Sunday, 25 October 2020 15:39

“ለእኔ ብላክ ሌብል፣ ለእሱ ጠቆር ያለ ቡና...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 "እኛን በተመለከተ “እውነት እኮ ዓለም ባንኩም፣ አይኤምኤፉም፣ ለጋሹም፣ አበዳሪውም ሁሉ---ለካይሮ እየወገነ፣ ይቺን ምስኪን ሀገር ሲበድል ኖሯል...” የሚል ፖለቲከኛ፤ ኦቫል ኦፊስ አጠገብ ይደርሳል ብሎ ማሰብ አሪፍ ነገር አይደለም፡፡ ውገናው በትረምፕ ዘመን አልተጀመረም፣ እሳቸው ሲሄዱም አያበቃም፡፡ ይሄ ነው የዛች ሀገር ፖለቲካ--"
                         እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስማ ወዳጄ... አሁን አንተ ትረምፕ ተመረጡ ባይደን ምን ቤት ነህ! ኸረ እባክሀ በገዛ ጓዳህ “እየኝ፣ እየኝ፣” የሚል መአት ጉድ አለ! የምን “ከዲሲ ይነጥለኝ!” አይነት መሀላ ነው! (ቂ...ቂ..ቂ...) በነገራችን ላይ ዲቪ ስትሞላ የዘንድሮው ስንተኛ መሆኑ ነው?! አሀ...‘እውቅና’ ሊሠጥህ ይገባላ! 
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አንዳንዶቻችን “እንደው ይሄን ትረምፕ የሚሉትን ሰውዬ ወደዛ በፈነገሉት!” እያልን ነው፡፡ ለነገሩ አል ሲሲን “ማይ ሊትል ዲክቴተር ምናምን እያለ እያሽሞነሞነማ፣ ለሌላ አራት ዓመት ሁዋይት ሀውስ መክረም የለበትም፡፡ አራት ነጥብ!” ከወደ ዋሽንግተን ለሚጠይቀን፣  መልሳችን ይሄ ይሆን ነበር ለማለት ነው፡፡ ግን እኮ...አለ አይደል... #አስተዳደሩ ቢለወጥ እኛን ይጠቅመናል፣ የሚቀጥለው አስተዳደር ለካይሮ አይወግንም; ምናምን ይመስለናል አንጂ የ‘አማሪካን’ ፖለቲካ እንደዚህ አይደለም፡፡ እኛን በተመለከተ “እውነት እኮ ዓለም ባንኩም፣ አይኤምኤፉም፣ ለጋሹም፣ አበዳሪውም ሁሉ---ለካይሮ እየወገነ፣ ይቺን ምስኪን ሀገር ሲበድል ኖሯል...” የሚል ፖለቲከኛ፤ ኦቫል ኦፊስ አጠገብ ይደርሳል ብሎ ማሰብ አሪፍ ነገር አይደለም፡፡ ውገናው በትረምፕ ዘመን አልተጀመረም፣ እሳቸው ሲሄዱም አያበቃም፡፡ ይሄ ነው የዛች ሀገር ፖለቲካ!
እኔ የምለው....የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ...ኦባማ በእነሱ 2008 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመረጡ እኮ፤ አዲስ አበባ ቀጫጭን ሀበሻ ‘በደስታ’ ሲደንስ ነበር ያደረው! እሳቸው አይደለም እዚህ ግባ የሚባል ነገር ሊያደርጉልን፣ ጭራሽ የመጡ ጊዜ ጀርባችን ላይ እንትን እየተደገነብን፣ በየህንጻው ግድግዳ፣ በደረታችን ስንለጠፍ አልነበር እንዴ የከረምነው! ምድረ ‘ማሪን’ በሄሊኮፕተር ያረጁ የመብራት ሀይል ምሰሶዎችን ሊነኩ ምንም ሳይቀራቸው፣ በአናታችን ላይ ሲመላለሱ አልነበር እንዴ...ያውም ቁልቁል ደግነወብን! የምር ግን... ስንት ሀገር እንዲህ እንደሚደረግ እግዜር ይወቀው! (እንትናዬ... ያን ጊዜ ስታዲየም አካባቢ በነበረ ህንጻ ግድግዳ ላይ ተለጥፈህ፣ ;ስፍራውን ሳይለቅ አልቀረም# ያልከው የጎድን አጥንት፣ ቦታው ተመለሰ እንዴ?!) እና የ‘አማሪካን’ ምርጫ ያሳሰበህ ወዳጄ...“በእኔ ምርጫ ምን ይኮነስርሀል የማለት መብትሀ እንደተጠበቀ መሆኑን ሹክ ልበልህ ብዬ ነው። 
የምር ግን... አንዳንዶቻችን እኮ እንዲሁ ነን...የዛኛውን ወገን ስሜት ሳናውቅ ለእሱ መራጭ እኛው እንሆናለን፡፡ ለምሳሌ የሆነ ሰው... “ዛሬ ምሳ እጋብዝሃለሁ...” ይላችሁና ‘ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል’ የሚል ማስታወቂያ ሰቅሎ፣ አሮጌ ፎጣውን ወዳልለወጠ እንትን ሬስቱራንት ትሄዳላችሁ፡፡ (ኮሚክ አኮ ነው... የዛሬ ስምንት ወር ተቦትርፋ ያያችኋት የጠረዼዛ ልብስ...ቢያንስ ምን አለ ሌላ ጠረዼዛ ላይ ቢያደርጓት?!)
እናላችሁ... ሜኑው ለሁለታችሁም ይቀርባል፡፡ (ጋባዥ ሌላ ሰው ከሆነ እኮ ሜኑ ስናነብ...አለ አይደል...ምግብ የምንመርጥ ሳይሆን ‘ፕሩፍሪዲንግ’ ምናምን ሥራ ላይ ያለን ነው የሚመስለው!) ታዲያላችሁ የዓይን አዋጅ ሆኖባችሁ አንድ በአንድ እያነበባችሁ እያለ፣ ጋባዥ ሆዬ ትእዛዝ ይሰጣል...
“ስማ... ለእኔ ዶሮ አሮስቶ፣ ለእሱ ደግሞ.... እ ቦዘና ሹሮ፡፡” ምን! እናንተ እኮ እንደ ሹሮ የሰለቻችሁ ነገር የለም፡፡ በቀደም ቤት ውስጥ ከማዳም ጋር ተጋጭታችሁ፣ አስራ አምስት ቀን ጀርባ ዞሮባችሁ የተኛችሁት፣ በዚህቹ በሹሮ ጦስ ነው፡፡
ትሪው፣ ሳህኑ እንጀራው ቦታ ቦታውን ይዟል፡፡ የወጥ ሳህኑ ይመጣል፡፡ ክዳኑ ከፈት ሲል፣ የእናንተ አፕታይት ጥርቅም ብሎ ይዘጋል፡፡
“ምነው ፊትህን ከሰከስክ?”
“እንደው አንዳንዴ ትንሽ ብታስቢልኝ ምናለበት!”
“ደግሞ ምን ሆንኩ ልትል ነው?”
”አራት ቀን በተከታታይ ሹሮ!”
“ይህንንም እኔ ልጅት ሆኜ ነው እንጂ፣ እንጀራው በወጥ ሳይሆን በሚጥሚጣ ነበር የሚቀርብለህ!”
“እና ዘላለም ጨጓራዬ በሹሮ መለሰን አለበት!?”
“አይ እንግዲህ፣ በሰንበት ምድር አትነጅሰኝ!”
ማዳም “አትነጅሰኝ...” የሚል ቃል መጠቀም ከጀመረች ነገርዬው ወደማይታረቅ ቅራኔ ስለሚገባ ጭጭ ብሎ በሹሮ ጨጓራውን ይለስናል፡፡ አለበለዛ ጀርባ አዙሮ መተኛቱ ለሁለት ወር ከምናምን ይሆንና ዋናው ረሀብ ይከተላል፡፡
እናም... ወደ ጨጓራ መለሰኛነት ያወረዳትና ደግሞም የሚስቱን ሰይጣን ልታመጣ ዳር ደርሳ የነበረችው ሹሮ፤ ሬስቱራንት ውስጥ መጣችላችሁ፡፡ ደግሞ እኮ ጋባዥ ሆዬ፤ ነገር ያማረለት መስሎት ወደ እናንተ ዞሮ ምን ቢል ጥሩ ነው... “ሹሮና ፍርፍር እንደምትወድ ስለማውቅ ነው!”
‘ኸረ የሚያፈረፍር....’ በሆዳችሁም ቢሆን ደግነቱ ዓረፍተ ነገሩ አለማለቁ፡፡ አሀ...እንደዛ በሽቃችሁ “...ያፈርፍርህ!’ የሚለው የመጨረሻ ቃል አምልጦ ቢወጣስ፡፡ ይሄ እኮ ለእርቅ ድርድርም ያስቸግራል፡፡
ስሙኛማ...የእርቅ ነገር ከተነሳ አይቀር እንበልና የጥንዶቹ ወዳጅ የሆነ ሰው ይደወልለታል፡፡
”ሄሎ...”
“ስማ፣ እፈልግሀለሁ...”
“ምን ሆንሽ፣ ደህና አይደለሽም እንዴ?!”
“እፈልግሀለሁ አልኩህ!”
“እሺ፣ እሺ ረጋ በይ፣ ማታ እመጣለሁ...”
“ማታ አይደለም፣ እሱ ከሥራ ከመመለሱ በፊት ነው የምፈልግህ...” የዛሬው ጫን ያለ መሆን አለበት፡፡
እንደተባለው ቀደም ብሎ ይሄዳል፡፡  በቀኝ ወገን ጠይም ጉንጯ ላይ ሰንበር ቢጤ በደብዛዛው ትታያለች!
“ምን ሆነሽ ነው?”
“ምን የሆንኩ እመስልሀለሁ፣ ንገረኛ፡፡ ምን የሆንኩ እመስልሀለሁ!”
“ንገሪኛ፣ ግራ አጋባሽኝ እኮ!”
“ለምን ጓደኛህን አትጠይቀውም! ምን ሆነች...ምን ሆነች አይደለም፡፡ ምን አድርገሀት ነው እንዲህ የሆነችው ብለህ ለምን አትጠይቀውም!”
“እሱ ነው እንዲህ ያደረገሽ?!”
“አይ አይደለም፣ ከበር ተጋጭቼ ነው፡፡ እንዲህ እንድልህ አይደል የፈለግኸው!”
ግን በእንባ ጠባቂነት ተጠርታችኋልና መቻል ነው፡፡ እናላችሁ... እዚህ ላይ ነው ነገርዬው ሊለማም ሊጠፋም የሚችለው፡፡
“ቆይ ረጋ በይ... ረጋ በይና እንነጋገር። ግዴለሽም ይሄን ነገር እኔ እፈታዋለሁ...” ምናምን ብሎ ለኖቤል ፕራይዝ የሚያሳጭ ተግባር መፈጸም አንድ ነገር ነው፡፡ ግን ደግሞ የዘንድሮ ነገር በብዙ መልኩ ስታዩት፣ ረጋ በይ ምናምን የሚል ብዙም አይደለም፡፡
“አንቺ! ምን አስተርፎሻል…ለትንሽ አይደል እንዴ የተረፍሽው!” ምናምን ይባልና አርጩሜ እንኳን ላልያዘችው ምስኪን፣ ጎራዴ ማቀበል የተለመደ ሆኗል፡፡ ባስ ሲል ደግሞ... “አሁን አንቺን የመሰልሽ ልጅ፤ እንዲህ አይነት ሰው ላይ ይጣልሽ!…” ሊባል ይችላል፡፡ የገዛ የልብ ጓደኛውን እኮ ነው! እኔ የምለው...ከጋብቻ በፊት አንድ ዓመት ተኩል ሙሉ፣ በሁለቱ መካከል መልእክት ስታመላልስ የኖርከው፣ አንደኛ ሚዜ ሆነህ በ“እኛማ ሙሽራ...” ዜማ ራፕ እየደነስክ፣ ዘፋኙን ግራ ያጋባኸው ራስህ አልነበርክም እንዴ! የምን ‘እንዲህ አይነት ሰው ላይ ይጣልሽ ወይ!’ ብሎ ነገር ነው!
ወይ ደግሞ አንዳንዱ አቤቱታ አቅራቢዋ ላይ ይዞራል... “አሁን በጥፊ ነካ አደረገኝ ብለሽ ነው ይሄ ሁሉ ያዙኝ ልቀቁኝ!” ምናምን ይልና ‘ብሌሚንግ ዘ ቪክቲም’ የሚሉት ተጠቂውን ጥፋተኛ የማድረግ ነገር ያመጣና፣ ነገር እንደማላላት፣ ጭራሽ ጧ ሊል እስኪደርስ ወጥሮት ቁጭ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ይሄ በሆነ ነገር የተጠቃን ወገን ጥፋተኛ የማድረግ ነገር እኮ የእኛ ሀገር ‘ቦተሊካ’ ውስጥ ‘ሁሉንም በጋራ የሚያስማማ ስትራቴጂ’ ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡ በተለይ ደግሞ በዳይ የተባለው የስልጣን ወይም የፈረንካ ጉልቤ ከሆነ፡፡ እናላችሁ...ፍርዱ “አሁን በጥፊ ነካ አደረገኝ ብለሽ ነው...!” አይነት ነገር ይሆናል፡፡
እሱ ዶሮ አሮስቶ እየጨረገደ፣ ለእኔ የአንጀት መለሰኛ ሹሮ ያዘዘልኝ ‘ወዳጄን’፤ ከእንግዲህ ግብዣህን ተቀብሎ የሚከተልህን እዛው ፈልግ ብሎሀል በሉልኝማ፡፡ ይሄ ሰውዬ እኮ ሌላ ጊዜ ከተከተልኩት “ለእኔ ደብል ብላክ ሌብል...እ... ለእሱ ደግሞ ጠቆር ያለ ቡና...” ብሎ አመዴን ቡን ካደረገ በኋላ ዘወር ብሎ... “ቡና ትወዳለህ ብዬ እኮ ነው!” ሊል ይችላል!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1068 times