድረግ የያዘው አርቴሚስ ፕሮግራም አካል የሆነውን ይህን የሞባይል ኔትወርክ ዝርጋታ ለማከናወን በርካታ ኩባንያዎች ቢወዳደሩም፣ ኖኪያ በአሸናፊነት መመረጡ ባለፈው ሰኞ ይፋ መደረጉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኖኪያ በአለማችን ታሪክ የመጀመሪያው የሆነውን የጠፈር የሞባይል ኔትወርክ ዝርጋታ እ.ኤ.አ እስከ 2022 መጨረሻ ድረስ ያጠናቅቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ኔትወርኩ 4ጂ/ኤልቲኢ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርና በሂደት ወደ 5ጂ እንደሚያድግም ገልጧል፡፡
የተለያዩ የአየር ንብረቶችን ተቋቁሞ የጠፈር ተመራማሪዎች፣ በድምጽና በምስል ግንኙነት እንዲያደርጉ ያስችላል ለተባለው ታሪካዊ የሞባይል ኔትወርክ ግንባታ የሚውሉ ቁሳቁሶችን፣ ወደ ጨረቃ የማጓጓዙን ስራ የሚያከናውነው፣ ተቀማጭነቱ በቴክሳስ የሆነው ኢንቲዩቲቭ ማሽንስ የተሰኘ የግል ኩባንያ መሆኑንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 4498 times