Saturday, 04 August 2012 10:48

ናኦል

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

“…ና! ጠጋ በልና ቁጭ በል!” አልኩት፤ ወታደራዊ በሚመስል ትዕዛዝ፡፡ ገፀ-ባህሪንማ የማዘዝ መብት ተሰጥቶኛል፡፡ we all know who we are … እኔ ደግሞ ፀሎተኛ ነኝ፡፡ ፀሎቴን ወደ ፈጣሪ ጆሮ የምተኩሰው በገፀ ባህሪው አማካኝነት ነው፡፡ ፈጣሪ፤ ድርሰትን እንጂ ደራሲውን የማድመጥ ፍላጐትም ሆነ ትዕግስት የለውም፡፡ ተራ ሰው የሚያሰማው ድምፅ… ተራ ነው፡፡ ተራው፤ ተራራ ስለሆነ … ለመወጣት ይከብደዋል፤ አድማጩን፡፡  የጠራሁትን ገፀ ባህሪ፤ ሰሞኑን በሙሉ በዙሪያዬ ሲሽከረከር እያየሁ እንዳላየሁ ችላ ብዬው ነበር፡፡ … ገፀ ባህሪዎች ካልተፃፉ አይሞቱም፡፡ በጭንቅላቴ ጀርባ እና ዙሪያ እየተሽከረከሩ እድሜ ልኬን ሰላም የሚነሱኝ ብዙ ሌሎች ገፀ ባህሪዎችም አሉ፡፡ የመግደያ ጊዜ አጥቼ ጭጭ ብዬአቸዋለሁ፡፡ … እየተንጫጩ ሰላሜን ሲያጠፉት…  አንዳንዶቹን ለሰው ጓደኞቼ አወራቸዋለሁ፡፡ … በመፃፍ ገፀ ባህሪን ገድለህ ሀውልት ማድረግ ካልቻልክ፤ በማውራት ግን ፓራላይዝ አድርገህ ዊልቸር ላይ ዘላለም ማስቀመጥ ትችላለህ፡፡

ፈጣሪ ከገፀ ባህሪ በላይ ነው፤ ሰው ደግም ከገፀ ባህሪ በታች፡፡ ለፈጣሪ የምለው ነገር ስላለኝ ፀሎቴን እንዲያደርስልኝ ይሄንን ገፀ-ባህሪ ጠራሁት፡፡

ተንደርድሮ መጥቶ ጐኔ ተቀመጠ፡፡ እኔም እስክሪፕቶ እና ወረቀት አወጣሁ፡፡ ስሙን ጠየቅሁት፡፡ አይኑን አቁለጨለጨ፡፡ ያቁለጨልጨው አይኑ እንኳን በአግባቡ አልተሰራለትም፡፡ ብቻ … የሆነ ደራሲ ከዚህ በፊት ጀምሮ ሳይቀጥለው ትቶት የሄደ ብጭቅጫቂ ነገር ነው፡፡ ስምም የለውም፡፡

እኔን እንዲመስል ስለፈለግሁ፣ በእኔ ቁመና እና የጭንቅላት መጠን አድርጌ መጥረብ ጀመርኩ፡፡ … በተጀመረው ገፀ ባህሪ ላይ እንደገና መጀመር የገፅ እና የባህሪ መመረዝን እንደሚያመጣ አውቃለሁ፡፡ ቢያንስ የደም አይነቱን የበፊቱን ከአሁኑ ጋር አንድ ማድረግ ነበረብኝ፡፡

“…ከዚህ በፊት መፃፍ የጀመረህ ደራሲ ነበር?” አልኩት፤ ቀና ብዬ በምናብ አይኔ ሳላየው፡፡ ማየት ሳልፈልግ፡፡ እኔ የምሰጠው ማንነት እንጂ … ከዚህ ቀደም ስለተሰጠው እኔን አይመለከተኝም፡፡ “…ከዚህ በፊት መፃፍ ተጀምሬ የነበረው በእርሳስ ነበር … ስምም ተሰጥቶኝ ነበር፡፡ ቶልቻ ነበር የመጀመሪያ ስሜ”

ድንገት አስጠላኝ፡፡ ናቅሁት፡፡ ገፀ ባህሪውን ብቻ ሳይሆን፤ በእርሳስ ፅፎ የጀመረውን ደራሲም ጨምሬ፡፡ ምን ማለት ነው ዘላለማዊ ፀሎትን በእርሳስ መፃፍ? በእርሳስ የሚፅፍ መሳሳት የሚያበዛ ደራሲ ነው፡፡ በላጲስ ለማጥፋት የማይሳሳ፡፡ ለዚህ ነው ቶልቻ ተብዬው ብዙ ነገሩ የጠፋ እና … ያልጠፋው ደግሞ የደበዘዘ የሆነው፡፡ ቶልቻን የጀመረው… ጀማሪ ደራሲ መሆን አለበት፡፡ … ጅማቱን ያጠነከረ ደራሲ፤ በቀለም ነው የሚስለው፤ በእስክሪፕቶ የዘይት ቀለም፡፡ ስርዝ ድልዝ በማይፈቅደው፣ አንዴ ከተጀመረ መጠናቀቅ ባለበት የውሳኔ አቋም ቀለም፡፡

“ስምህን ቀይሬዋለሁ… ከእንግዲህ ቶልቻ ሳትሆን … ናኦል ነህ፡፡ ትርጉሙ ለአንተ ምንም ባያደርግልህም፤ ለሚያነብህ ፈጣሪ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ “ከእኔ በላይ” ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ ከእኔ በላይ ላለው ፈጣሪ … ከእኔ በላይ የሚደርሰውን ፀሎቴን ወስደህ ታስረክብልኛለህ”

“ምንድነው ፀሎቱ?” ብሎ ጠየቀኝ… ፊሪ ነገር ይመስላል፡ ፈራ-ተባ በሚል ፀሀፊ የተጀመረ ፍጥረት ነገር ነው፡፡

“የፀሎቱ መልእክት አድራሽ ነህ እንጂ፤ ፀሎቱ ምን እንደሆነ ማወቅ አትችልም፡፡ ገፀ ባህሪ ከደራሲ ጋር መወያየት አይችልም፡፡

… በነፃነት እንድታወራ ማን እንደፈቀድልህ አላውቅም፡፡ እኔ እንደ ሌሎቹ ደራሲዎች አይደለሁም፡፡ ኢምፕሮቫይዜሽን… ምናምን የሚባል ጣጣ አላውቅም፡፡ አንተ መልዕክት አድራሽ ነህ፡፡ እኔ መልዕክት ላኪው ነኝ፡፡ ወደ ኋላ ዞረህ መልዕክቱ ምንድነው? ብለህ እንዳትጠይቀኝ ከእንግዲህ!” የዕውነት ተቆጣሁ፡፡ ገፀ ባህሪ እንደ አህያ እየገረፉ ካላሸከሙት ይጠግባል፡፡ አህያነቱን ረስቶ ፈረስ የሆነ ይመስለዋል፡፡

“ቢያንስ… በተጀመርኩበት የደሜ ቀለም… በእርሳስ ትፅፈኛለህ?...ጋሼ?!”

“እኔ በእርሳስ አልፅፍም፡፡ የምፅፈው ለመሰረዝ ለመደለዝ አይደለም፡፡ የምፅፈው በማይጠፋው የብዕር ቀለም ነው፡፡ አንተ ደግሞ እኔን ተመስለህ ስለሆነ ፈጣሪ ፊት የምትቀርበው፤ ስህተት ሊኖርብህ አይገባም፡፡ በእርሳስ ፅፌህ፤ ፀሎቴ በሰይጣን እጅ ቢገባ… በላጲስ ድርሰቴን አጥፍቶ የራሱን ጠማማ ፍላጐት በእኔ መልዕክት ውስጥ ሊፅፍ ይችላል’እኮ!...አሁን አርፈህ ተቀመጥ፡፡ ልድረስህ”

***

አርፎ ተቀመጠ፡፡ እኔም መፃፍ ቀጠልኩ፡፡ መጀመሪያ ገፀ ባህሪው ናኦልን በመልክም ሆነ በአመለካከት እኔን እንዲሆን አድርጌ በፊደሎች ቅብ ዳራውን ሰራሁት፡፡ ከዛ፤ እኔ በአሁኑ ሰአት ፍቅር እንደያዘኝ የሚያሳየውን ደስተኝነት እና “ሙሉነት” ለናኦል ሰጠሁት፡፡ … ፍቅረኛዬን ሙሉን ከጐኑ አስቀምጬ አስተቃቀፍኳቸው፡፡ አስተቃቅፌ ገለፅኳቸው፡፡ ሙሉና እኔ የተገናኘንበትን አጋጣሚ ለናኦል እና ሙሉ ሰጥቼ አስዋብኳቸው፡፡ እኔ እንዴት እንደምወዳት እና እሷ እንዴት እንደምትወደኝ … የሚሰማኝን ሁሉ ለናኦል እና እሷ እንዲሰማቸው አድርጌ ፃፍኳቸው፡፡

ስትስመው፤ ከንፈሯ እንዴት ያለፈውን ጊዜ እና የሚመጣውን መጥጦ እንደሚያጠፋ፤ … እሱን ውስጧ ሙሉ ለሙሉ ለማስገባት የምታደርገውን ሙከራ አንድ በአንድ ገለፅኩት፡፡ … በነብሱ አጥንት ውስጥ ሊያትማት እንዴት አድርጐ ጨምቆ እንደሚያቅፋት … ፍቅር ሲሰሩ … በሰው ልጆች ላይ ሳይሰራ የቀረ  ነገር ሁሉ እንደሚጠናቀቅ … እሱ ሲያወራላት … ጆሮዋ የተፈጠረበትን ምክንያት እንዴት አድርጋ እንደምትገነዘብ … ሁሉንም ለእነሱ ሰጥቼ ደረስኳቸው፡፡ ለናኦል እና ለሙሉ፡፡ … ስህተት የሰራሁትም እዚህ ላይ ነው፡፡

***

ድርሰቱ ተጠናቀቀ፡፡ ናኦልም ዘላለማዊ ሆኖ ሞተ፡፡ ጊዜ የማያልፍበት … ሁሉ ለአላፊው ጊዜ እይታ ሙታን ነው፡፡ የድርሰቴ ዋና አላማ ፀሎት ስለነበር፤ የፀሎቱን ምላሽ መጠባበቅ ያዝኩኝ፡፡ ፀሎቱ በአጭሩ … የእኔና የሙሉ ፍቅር እስክንሞት  ድረስ እንዲቀጥል ለመለማመጥ … ፈጣሪን ማባበያ ነበር፡፡ … ያዝልቅላችሁ እንዲለኝ ነበር ዘላቂ ድርሰት የፃፍኩት፡፡

***

የፀሎቴም ምላሽ አልመጣም፡፡ ሙሉንም ድርሰቱ ከተጠናቀቀበት እለት አንስቶ አይቻት አላውቅም፡፡ … እንግዲህ፤ የጠፋችበትን ምክንያት ከብዙ ማሰላሰል በኋላ ነበር የደረስኩበት …፡፡

ስዕልን በቅርበት ስትቀባው ልታየው ስለማትችል የሰራኸውን ለማየት ከስዕሉ መጠን ሶስት እጥፍ ራቅ ብለህ … ልትመለከተው ይገባል፡፡ የገለፅኩት ትክክል መሆኑን ከድርሰቱ ሶስት እጥፍ ርቀት ላይ ሆኜ ስመለከተው … ድርሰቱ እንጂ ምርጥ ፍቅረኛዬ ሙሉ ግን እንዳሰብኳት እንዳልሆነች ተገነዘብኩ፡፡ … ጥላኝ የሄደችው የድርሰቷ ሙሉ ነች እንጂ (ተራዋ) የኑሮዋ አብራኝ አለች፡፡ እኔም፤ እንደሷው ሆኜ አብሬአት መኖር ቀጠልኩ፡፡ ተራውን ተራራ መስዬ፡፡ ፀሎቴ ግን ወደ ተነጣጠረበት ኢላማ ደርሷል፡፡

…እኔና…ኑሮዬ የኑሮ ፍቅራችን ዘልቆልን አብረን ቆየን፡፡ ናኦል እና ፍቅረኛዬም አብረው እንዳሉ ድርሰቴን ያነበበ ሰው ሁሉ በየጊዜው ይነግረኛል፡፡ ድሮውኑ ፍቅር ያስያዘችኝ ሙሉ እኔ የተመኘሁዋት ገፀ-ባህሪ ነበረች ለካ! … ከገፀ ባህሪዬ የተማርኩትም ትምህርት ሁሉ እንደ ሳግ ጉሮሮዬ ላይ እየመጣ ያንቀኛል፡፡ ምርጡን ማንነቴን ለገፀ ባህሪው (ናኦል) … ምርጡን የፍቅር ትዝታዬን ደግሞ ለገፀ ባህሪዋ (ሙሉ) ሰጥቼ … እኔ ተራውን ደራሲነቴን ከተራዋ የኑሮ አጋሬ ጋር እየጋገርኩ መቀጠል … የስኬቴ መጨረሻ … የእውቀቴው ጫፍ ሆነልኝ፡፡

 

 

 

Read 4855 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 10:55