Monday, 19 October 2020 00:00

ኢትዮጵያ፣ ብዙ ሙፈሪሃቶች ያስፈልጓታል!

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(0 votes)

   ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ እትም ላይ “ሴታዊነት፤ ለፖለቲካችን ጤናማነት ያለው ሚና” በሚል ርዕስ አንድ ጽሁፍ አስነብቤ ነበር። በዚሁ ጽሁፍ ላይ፣ የወንዳዊነት አስተሳሰብ ጎልቶ በሚታይበት የሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት፣ የፖለቲካችንን ሴታዊነት ባህርይ ማጠናከር ሊኖረው የሚችለውን ጉልህ ድርሻ ለማመላከት ተሞክሯል፡፡ በተጨማሪም፣ ስም ሳልጠቅስ “እንደ ምሳሌ ሊወሰዱ የሚችሉ የሴታዊነት መሰረታቸውን የጠበቁ ሴት አመራሮች እያየን በመሆኑ የእነርሱን አርአያነት ማበራከት ያስፈልጋል” በማለት ገልጬ ነበር፡። ሰሞኑን፣ ከነዚህ ተምሳሌታዊ ሴት አመራሮች አንዷ የሆኑት የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩት የተባለው መልዕክት፣ በመደበኛና ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከፍተኛ የመነጋገርያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ይህ በመሰረቱ ጠቃሚ ሆኖ ሳለ፣ ባንዳንድ ወገኖች የሚካሄደው ዘመቻ መሰል እንቅስቃሴ ግን የሚያሳስብ ነው። ከሁሉም በላይ፣ ከብዙዎች በተሻለ ደረጃ ሚዛናዊ ናቸው ብዬ የምገምታቸው ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ተንታኞችና ጦማሪዎችም የዚሁ ዘመቻ አካል የሚያስመስላቸው ሃሳብ ሲሰጡ መስማቴ እጅግ አሳዝኖኛል። ወደ ዝርዝር ሃሳቤ ከመግባቴ በፊት ከዚህ በታች ያለውን ጽሁፍ ይዘት ባግባቡ ለመረዳት፣ አንባቢዎች ከላይ የተጠቀሰውን በሴታዊነት ላይ ያተኮረውን  ጽሁፍ (ካላነበቡት) ከአዲስ አድማስ ድረ-ገጽ ላይ ፈልገው እንዲያነቡት አሳስባለሁ።
ለመሆኑ፣ ከሰሞኑ ከየአቅጣጫው የተዘመተባቸው ወ/ሮ ሙፈሪሃት የተናገሩት ምንድን ነው? ምንም እንኳን ንግግራቸውን እንደወረደ (verbatim) የመስማት እድል ባይኖረኝም፣ በተለያዩ ሚዲያዎች እንደቀረበው ከሆነ የሚከተሉት አንኳር ነጥቦች ይገኙበታል። አንደኛ፣ የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ መንግስታት ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የህዝቡንና የሃገሪቱን ጥቅም ማስቀደም አለባቸው። ሁለተኛ፣ ፖለቲከኞቻችን በሃሳብ ተለያየን ብለው አይንህን ለአፈር መባባላቸው ነውር ነው። ሶስተኛ፣ መርዝን ከሚረጩ ጥቂት ፖለቲከኞች ባሻገር ህዝብና ሃገር የሚባሉ ታላቅ ጉዳዮች አሉ። አራተኛ፣ በር ዘግቶ እንኪያ ስላንቲያ ከመግጠም ይልቅ ወደ ጠረዼዛ ዙሪያ መጥተን መወያየት ይኖርብናል። አምስተኛ፣ ያለብንን የፖለቲካ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አሁንም እድሉ አለን። ነገር  ግን ይህ ዕውን እንዲሆን በሁለቱም ወገኖች ያሉ የፖለቲካ መሪዎች ሰከን ሊሉ ይገባል። ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሃሳቦች እንደ ሃሳብ እንከን ሊወጣላቸው የማይችል ከመሆናቸውም ባሻገር፣ ምናልባትም እኔን ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚጋሯቸው ጭንቀቶችና ሃሳቦች ይመስሉኛል። ለዚህም ታላቅ ከበሬታና አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ የተለያዩ ወገኖች ወ/ሮ ሙፈሪሃትን ከልዩ ልዩ አቅጣጫ ሲወቅሱ ይሰማል። ከዚህ በመቀጠል የነዚህን ወገኖች ዋና ዋና መከራከሪያዎች ለመመልከት እንሞክራለን።
በቀዳሚነት በብዙዎቹ የተነሳው፣ እነኚህን ከብልፅግና ፓርቲ የተለዩ የሚመስሉ ሃሳቦችን አደባባይ ላይ እንዲወጣ ማድረጋቸው ከፓርቲው መስመር ማፈንገጣቸውን ከማመልከቱም በላይ በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል መከፋፈል እንዳለ ያሳያል የሚለው ነው። እንዲህ አይነቱ አመለካከት ለረዥም ዘመናት ተቆራኝቶን ከቆየው የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አስተሳሰብ ጋር የተያያዘና የውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲ አስፈላጊነትን ካለመረዳት የመነጨ ሊሆን ይችላል። ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ፣ ባንድ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ውስጥ በመሰረታዊ የፖለቲካ ዓላማዎችና ግቦች የጋራ አመለካከት መኖር አስፈላጊ የመሆኑን ያህል፣ ወደነዚህ ግቦች ለመድረስ በሚያስችሉ መንገዶች ላይ የተለያዩ አማራጮች መኖር፣ ለፓርቲው ጤናማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እስካሁን በይፋ ከተነገረው፣ ብልፅግና ፓርቲ እንደ ፓርቲ፣ በአሁኑ ሰዓት በፌዴራል መንግስቱና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል እየሰፋ የመጣውን የአመለካከትና የአስተዳደር ልዩነት፣ ከጦርነትና ግጭት በመለስ መፈታት እንደሚገባው ያምናል።  በርግጥ፣ ከብልፅግና ውጭ ያሉ አንዳንድ ፖለቲከኞችና ተንታኞች፣ የትግራይ ክልልን በመምራት ላይ የሚገኘው ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)፤ በማናቸውም መንገድ ከስልጣን እንዲወገድ የሚሹ መሆኑ አይካድም። በብልፅግና ፓርቲ ውስጥም ይህንን አማራጭ የሚደግፉ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ልዩ ልዩ አማራጮችን የመፈተሽና የማንሸራሸር ባህል፣ ለሃገሪቱ ፖለቲካ ጤናማነት የሚበጅ እንጂ ጎጂ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በመሆኑም፣ ብልፅግናም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለየት ያሉ ሃሳቦችን ወደ አደባባይ ማውጣት ሊያበረታቱት የሚገባ ልማድ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ሊታመን የሚገባው፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ የምንጊዜውም ተመራጭ መንገድ መሆኑን ነው።
በሁለተኛ ደረጃ የሚነሳው፣ እንዴት በማናቸውም መንገድ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት መጥፋትና መወገድ ከሚገባው ህወሃት ጋር ባንድ ጠረዼዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን እንወያይ ይላሉ የሚል ነው። እነኚህ ወገኖች፣ ባብዛኛው በህወሃት የበላይነት ይመራ በነበረው ዘመነ ኢህአዴግ (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር) የፖለቲካና አስተዳደር በደል የተጎዱና የቆሰሉ ወገኖች ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን፣ ዲሞክራሲያዊ ባህልን ከመገንባት አኳያ፣ የነዚህ ወገኖች ትኩረትና ጥረት መሆን ያለበት፣ ህወሃት በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ያደረሳቸውን በደሎችና የፈጸማቸውን ስህተቶች በተጨባጭ በማሳወቅና የተሻሉ አማራጮችን በማቅረብ የድርጅቱን እጣ ፈንታ እራሱ  የትግራይ ህዝብ እንዲወስን ማድረግ ነው። ይህንን ለማድረግም፣ ህወሃት ቀይ ምንጣፍ አንጥፎ እንዲቀበላቸው መጠበቅም የለባቸውም። ከዚህ በተቃራኒው፣ ህወሃት በማናቸውም መንገድ መወገድና መጥፋት አለበት ብሎ መናገር የዲሞክራሲያዊነት ዋነኛ መሰረት የሆነውን የህዝብን የመጨረሻ ወሳኝነት መብት መንጠቅ ከመሆኑም በላይ ቀደም ሲል ህወሃት በተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ላይ ፈጽሞታል የሚባለውን ታሪካዊ ስህተት መድገም ይሆናል።
በሶስተኛ ደረጃ የሚነሳው፣ ወ/ሮ ሙፈሪሃት በሃገሪቱ ውስጥ ህግና ሰላምን ለማስከበር ከፍተኛ ሃላፊነት የተሰጣቸውን ዋና ዋና መስሪያ ቤቶችን የሚመራውን የሚኒስቴር መስሪያ ቤት በበላይነት የሚመሩ በመሆናቸው፣ ባለፉት ሁለት የለውጥ ዓመታት በሃገሪቱ ለደረሰው የጸጥታ መናጋትና ህዝቦች መፈናቀል ዋነኛ ተጠያቂ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ከሰሞኑ የሰጡትን መግለጫም፣ የማይመለከታቸውን የድርድር ጉዳይ በማንሳት ድክመታቸውን ለመሸፈን የተደረገ ጥረት እንደሆነ ያመለክታሉ።  እንዲህ አይነቱ አመለካከት የሰላም ሚኒስቴርን መሰረታዊ አላማና ተግባራት ካለመረዳትና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወገኖች ተነሳሽነት ለተካሄዱ ውይይቶችና ድርድሮች ይሰጥ የነበረውን ድጋፍ ካለመገንዘብ የመነጨ ሊሆን ይችላል። የአንድ የሽግግር ወቅት መንግስት ውጤታማነት የሚወሰነው በእጁ ውስጥ ያለውን የኃይልና የማሳመን አቅም (hard and soft power) በሚዛናዊነት ለመጠቀም ባለው ብቃት ነው። እንዲህ አይነቱ ተግባርም ባንድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚከናወን ሳይሆን አጠቃላዩ የመንግስት መዋቅር የሚረባረብበት ነው። በዚህ ረገድ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ የተጀመረውን ህግን የማስከበር ተግባር ከውጤታማ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ጋር ማቀናጀት እጅግ አስፈላጊ ነው።  ከሰሞኑ፣ ወ/ሮ ሙፈሪሃት የተናገሩት ነገርም ይህንን ሚዛን ለመጠበቅ የተደረገ መልካም ጥረት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።
በአራተኛ ደረጃ፣ አንዳንድ ወገኖች ሚኒስትሯ የተናገሩትን ሃሳብ ለህወሃት ነበራቸው ከሚባለው ስስ ስሜት (sympathy) ጋር በማያያዝ እየተካሄደ ላለው ለውጥ ያላቸውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት ሞክረዋል። ጥቂቶችም፣ ካሉበት ኃላፊነት መነሳት አለባቸው ብለዋል።ይህ አሳዛኝ አመለካከት፣ ለረዥም ዘመን ተጠናውቶን የቆየው ሃሳብን በሃሳብ ከመሞገት ይልቅ ወደ ስም ማጥፋትና ማጠልሸት (character assassination) የመሄድ አሳፋሪ የፖለቲካ ቅሪትን ያመላክታል። እንዲህ አይነቱን አዝማሚያ ሁሉም በሃገራችን ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን የሚሹ ወገኖች ሊያወግዙትና በጽኑ ሊታገሉት ይገባል። በተለይም፣ በአብዛኛው ማህበረሰብ እንደ አቅጣጫ አመላካች (opinion makers) ተደርገው የሚገመቱ ወገኖች ከእንዲህ አይነቱ ስህተት ሊጠበቁ ይገባል።  
በአምስተኛ ደረጃ የሚነሳው፣ እንዴት የፌዴራሉንና የክልሉን መንግስት በእኩልነት በማስቀመጥ ሁለቱንም ወገኖች ‘ሰከን በሉ’ ብለው ይናገራሉ የሚል ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ እኔ እንደተረዳሁት፣ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ሰከን በሉ ያሉት በሁለቱም ወገኖች ያሉ አንዳንድ ፖለቲከኞችን እንጂ መንግስታቱን አይደለም። በርግጥም፣ በሁለቱም ወገኖች ያሉ አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች በተለያየ ወቅት እየወጡ የሚናገሩት ነገር ውጥረቱን ይበልጥ የሚያከሩ እንጂ ወደ መፍትሔ ለመሄድ የሚያግዙ አይደሉም። ከሌሎች ሃገሮች ተመክሮ እንደታየው፣ ለሰላማዊ መፍትሄ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት የመጀመሪያው እርምጃ፣ ሁሉም ወገኖች ውጥረትን ከሚያባብሱ አባባሎች (rhetoric) መታቀብ ይሆናል። ባሁኑ ሰዓት በፌዴራል መንግስቱና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል ያለውን መካረር ለማርገብና ለመፍታት ከሁሉም ወገኖች በተለይም ከፌዴራል መንግስቱ፣ ከምንም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ሆደ ሰፊነት (magnanimity) እና ታጋሽነት የሚጠበቅበት ወቅት ነው። ይህንን ማድረግ ለሃገርና ለህዝብ ታላቅ አክብሮት በማሳየት መከበርን የሚያስገኝ እንጂ በደካማነት የሚያስፈርጅ አይሆንም።
በአጠቃላይ፣ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ተናገሩት የተባሉት ነጥቦች ለወቅቱ የሃገራችን የፖለቲካ ውጥረት መፈታት አይነተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ በመሆናቸው ልንደግፋቸው ይገባል። ይህ ንግግራቸው፣ በወንዳዊነት መንፈስ የተጫነብንን ‘የዘራፍ’ ፖለቲካ ለማከም የሴታዊነት አመለካከት ሊኖረው የሚችለውን ጉልህ አስተዋጽኦ በተጨባጭ የሚያሳይ በመሆኑ በድጋሚ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙ ሙፈሪሃቶች ያስፈልገዋል እንላለን። በዚሁ አጋጣሚ፣ የትግራይ ክልል መንግስት መሪዎችም፣ የቀረበውን የብሔራዊ መግባባት ውይይት ጥሪ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በመቀበል በቀዳሚነት ለትግራይ ህዝብና በትግሉ ወቅት ለተሰዉ ሰማዕታት፣ በጥቅሉ ደግሞ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸውን አክብሮት እንዲያሳዩ በትህትና አሳስባለሁ።  ታላቁ የሳይንስ ምሁር አልበርት አይንሽታይን እንዳለው፤ ‘የዛሬውን ችግራችንን በትናንትናው መንገድ ለመፍታት መሞከር ከንቱ ድካም ነው’።  
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው  ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።


Read 2328 times