Monday, 19 October 2020 00:00

‘ፈረንጅ ነፍሴ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል፤.... ውሸት መናገር፣ ነጩን ነገር ጥቁር ነው ብሎ ድርቅ ማለት ምናምን በቃ ሁላችንን የሚያመሳስል ባህሪይ ሊሆን ነው ማለት ነው! ውሸት መናገር እንደ ቀድሞው አንገት ማስደፋቱ ቀርቷል፡፡ ሀሰት መናገር እንደ ቀድሞው ማሸማቅቁ ያበቃለት ይመስላል፡፡ ከእኛ ምድር ቤት ካለነው ጀምሮ እስከ ‘ቦሶቻችን’ ድረስ ሽምጠጣ ‘አርት’ እየሆነ ነው፡፡ ሳይንስ የሆነ እለት ነው ጉዳችን የሚፈላው! (ቂ...ቂ...ቂ...)
እናላችሁ... በቱሪስትነት ከመጣ ትንሽ ቀናት ከቆየ በኋላ እኛ ‘ጆርናሊስቶች’ ድምጽ መቅጃችንን ገፋ እናደርጋለን... “ለመሆኑ ከሀገራችን የምታደንቀው ነገር ምንድነው?” ስንል ‘አፋጣጭ’ ጥያቄ  እንጠይቃለን። (አሁን እንግዲህ እኛ እንዲህ ትንፋሽ የሚያሳጥር ጥያቄ እየጠየቅን እነ ስቲፈን ሳከር፣ ጄክ ታፐር ምናምን ብቻ ስማቸው መጠራቱ የለየት አድልዎ ነው!) እሱ ምን ብሎ ይመልሳል መሰላችሁ...“ሴቶቻችሁ ቆንጆ ናቸው፡፡”
እኛ ‘ጆርናሊስቶች’ እንቀበልና ምን የመሰለች ሽልማት የምታስገኝ ሰበር ዜና እንሠራበታለን “በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ የነበሩ የጀርመን ቱሪስቶች፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ቆንጆ መሆናቸውን አረጋገጡ፡፡” ምርጥ ዘገባ! ብራቮ! ይህ በሩጫ ያሸነፈ አትሌት ሜዳሊያውንና ባንዲራውን እያሳየ ሜዳውን አንድ ዙር የሚሮጥበት ‘ቪክትሪ ላፕ’ የሚሉት ነገር ያስፈልገናል፡፡ ‘ጆርናሊስቶች’...ኸረ ሰዋችን በጣም እየቀደመን ነው! ጊዜው እኮ ሰዋችን መረጃዎች የሚያገኝባቸው በርካታ አማራጮች ያሉበት ነው፡፡ እናም ምን ለማለት ነው.... “ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ መሆኑን የወረዳ መቶ ምናምን የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ገለጹ...” አይነት ‘ሰበር ዜና’ መውጣት ካልቻልን አስቸጋሪ ነው፡፡
የምር ግን፣ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ለሁሉ ነገር የፈረንጅ ቡራኬ ያስፈልገናል ማለት ነው?! እኛ በራሳችን መለኪያዎች ምርጥ ለሆኑ ነገሮቻችን ‘ቪክትሪ ላፕ’ የምንሮጠው ፈረንጅ ‘ኦኬ’ ሲለን ብቻ ነው ማለት ነው!?  
አሁን በአሜሪካ የምርጫ ዘመቻ ሰሞን ላይ ሌላው ሀገር ላይ ማእቀብ ለመጣል እንትን የሆነች ዶሮ የማትቀድማቸው የኮንግረስ አባላት በተነሱ ሃሳቦች ሳይሆን በፓርቲ አባልነት  ብቻ ተመስርተው  የሚያካሄዱትንና አንዳንዶቹ ራሳቸው ‘ቻይልዲሽ’ የሚሉት አይነት እሰጥ አገባ እያየን አይደል! ፕሬዝዳንታቸው በየጊዜው የሚናገሩት፣ አንድ ተራ ሰው ቢናገረው “ይህች ሰውዬ አንደኛውን ነቀለችና አረፈች!” የሚያስብሉ እኮ ናቸው፡፡  
እናማ... ‘ፈረንጅ’ እርስ በእርሱ መደማመጥ ሲያቅተው እያየን ነው። እና ፖለቲከኛውም፣ ምኑም ስቴት ዲፓርትመንት በር መቆርቆርን ትቶ ቢደማመጥ ለማለት ያህል ነው፡፡
“ለስንትና ስንት ዘመን ስንዘባበትባት የኖርናትን ጤፍ እኮ ብሄራዊ አጄንዳችን ነገር ያደረግናት “ፈረንጅ እየለመዳት ነው፣” ሲባል፣ አንዱ ፈረንጅ ደግሞ “የጤፍ ኮፒራይት ለእኔ ነው የሚገባው፣” ምናምን ነገር አለ ሲባል ነው፡፡
ታዲያላችሁ...እኛ እኮ ስንትና ስንት የምንጠቅሳቸው ነገሮች እያለን፣ የጥበብ ሀገር ያልነበረች ይመስል...  “እንትና የሚባለው የአሥራ ስድስተኛው ክፍል ዘመን የእንግሊዝ ደራሲ በአንድ ወቅት እንደተናገረው...” እንላለን፡፡ እናላችሁ... በርካታ መረጃ ሞልቶ በተረፈበት ወቅት እኛ ግን ‘ፈረንጅ ነፍሴ’ አይነት ነገር ገና የለቀቀችን አይመስልም!
እናላችሁ...
ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ እንግዲህ ታከተኝ
የሆዴን ጠይቆ ማን ባሰናበተኝ…
የምትል የከረመች ስንኝ አለች፡፡ የምር አሁን የሆዳችንን የሚጠይቀን አጥተን ነው እንጂ...ስንቱን ባወራነው ነበር፡፡ የሚጠይቀን ቢኖር ኖሮ... “እባካችሁ ለወደቀውም፣ ለተንጋደደውም ፈረንጅ፣ ፈረንጅ ማለት ትተን ወደ ራሳችን መመልከት እንጀምር...” እንላቸው ነበር፡፡ የሚጠይቀን ቢኖር ኖሮ... የሆነ የውጭ መንግሥት ሹምም ሆነ፣ የሆነ ተራ ቱሪስት ነገር ስላጨበጨቡልን ብቻ፣ እሰይ፣ እሰይ ስላሉን ብቻ እውነታቸውን ነው ማለት አይደለም፡፡ እና የ‘ፈረንጅ ነፍሴ’ አስተሳሰብ አይደለም ወንዝ ሊያሻግረን፣ ድልድዩ አጠገብ አያደርሰንም። እና በአፋቸው የፈለጉትን ይበሉ እንጂ በውስጣቸው የሚያስቡት.... “ሴቶቻችሁ ቆንጆ ናቸው፣” ከማለት የተሻለ አይደለም፡፡   
ታዲያላችሁ... ራሱ መደማመጥ ያቃተው ‘ፈረንጅ’፣ ራሱ በአደባባይ ዜጎቹ አንገት ላይ ጉልበት ጭኖ ለሞት የሚዳርግ ‘ፈረንጅ’፣ እኛን ስለ ህግና ህጋዊ ስርአት  ለማስተማር የትኛው የሞራል ከፍታ ነው የሚፈቅድላቸው! እንዴት ነው እነሱ ሁሉንም ነገር የጨረባ ተዝካር አድርገው ሲዘላለፉ እየዋሉና እያደሩ፣ እኛን  እየተደማመጣችሁ ተነጋገሩ የማለት ሞራል ሊኖራቸው የሚችለው!?  
በራሳቸው ሀገር የምርጫ ነገር ‘ውጪ ነፍስ፣ ግቢ ነፍስ’ ወደሚመስል ዳርቻ ላይ ቆመው ሳለ “ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ካላካሄዳችሁ ወዮላችሁ፣ ቪዛ ኖንቼ!” የሚሉን እንዴት ነው?! ‘የያዘ አይለቅ’ ሆኖባቸው ነው እንጂ፡፡ ደግሞላችሁ... በፖለቲከኞቻቸውም በሌሎች ዘርፎች ባለሙያዎቻቸውም የተዛቡና ፍጥጥ ያሉ የሀሰት መረጃዎችና ትርክቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እያየንም፣ እየሰማንም ነው። እናላችሁ...ለራሱ ታማኝ ያልሆነ ‘ፈረንጅ’ እንዴት ነው ለእኛ ታማኝ የሚሆነው?!
በሀሰት ለለወጧት እውነትን በአፋቸው
የቁም ነገር አምላክ ይቅር ይበላቸው፣
ገሸሽ አድርገዋት ታላቋን ፍቅር
ሆነው ለተገኙ የሀሰት ምስክር
በእውነት ጨክነው ቃላቸውን ላጠፉት
ይቅር ይበላቸው ላሉትም ላለፉት፣
የምትል ስንኝ አለች፡፡ “ይቅር ይበላቸው፣” ማለት እንዳለ ይሁንና ፈረንጅን ሰማይ የሚሰቅል አስተያየት አንጀታችንን ሰርስሮ ለመግባት ሲሞክርም፣ ሁሌም እቅጩን እየተናገረ ነው ብሎ መደምደሙ...‘ሳሩን አይቶ ገደሉን አለማየት’ ነው የሚሆነው። እዚህ ሀገር ለበርካታ ወራት ሲገጥሙን በነበሩና እስካሁንም እየገጠሙን ባሉ  ችግሮች  የ‘ፈረንጅ ነፍሴ’ ረጅም እጅ ሊኖርበት ይችላል ብሎ ማሰብ ክፋት አይኖረውም፡፡ ውለታ ቢስነትም አይሆንም። ጭብጨባ ብቻ እየሰሙ ዓይንን መጨፈኑ ልክ አይሆንም፡፡
ይቺን ‘ጆክ’ ስሙኛማ...ሰውየው ጓደኛውን ይጠይቀዋል፡፡ “አንድ ሰው አህያውን ሲደበድብ ባየውና አህያውን ባስጥለው ምን አይነት ፍቅር ይባላል?” እናላችሁ... አጅሬው ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው... “ወንድማዊ ፍቅር!” ምን ለማለት ነው--ጭብጨባ ብቻ ማሳደድ እንዲህ አይነት ምላሽም  ሊያስከትል ይችላል ለማለት ያህል ነው፡፡
ሀሰት ለመናገር አትሻም ምላሴ
ለእውነት እሞታለሁ፣ አልሳሳም ለነፍሴ
ያልሆነውን ሆነ ብዬ ከማለት
እውነት ተናግሬ ይሻለኛል ሞት
የምትል ስንኝ አለች፡፡
ታዲያላችሁ... ‘እውነት ተናግሮ ይቺን ዓለም መሰናበት ብሎ ነገር አይደለም በእውነተኛው ዓለም፣ ፊልም ውስጥም ብዙ የሚታይ አይደለም፡፡ እናማ... ‘ፈረንጅ ነፍሴ’ን እውነተኛ፣ ሀቀኛ፣ ለክሩ የሚታመን ምናምን ብሎ የማሰብ ነገር ዋጋ ያስከፍለናል እንጂ ከተራራው ማዶ አያደርሰንም፡፡
በነገራችን ላይ እስካሁን ‘ፈረንጅ ነፍሴ’ ስንል የቆየነው ‘የቆዳ ቀለምን ብቻ’ የሚመለከት እንዳልሆነ ልብ ይባልልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ! 

Read 1203 times