Sunday, 25 October 2020 15:37

“የአባት ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን ከታዋቂው መምህርናa ደራሲው ባለቅኔአችን ከከበደ ሚካኤል ጋር አንድ የሀገራችን ገጣሚ ተገናኝቶ ሲወያይ :-
“እስከዛሬ ከፃፉልን ግጥሞች የትኛውን በጣም ይወዱታል ብሎ ጠየቃቸው”
አቶ ከበደም፤ ልጅን ማመረጥ አይቻልም፡፡
“ከልጅ ልጅ ቢለዩ አመትም አይቆዩ ሲባል አልሰማህም” ይሉታል፡፡
ገጣሚውም፤ “እርግጥ ነው አቶ ከበደ ያሉት እውነት ነው” ነገር ግን አንድን ፈጠራችንን አብዝተን እንወዳለን ማለት ሌላውን እንጠላለን ማለት አይደለም። “እንዲያው በጣም የሚያስታውሱትን ግጥም ይንገሩኝ፤ ብዬ ነው፡፡” ይላቸዋል በትህትና።
አቶ ከበደም በቃላቸው የሚከተለውን ግጥም ይሉለታል፡፡
አንድ ቀን አንድ ሰው ሲሄድ በመንገድ
የወንዝ ውሃ ሞልቶ ደፍርሶ ሲወርድ
ያው ከወንዙ ዳር እያለ ጐርደድ
አንድ አዝማሪ አገኘ ሲዘፍን አምርሮ
በሚያሳዝን ዜማ ድምፁን አሳምሮ
“ምነው አቶ አዝማሪ ምን ትሠራለህ?” ብሎ ቢጠይቀው
ምን ሁን ትላለህ?
አላሻግር ቢለኝ የውሃ ሙላት
እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት
ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ”
“አሁን ገና ሞኝ ሆንክ ምነዋ ሰውዬ
ነገሩ ባልከፋ ውሃውን ማወደስ
ግን እንደዚህ ፈጥኖ በችኮላ ሲፈስ
ምን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ
ድምፁን እያሽካካ መገስገሱን ትቶ?
እስኪ ተመልከተው ይሄ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ
ተግሳጽም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ!” አሉት፡፡
*   *   *
የሀገራችን ገጣሚያን በተለይ የጥንቶቹ ከልባቸው መካሪ፣ ከአንጀታቸው አስተማሪ ናቸው፡፡ ልጅነታችንን ያነፁ፣ አዋቂነታችንን የቀረፁ፡፡ ሃዋሪያት ነበሩ፡፡ ዛሬም ናቸው፡፡ ነገም ለልጆቻችን በእኛ ውስጥ ይኖራሉ!
“እያንዳንዱ ደራሲ አንድ ሌላ መንግስት ነው!” የሚለው የቶልስቶይ አባባል እውነትነቱ፤ ደራሲ የህዝብ አይን በመሆኑ ላይ ነው፡፡ ሌላ መንግሥት ነው የሚለን፤ የነገ ህልውናችንን ጠቋሚና አመላካች በመሆኑ ነው! ነጋችን የዛሬ ጥንስሳችን በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የዛሬ እቅድ የሁሉም ወደፊት መሠረት  ማለት ነው፡፡ “አንድ ፀሐፊ Plagiarize the future” እንዳለው ነው ጉዳዩ፡፡  
የኢትዮጵያ ስልጣን “አልሰሜን ግባ በለው” የሚባል አይነት ነው፡፡ ጨከን ብለን ካሰብንበትም “የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው!” መባሉ እውነት አለው፡፡
“ሥልጣንንም የህዝብ ማገልገያ እንጂ የግል መጠቀሚያ እንዳናደርግ አንድም ህሊናችን፣ አንድም ህግ ሊያስገድደን ይገባል፡፡”ይሉናል ጠበብት፡፡
“Absolute Tower corrupts absolutely” ይላሉ፡፡ “ፍፁም ስልጣን ፍፁም ሌባ ያደርጋል” እንደማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ህግን መሠረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ግለሰቦች ወደ ግለሰባዊ ጥቅማቸው እንዳያተኩሩ መቆጣጠሪያው ህግ ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ግን  “ተቆጣጣሪዎቹን ማን ይቆጣጠራቸው?” የሚለውን በጥብቅ ማስተዋል ይገባል ማለት ነው፡፡ በተለይ እንደኛ ሀገር የበቃ የሰው ሃይል በበቂ ደረጃ በሌለበት፣ በቂ ማቴሪያልና አመቺ ሁኔታ ባልጠረቃበት ሁኔታ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” ይባል እንደነበረው ዛሬ ፣ሁሉም ነገር ወደ ልማት መባሉ አግባብነት አለው፡፡ “ጉዞችን ረጅም ትግላችን መራራ መባሉን እንደ አርቆ አስተዋይ አሳቢ ሁነኛ መርህ ነው እንደ እኛ አገር ባለ ኋላቀር ኢኮኖሚያዊ አቅም መሠረታዊና የማያወላዳ ለውጥን ለማምጣት፤ በሂደት ቀስ በቀስ መበልፀግ እንጂ በዕመርታ ማደግ እጅግ አዳጋች ነው፡፡ ምኞትና ትጋት በቀላሉ አይጣጣሙም፡፡ ልማትን ልማት የማያደርጉ አያሌ ሳንካዎች አሉ፡፡ “የግድቡ ሙሌት የልባችን ሙሌት ነው”፡፡ ለማለት ብዙ የጥርጣሬ ጐርፍ ካናወጠን በኋላ የመጣ ነው፡፡ ተመስገን ነው! ከግል ስጋታችን ባሻገር የጐረቤቶቻችን አይን መቅላት፣ የሌሎች ሀገሮች የሩቅ ባላንጣነት ተጨማምሮ፣ ለብዙ አሉታዊ መላምት መዳረጉ ፀሐይ የመታው እውነት ነው፡፡
መቼም በደሀ ሀገር፣ ሁሉ አልጋ በአልጋ አይደሉምና፣ አልፎ አልፎ የሚያገረሹ የጐሣ ግጭቶች፣ የአልፀዱ ብሔር ብሔረሰቦች ፣የነገር ፈሪ ሴራዎች፣ ካልተባ አዕምሮ የሚመነጩ ስህተቶች ወዘተ ለለጋ እድገታችን ማነቆ መሆናቸው የሚታበል አይደለም ስለሆነም፤ ችግሮቻችንን ለመቅረፍ የሚችሉ ምሁራንን በበለጠ አሳምኖ በመጋበዝ፣ ከፍዝ ተመልካችነትና ከምንግዴ ዜግነት ወደ ንቁ ተሳታፊነት ማሸጋገር ዋና ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ ካላመጣን የየአቅጣጫውን ዘራፌነትና ምዝበራ ማስቆም ዘበት ይሆናል፡፡ የምሁራን አይነተኛ ሚና ጠቃሚ መሣሪያ የሚሆነውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ከሁሉ በፊት “የአባት ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” የሚለውን አስተሳሰብ እንዲዋጉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የምንለው ለዚህ ነው፡፡   

Read 11651 times