Saturday, 04 August 2012 10:45

ሰለሞን ሽፈራው ሕልሞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

የግጥም መጻሕፍት እንደ አሸን የፈሉበት፣ እንደፈሉም ሣይቆዩ ብርሃን አልባ ሆነው፣ ያለ ክብር ድርግም የሚሉበት ዘመን ቢኖር ይህ የኛ ዘመን ነው፡፡ ችግሩ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥናት ቢጠይቅም ዋነኛውና የሚታየው ግን ለግል ለጓዳ የምንፅፋቸውን ግጥሞች ሀገር ካላነበባቸው የሚል የስሜታዊነት ግልቢያ ነው፡፡ ታዲያ ይህ አሠሥ ገሰሱን አደባባይ ማውጣት የሚያመጣው ችግር የሚጐዳው፣ ግጥም የፃፉ ግን ገጣሚ ያልሆኑትን ሰዎች ብቻ ሣይሆን ገጣሚ ሆነው ግጥም የፃፉትንም ጭምር ነው፡፡

ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ሆኖ፣ ሥጋ ብቻ ሣይሆን አጥንት ያላቸውም ይዳጣሉ፡፡

አንባቢያን አንዳንዴ፣ ለዚያውም ፍቅር የላቀብን የወጡትን መፃሕፍት ገልበጥ-ገልበጥ አድርገን እናያለን - ግጥም ናፍቆን! የግጥም ንባብን ናፍቆት ያልደረሰበት አያውቀውም!

ይኸው ዛሬም በእጄ ላይ ወር ያህል የቆየውን የሰለሞን ሽፈራውን መጽሐፍ ፋታ ሣገኝ አገላበጥኩት! አንዳንዶቹን አልወደድኳቸውም! የወደድኳቸውም ጥቂት አይደሉም! … ያልወደድኳቸው መጥፎ ሆነው አይደለም! አንዳንዴ ውበት እንደ አልማዝ ካላብረቀረቀበት የሚል ክፉ ዓመል ስላለብኝ እንጂ፡፡ ይሁን እንጂ ሰለሞን የአንድ ሰሞን ዝናም ያበቀለው ገጣሚ አይደለም፣ ሥር ያለው እውነተኛ የጥበብ ሕይወት የበቀለበት ልብ እንዳለው የሚሸተት ነው!... አንዳንድ ቦታ ፖለቲከኛ ይመሥላል፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ምስኪን ልብ ያለው የጥበብ ሰው፣ ርሁሩህ ነፍስ ድምፅ ይደመጥበታል! … ለሀገር ተቆርቋሪ፣ ለትውልድ የሚብከነከን ልብ ያለው ነው የሚያሠኝ አዝማሚያ ይንፀባረቅበታል፡፡

ለምሳሌ ለሀገር ሲቆረቆር

“ፈሪ ቁም - ፈረ ቁም”

ምንተ ላል ይብላ

ሲሸሽ የሞተ ሰው፤

ተዝካሩ አይበላ፡፡

እንዲህ ያለው ብሂል

ሁሉም የየራሱን፣ የመከራ መስቀል

ደፍሮ በመሸከም ሳይደማ ሳይቆስል

ሞት ሳይኖር፣ ትንሳኤ የሚገኝ ይመስል …

ስንቶች እዚያ ማዶ ከነጭ ሰራሹ

የነገደ ያንኪን

መንግስተ ሰማያት፣ ለመውረስ የሚሹ

(ያውም በቀውጢ ቀን)

ይቺን ምስኪን አገር እየጣሏት ሸሹ… ገጣሚው በክፉ ቀን አገራቸውን ጥለው የሸሹ “ፈሪ ለናቱዎችን” እያወገዘ ነው፡፡ የትኛው ቀውጢ ቀን እንደሆነ ባናውቅም! ለሀገራችን ቀውጢ ያልሆነ  ቀን የቱ ይሆን? በርግጥ አንዱ ካንዱ ይብሣል!

ሌለው የተመቸኝ ሀሣብ “አፍ እላፊ” የሚለው ነው

ህይወት ፍቅር ተስፋ

እምነት እውነት ውበት

ጨርሶ ሊጠፋ

አገር ታምሞ ሊሞት

በተቃረበበት …

አንድ የቀን ጨለማ

እኔና ጐጆዬ እግዜርን ስናማ

“የብሉይ የአዲስ

ህያው ቅዱስ ቃሉን እምነት ሳናሳልስ

ዛሬም በጭንቅ ቀን

ዓርብ ዕሮብ ሁዳዴን ፆም ፀሎት አጥብቀን

ምሃረነ እያልን አውጣን ተመከራ

ሰባ ጊዜ ሰባት ስሙን ስንጠራ

ጆሮ ዳባ ታለ

እሱም ቃል ብቻ ነው - ተሰው ያልተሻለ

ብለን በሹክሹክታ እኔና ጐጆዬ

እግዜርን ስናማው፤

ድንገት ሰምቶን ኖሮ ባሰብን ጨለማው፡፡

የሰው ሕይወት ናት ይህቺ! ያመነ ሰው፣ ቀን ሲከፋበት፣ እንደ ዕምባቆም ይጠይቃል፤ ይነዘንዛል! እንደ ሣራ አምላኩ ላይ ይሥቃል! ፍፃሜው ግን ሰለሞን ካለው የሚለይ ይመሥለኛል! ገጣሚው ግን በምናቡ የፈቀደውን ያህል መሄድ ይችላል፡፡ ብቻ ደስ ይላል - ሀሣቡ! በተለይ ጐጆውና እርሱ መሆናቸው ጠለቅ ያለ ጉዞ ሊወስደን ይችላል፡፡ ሩቅ ነው ሀሣቡ!

“የፈጠራ ነፍስ” የምትለው ግጥም ስሜት ትነዝራለች! የብዙ ሰዎች ሕይወት የተንጋደደበት፣ ጥም ያጣበትም ምክንያት ናት!!

በሰው ደን ተከብቤ

ሰዎች መሀል እየኖርኩኝ

ለምንድነው ሰው መራቤ?

አወይ እኔ ይብላልኝ!

ከማን ጋራ ይሆን ጠቤ…?

የዕድሜዬን እኩሌታ

ያባከንኩት ተብከንክኘ

ለካስ ህይወት መቅኖም የላት

ሰው መክሊቱን ካላገኘ፡፡

“የጠቆሩ ልቦች” ለኔ ከጣሙኝ ግጥሞች ተርታ አንዱ ነው

ይቺ አጉል ዘመናይ፣ የወንዜ ልጅ እቱ

አፍሪካዊ መልኳ፤ “ደብሯት” ጥቁረቱ

ፊቷን በ”ሜክ አፕ” እጇን በእንሶስላ

ፀጉሯን ባንዳች ቀለም፣ ቀባችው ልትቀላ፡፡

ግን ባይገባት እንጂ፣ እንዲህ የምትደክም

እንዲህ የምትለፋ …

የቆዳችን ሳይሆን፣ የልባችን መጥቆር

ነው አገር ያጠፋ፡፡

ሰለሞን ሽፈራው ውበት አድናቂም ነው፡፡ የሚቀጣጠል የገጣሚ ነፍስ አለው፡፡

ጥበብን ያደንቃል፣ ውበትን ያደንቃል፡፡ የጥበብ መነሻ ውበት ነው፡፡

የውበት ጭቅቅት ደንቃራ ነው፡፡ ስለ ውበት መሣቅ፣ ስለ ውበት ማልቀስ የገጣሚ ሚና ነው፡፡ መንደድ መቃጠልም አለው!... ነድዶ አመድ መበተን! “ሰው ሰራሽ በሆነ” የሚለው የሰለሞን ግጥም ዘላለማዊ ውበትን ተመኝቷል፡፡ የማይጨማደድ ቆዳ፣ የሚንቦገቦግ ደም፣ የሚነድዱ ዓይኖች! … የማያንቀላፉ ቀኖች! … ገጣሚ ከተፈጥሮ አጥር ዘልሎ ካልተመኘ የዛሬ እሥረኛ ይሆን ነበር!... ግን ሰንሰለቱን በጥሶ፣ ተፈጥሮን “አፍንጫሽን ላሺ” ብሎ በምናብ ሰማይ ላይ ቁልቁል ሊያሽሟጥጥ ይችላል! የተወራራሽ ሕልሞቹ እንዲህ ነው፡፡

ይሄ ያንቺ ውበት

አምላክ ሰርቶ አፍራሹ፣ የተጠበበበት

ምሉዕ በኩሌሎው፣ ይህ ላንቺ ሰውነት

አመልማሎ ገላ

ምነው ታይቶ ጠፊ፣ ስጋ ለባሽ ሸክላ

መሆኑ በቀረ…!

እንደሞናሊዛ

በሰዐሊ ብሩሽ! እየተቀሸረ

በግዑዝ ሸራ ላይ፤ ከቅይጥ ቀለማት

የተመሰጠረ

“አብስትራክት” ሆኖ ዝንታለም በኖረ፡፡

ትውልድ ሁሉ ውበትሽን ባየው! የሚል ነው ምኞቱ! … አፈር አይብላሽ፣ ሞት አያጠውልግሽ!... በዘላለም ቀለበት ተሽከርከሪ! ማለቱ ነው!!

“ተወራራሽ ሕልሞች” የሚለው የሰለሞን ሽፈራው መጽሐፍ ውስጥ ሌሎችም ጥሩ ጣዕም ያላቸው ግጥሞች አሉ፡ በአብዛኛው “ሂሶች” ናቸው፤ ፀፀቶች! ምርቃት ርግማንም አለ፡፡ ሕይወትም የነዚህን አላባውያን መሠላል ሣትረግጥ አትራመድም! ገጣሚም ከሕይወት ጅረት በስተቀር ከየትም አይቀዳም፡- “ስሞታ” ቁ.2ን ቦታ ቢኖረኝና ባሥነብባችሁ ጥሩ ነበር፡፡ ግን ቦታ አነሰኝ! … ደስ ትላለች! አንድ ነጠላ ግጥም ተጋበዙልኛ!… ከመፅሃፉ፡፡

 

 

 

Read 2323 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 11:25