Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 04 August 2012 10:34

“ገንዘቡ ባይኖረን ቃልኪዳኑ አለን”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የድርጅታችሁ ዓላማ ምንድነው?

ሀገራዊ ራዕይ መሸከም የሚችል ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ እስካሁን ይህን ለመተግበር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ሴት ተማሪዎች ላይ ሰርተናል፤ ሴቶችን ማስተማር ሀገርንና ሕዝብን ማስተማር ነው በሚል መርህ፡፡ ባለፈው ዓመት ለሰባት ሺህ ሴቶች በሚሊኒየም አዳራሽ ጉባዔ አዘጋጅተን፣ ስኬታማ ሴቶች ልምድ እንዲያጋሯቸው አድርገናል፡፡ የሐይማኖት መሪዎችም ነበሩ፡፡ ውጤቱንም እያየን ነው፡፡ የተሻለ የትምህርት ውጤት ኖሯቸው በአቅም ማነስ መማር ያልቻሉ ሴት ተማሪዎችን በመደገፍ፣ ሕፃናቱ ትምህርት እንዲቀጥሉ እድል ፈጥረናል፡፡ ጐንደር ላይ የልቀት ማዕከል ለማቋቋም በክቡር አቶ በረከት ስምኦንና በክቡር አቶ መላኩ ፈንታ የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፤ ወደ ግንባታ እየገባን ነው፡፡ ማዕከሉ እንደ ዊንጌት እና በእደ ማርያም ት/ቤቶች የመጠቁ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች የሚያፈራ ነው፡፡ የምክርና የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

የጐንደሩ ማዕከል ሥራ ፈቅ እንዳላለ ነው ያለኝ መረጃ…

የመሠረት ድንጋይ ሲጣል ከጐንደር ካርኒቫል ጋር ተያይዞ እንዲጣል ጥር ላይ ነው የተቋቋመው፡፡ ቦታው ምቹ ስላልሆነ ጐንደር ዩኒቨርሲቲ አካባቢ እንደገና ተመርቶ እየተገነባ ነው፡፡ በዓመቱ ለጥር ወር የሚታይ ግንባታ ይኖራል፡፡

ድርጅታችሁ ምንም ገንዘብ ሳይኖረው እንዴት በሚሊየኖች የሚቆጠር ባጀት ያቅዳል?

እንዲህ የሚሉ በማየት የሚያምኑ ናቸው፡፡ ተቋማችን ገና ትልቅ ተቋም የሚባል አይደለም ሕዝቡን የሚያሳምን ራዕይ ካለህ ሕዝቡን ይዘህ ትልቅ ሥራ መሥራት ትችላለህ፡፡ ገንዘቡ ባይኖረን ቃልኪዳኑ አለን፡፡ ለምሣሌ ለግንባታ የሚያስፈልገውን ጠቅላላ ሲሚንቶ አግኝተናል፡የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ ሲሚንቶም ብርም አልነበረንም፡፡ አባይን እንገድባለን ሲባል ገንዘብ ኖሮ አልነበረም፡፡

የጐንደሩ መሬት በስልክ ነው የተሰጠው ሲባል ሰምቻለሁ?

ምን? መሬት በስልክ አይደለም፡፡ በስልክ መሬት ተሰጥቶም አያውቅም፤ ካለም የተበላሸ አሰራር ነው፡፡ መስተካከል አለበት፡፡ ጥያቄ በደብዳቤ አቅርበን ነው የተሰጠን፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ሳይሆን የክልሉ ካቢኔ ነው መሬቱን የፈቀደው፡፡ በስልክ ወሰዱ የተባለው የሰፈር ወሬ ነው፡፡

ግን እኮ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ትቀራረባለህና… ሳያንኳኳ በሩ ይከፈትለታል ብትባልስ?

ሳላንኳኳ ቢከፈትልኝ ትልቅ እድል ነው፡፡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በር ሳላንኳኳ ከከፈቱልኝ አንድ ለውጥ የሚያመጣ ራዕይ አይተዋል ማለት ነው፡ ሳላንኳኳ እንዲከፈትልኝ ነው ፀሎቴ፡፡ እኛ ሀገር አንኳክተህም ላይከፈትልህ ይችላል፡፡ ከሕይወት መመሪያዎቼ አንዱ ለሕግና ሥርአት መገዛት ነው፡ ራዕዬን ላገኘሁት ሰው እናገራለሁ፡፡ ለምሣሌ ለአቡነ ጳውሎስ ሥርአቱን ጠብቄ አነጋግሬ አግዙኝ ብዬ ለምኛቸዋለሁ፡፡ ተቋማችን ሕጋዊ ነው፡፡ ደብዳቤ ይፃፃፋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መጀመሪያ ከወጣቶች ጋር ያደረጉትን ስብሰባ የእኛ ድርጅት ነው ያዘጋጀው፡፡

በአቡነ ጳውሎስ ስም የሕክምና ማዕከል ማቋቋሙ እንዴት ታሰበ?

በጥቅም ትስስር አይደለም ይሄን የምንሰራው፡አቡነ ጳውሎስ የኛን ራዕይ በማሳካት ይጠቅሙናል፡፡ ከሳቸው ጋር ያለን ግንኙነት የተወሰነ ነው፡፡ ደጀሰላም ድረገጽ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር የጥቅም ትስስር አላቸው ብሎ አውጥቷል፡፡ አንድ የሀይማኖት አባትን እንዲህ ማለት በጣም ፀያፍ የሆነ ተግባር ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ሰው አይደለሁም፡፡ ሊሾሙኝ ሊሸልሙኝ አይችሉም፡፡ ከባህርያቸው ስንነሳም እንዲህ የወረደ ተግባር ላይ ይሰማራሉ የሚል እምነትም የለኝም በግሌ፡፡ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ድክመት ሊኖረው ይችላል፡፡

በነገራችን ላይ የሕክምና ተቋሙን ያሰብነው በሳቸው ስም አልነበረም፡፡ ታናሽ እህቴ በሳንባ በሽታ ሞተች፡፡ አላሳከምኳትም፡፡ ሁልጊዜ በስሟ ኢየሩሳሌም ቲቢ ማዕከል የሚል ሃያ ሰው እንኳ ቢሆን የሚረዳበት ባቋቁም የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ የኔን እህት ማን ያውቃታል? ማን ያግዘኛል? ዝም ብሎ ተረትና የቤተሰብ ፍቅር ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ በታዋቂ ሰው ስም ቢደረግ ገንዘቡ ሊመጣ ይችላል፡፡ ለአቡነ ጳውሎስ ሀሳቡን አመንጭተን አስረከብናቸው፡፡ በስማቸው ያደረግንበት ዋናው ምክንያት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርክ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ቦርዳችን ውስጥ ሦስታችን የተለያየ ክርስትያን ሁለቱ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ የሃይማኖት ሥራ አንሰራም፡፡ “ሰላም ለኢትዮጵያ” የሚል ድርጅቴ ላይ የበላይ ጠባቂ ናቸው፡፡ በቋንቋ የማይገለፅ ብዙ እገዛ አድርገውልናል፡፡ በ1997 በምንሰራቸው ሥራዎች ብዛት ወደ ማረሚያ ቤት ልንላክ ሁሉ ነበር፡፡ እሳቸው ናቸው የተከላከሉልንና የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅትን ያልተቀላቀልን የሰላም ሰዎች መሆናችንን ያስረዱት፡፡ በእሳቸውም ስም ነግደን ይህን የሕክምና ማዕከል ለትውልድ ማትረፍ እንፈልጋለን፡፡ እነ “ደጀ ሰላም” ጉድለቶችን ብቻ ነው የሚያዩት፡፡ እኛ ግን ጉድለት ላይ ሳናተኩር ለአባቶች በጐ ሥራ እውቅና እንሰጣለን፡፡ ትልልቆችን ማክበር የጀመርነው በአቡነ ጳውሎስ አይደለም፡፡ ሦስት ሚሊየን ተኩል ብር አውጥተን ለአርበኞች ክብር ሰጥተናል፡፡ በሃያ ደቂቃ ንግግር ጀነራል ሳሞራ የኑስ የአንድ ሚሊዮን ብር ሜዳልያ ነው የሰጡን፡፡ ሸራተን ምግቡን ቻለልን፡ አፄ ቴዎድሮስንም ትልቅነታቸውን አውቀን ነግደንባቸው ለአሁን ትውልድ የሚጠቅም ማዕከል እንገነባለን፡፡ ተቋም ተገነባም አልተገነባም ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ ያላቸው ቦታ የተጠበቀ ነው፡፡ ከመንግሥት ጋር ለመነጋገር ሕግ አለ፡፡ በአቋራጭ አትሰራም፤ እኔ ደላላ አይደለሁም፡፡

በምንድነው የምትተዳደረው?

የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል የምል ሰው ነኝ፡፡ ከ”ሰላም ለኢትዮጵያ” ደመወዝ አለኝ፡፡ ውጭ ሀገር የምትኖር ባለቤቴም የራሷ ሥራ ስላላት እንረዳዳለን፡፡ ደመወዜን አብቃቅቼ እኖራለሁ፡ ለወደፊት ወደ ግብርና ለመግባትም አስባለሁ፡ ለሀገሬም እሰራለሁ፡፡ በታማኝነት ለራሴም እሰራለሁ፡፡ ደጀሰላም “ቪዥን ፎር ጀነሬሽን” ገንዘብ እያካበተ ነው ብሏል፡፡ የ”ቪዥን ፎር ጀነሬሽን” የሂሳብ ደብተር ግን የተከፈተው ባለፈው ሳምንት በእኔ 500 ብር ነው፡፡ አንድ ብር የለውም፡፡ ዳሸን ባንክ ሄደህ ጠይቅ፡፡

በፓትርያርኩ ስም ሊሰራ የታቀደው የሕክምና ማዕከል በምን ሊገነባ ነው ታዲያ?

ፓትርያርኩ ባላቸው አለም አቀፍ እውቅና አማካይነት በቦርድ ይመራል፡፡ በዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ ድጋፍ ይሰራል፡፡ መታሰቢያ ድርጅት በስማቸው ነው የተቋቋመው፡፡ የቦርድ ሰብሳቢውም ራሳቸው ናቸው፡፡ ላቀረብነው ሃሳብ ጥቅም አልጠየቅንም፡፡

ቦሌ መድኃኒዓለም ያለው የአቡነ ጳውሎስ ሐውልት ሲሰራ ተሳትፈሃል ሲባል ሰምቻለሁ…

በጭራሽ የለሁበትም፡፡ ሐውልቱ ላይ የለሁበትም፡፡ የእሳቸው ግን ወዳጅ ነኝ፡፡ ወዳጅነቴ ለራሴ ጥቅም ነው፡፡ እጃቸው ወፍራም ነው፡፡ የእኔ ቀጭን ነው፡፡ ስለዚህ በእሳቸው እጅ አንኳኩቼ አስከፍታለሁ፡፡ ለትውልድ የሚጠቅም ሥራ እንሰራለን፡፡ በጋራ እንሰራለን እንጂ ሌላ ጉዳይ የለም፡፡

በሸራተኑ ዝግጅት ማህበረ ቅዱሳንን አልጋበዝክም እንዴ?

ማህበረ ቅዱሳን በቤተክህነት መዋቅር ነው ያለው፡፡ የጥሪ ካርድ ስናስተላልፍ ከመዋቅሩ ላሉ ነው ጥሪው የተላለፈው፡፡ የጥሪ ካርዱ ለማህበረ ቅዱሳን በእኔ በኩል ሳይሆን በመዋቅሩ ነው መሆን ያለበት፡፡ ከማህበሩ ጋር ችግር የለብኝም፡በጋራ የሚያሰራ ሥራ ሲኖር አብሮ ለመስራት ዝግጅ ነኝ፡፡ ቤተሰቦቼ ኦርቶዶክስ ክርስትያን ናቸው፡፡ እኔም እንደዚያው ነኝ፡፡ አዘውትሬ ግን ቤተክርስትያን የምሄድ የሐይማኖት ሰው አይደለሁም፡፡ በጋራ ጉዳይ አብረን መሥራት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር በሰላም እና ልማት ጉዳዮች ላይ አብረን መሥራት እንችላለን፡፡ መስቀል ሲያሳልሙ አብሬ አሳልማለሁ ማለት ግን አይደለም፡፡

ስለ ሰላም ስሰራ ንግግር ያደርጉልኛል፤ በሴት ልጅ ትምህርት ላይ ስሰራ ምክር ይሰጡኛል፡፡

መሰናበቻ ሃሳብ ካለህ?

ረዥም እድሜ ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ አንዳንዴ ከባህል የሚያፈነግጡ ድርጊቶች አያለሁ፡ከመሬት ተነስቶ ስም መስጠት ነውር ነው፡፡ በጐ ነገር የማየት አቅማችንን እንጠቀምበት፡፡ ለመታረም ፈቃደኛ ስለሆንኩ በግል አድራሻዬ እገኛለሁ፡ጀግኖቻችንን፤ ባለውለቶቻችንን እናክብር፤ መኖርያ ቤታቸውን ለዩኒቨርሲቲ የሰጡት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፤ ዩኒቨርሲቲው በስማቸው መሰየም ይችላል፡፡ ቦሌ አየር ማረፊያ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቢሰየምም ባለውለታን ማክበር ነው፡፡

 

 

Read 2591 times Last modified on Saturday, 04 August 2012 10:45