Wednesday, 21 October 2020 00:00

የደራርቱ ነገር፣ የለተሰንበት ጉዳይ እና በእግረ-መንገድ፡- “የኢ-ሜይል አድራሻ ስለሌለው ከበርቴ”

Written by  አበበ ገ/ህይወት
Rate this item
(7 votes)

   ፍልቅልቋ ደራርቱ በጊዜዋ ከልብ አስፈንድቃናለች፡፡ አገራችን ውጥንቅጥ ውስጥ በነበረች ጊዜ፣ ሰንደቅ ዓላማችን ክብሯ ዝቅ እንዲል በተደረገበት ወቅት፤ በባርሴሎና ኦሎምፒክ በአስር ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታልናለች፡፡
ሰንደቅ ዓላማችን በኦሎምፒክ መድረክ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ዕንባዋ በጉንጮቿ ሲወርድ፣ እኛም ሳይታወቀን ጉንጫችን በዕንባ የረጠበ፣ ልባችን አብሯት ያለቀሰ፣ ለምንጊዜም ጀግናችን ዘመን የማይሽረው ልዩ ፍቅርና ክብር አለን፡፡
የአበበ ቢቂላ የስኬት ምስጢር በሴቶችም ሊተገበር የሚችል መሆኑን ያሳየች፣ የጠንካራ ሥራና ውጤት ተምሳሌት ነች፡፡ ዛሬም በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊነት ቦታ ሆና መሪነት ማለት በተግባር እያሳዩ መምራት (Leading by example) እያገለገሉ መምራት (Servant leadership) መሆኑን እያሳየች ትገኛለች፡፡
በቅርቡ ከኦሎምፒክ ጽ/ቤቱ ጋር የተፈጠረውን ችግርና ጉዳዩን ያስተናገደችበት መንገድ የመሪነት ብቃቷን አሳይቷል፡፡ ለተሰንበትና አሰልጣኟ በምንም ምክንያት ይሁን፣ በተቸገሩ ጊዜ በምሽት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝታ የችግሩ መፍትሔ ሆናለች፡፡
አትሌቷ አሸንፋ ስትመለስም፤ በዓለም መድረክ ማሸነፍ ከምን ያህል ጥረት በኋላ እንደሚገኝ ጠንቅቃ የምታውቀው ጀግናዋ ደራርቱ፤ ለተሰንበትንና አሰልጣኟን በጠዋት አየር ማረፊያ ተገኝታ #እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ እንኳን ደስ አለን; ብላቸዋለች። የትናንት አሸናፊነት ለዛሬ ዋስትና አይሆንምና ለተሰንበትንና አሰልጣኟን ለቀጣዩ ኦሎምፒክ ጠንክረው እንዲሰሩ ልምዷንና ምክሯን አካፍላቸዋለች፡፡ እነሱም ስለ እሷ ጥረትና በጎነት ለመናገር ቃላት እንደሚያጥራቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
በመገናኛ ብዙሃን በተለይ በማህበራዊ ድረገፆች ነገሩን ፖለቲካዊ መልክ ለመስጠትና ለማካረር የተሄደበትን መንገድ ብስለት የተሞላበት የቀና ሰው አስተያየት በመስጠት ረገብ እንዲል መክራለች፡፡ እንደ ደራርቱ የተግባር ሰው ለመሆን እንጣር ብለን ወደ ለተሰንበት ስንሻገር፡-
ለተሰንበት እና “ማኀበራዊ ሚዲያ” አይተዋወቁም
የለተሰንበትን የአሸናፊነት ውጤት ስንመለከት ውጤቷ ድንገት ከሰማይ ዱብ ያለ አይደለም፡፡ አሰልጣኟ እንደገለፁት ላለፉት ስድስት ዓመታት በምትኖርበት አካባቢ፣ በእጇ ባለው ነገር፣ የምትችለውን ሁሉ ጥረት ታደርግ ነበር፡፡ ልክ እንደ አበበ ቢቂላ እና እንደ ደራርቱ ቱሉ፡፡
የዓለም ክብረ ወሰንን ስታሻሽል ከውጤቷ በላይ በማህበራዊ ሚዲያ ሰፈር ትርምሱ ገዘፈ፡፡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ህይወትን ቀለል ለማድረግ የማስቻላቸውን ያህል የሰነፎች፣ የሴረኞችና የሥራ ፈቶች ምሽግ መሆናቸውም በተደጋጋሚ የሚታይ ነገር ከሆነ ሰነባበተ፡፡
እንደ አሰልጣኟ ገለፃ፤ "ለተስንበት እንኳን ማኀበራዊ ገፅ ልትጠቀም ይቅርና የእጅ ስልክ የላትም”፡፡ እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ትኩረቴን ሊከፋፍሉት ይችላሉ፣ ከዓላማዬ ሊያደናቅፉኝ ይችላሉ ብላ በመገመት ለጊዜው እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በፍፁም አትጠቀምም፡፡ ለአስፈላጊ ጉዳይ የአሰልጣኟን ስልክ ትጠቀማለች፡፡ እንደ እሷ በተግባር የተፈተኑትን የደራርቱንና የሌሎች እህቶቿን ፈለግ በመከተል ጠንክራ መስራቷን ቀጥላለች፡፡ በስሟ የተከፈቱት ማኀበራዊ ድረ ገፆች አንዳቸውም የእሷ አይደሉም። የዓለም ሻምፒዮና እና የኦሎምፒክ ባለድል ለመሆን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት መስፈርት ውስጥ እንደሌለበት ስለምታውቅ ብዙ አትጨነቅም፡፡ የእሷ ትኩረት በቶኪዮ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ለራሷና ለአገሯ ታሪክ መስራት ነው፡፡
እግረ መንገድ፡- “የኢሜይል አድራሻ የሌለው ከበርቴ” ታሪክ
አንድ ሥራ-አጥ የሆነ ሰው በአንድ ትልቅ ኩባንያ ውስጥ በፅዳት ሠራተኝነት/ተላላኪነት ለመቀጠር ያመለክታል፡፡ ከቃለ-መጠይቅና ቀለል ያለ የተግባር ፈተና በኋላ፤ አሠሪው "እንኳን ደስ አለህ! ተቀጥረሃል" ካለው በኋላ፤ ቀጠል አድርጎም፣ "የኢ-ሜይል አድራሻህን ስጠኝና የቅጥር ፎርሙንና መቼ ሥራውን መጀመር እንዳለብህ መልዕክት እልክልሃለሁ" ይለዋል፡፡
ሥራ ፈላጊው ሰውዬ ግር አለው፡፡ እያመነታ ኮምፒዩተርም ሆነ የኢ-ሜይል አድራሻ የለኝም ብሎ መለሰ፡፡ አሰሪው በመገረም ምን አልክ?! በጣም አዝናለሁ። የኢ-ሜይል አድራሻ ከሌለህ እንደ ሰው አትቆጠርም፡፡ ሰው ካልሆንክ ደግሞ ሥራ ሊኖርህ አይችልም በማለት አሰናበተው። በኪሱ ውስጥ አሥር ብር ብቻ የነበረው ሥራ-ፈላጊ፣ አግኝቶት የነበረው ተስፋ ከመቅፅበት የጨለመበት ቢሆንም፣ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ሃሳቡን ሰበሰበ፡፡ ወዲያውኑ አንድ ውሳኔ ወሰነ፡፡ ከፊት ለፊቱ ወደ ተመለከተው የአትክልት መሸጫ ሱቅ ሄደና በአሥር ብሩ ቲማቲም ገዛ፡፡ ቲማቲሙን በር-ለበር ተዟዙሮ በመሸጥ ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ገንዘቡን እጥፍ አደረገው፡፡ ሁኔታውን ደጋገመ፡፡ ማታ ወደ ቤቱ 60 ብር ይዞ ገባ፡፡
ሥራ-አጡ ሰውዬ ሕይወቱን በዚህ መንገድ መቀጠል እንደሚችል ተረዳ፡፡ ከእሱ የሚጠበቀው ጥረት ማድረግ ብቻ እንደሆነ ተገነዘበ፡፡ በለሊት ከቤቱ ይወጣና በጣም አምሽቶ ይመለሳል፡፡ በጥረቱ ልክ ገንዘቡ እየበዛ፤ እጥፍ ደርብ እየሆነ ሄደ፡፡
በመጀመሪያ ጋሪ፣ ቀጥሎ አነስተኛ ተሸከርካሪ፤ በመቀጠልም ብዙ ተሽከርካሪዎች ያሉት ነጋዴ ሆነ፡፡
ከአምስት ዓመታት በኋላ …
በአካባቢው የታወቀ (ትልቁ) የምግብ ሸቀጥ ኩባንያ ባለቤት ሆነ፡፡ ንግዱና ኩባንያው እያደገ በመምጣቱ ለሕይወቱም ሆነ ለንብረቱ የመድን (ኢንሹራንስ) ሽፋን ለመግዛት ወሰነ፡፡ በዚሁ መሠረት ከአንዱ የኢንሹራንስ ባለሙያ ጋር አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ከተነጋገሩ በኋላ የኢንሹራንስ ሠራተኛው ነጋዴውን የኢ-ሜይል አድራሻ ጠየቀው፡፡
ነጋዴው ፈርጠም ብሎ የለኝም አለው። የኢንሹራንስ ሠራተኛው በመገረም “የኢ-ሜይል አድራሻ” ሳይኖርህ ይህንን ታላቅ የንግድ ኩባንያ ገንብተሃል፤ በዚህ ላይ የኢ-ሜይል አድራሻ ቢኖርህ ምን ማድረግ እንደምትችልና ንግድህም የት ሊደርስ እንደሚችል አስበህ ታውቃለህ? ብሎ ጠየቀው፡፡
ነጋዴው ለጥቂት ሰከንዶች ካሰበ በኋላ፤ #የኢ-ሜይል አድራሻ ቢኖረኝ ኖሮ የፅዳት ሠራተኛና ተላላኪ ሆኜ እቀር ነበር; አለው፡፡
የታሪኩ ማጠንጠኛ
ቴክኖሎጂን የሁሉም ነገር መቋጫ፤ የዕውቀት ጥግ፤ የስኬት ምንጭ አድርጎ መቁጠር እየተለመደ መምጣቱን፤ ሆኖም ግን ቴክኖሎጂ በራሱ ብቻውን የሀብት፣ የስኬትና የደስታ ምንጭ አለመሆኑን ከላይ የቀረበው ታሪክ ያሳያል፡፡
የለተሰንበትም ሆነ የተላላኪው ከበርቴ ታሪክ የሚያሳየን ነገር፣ የስኬት ምሥጢሩ በእጃችን ባለው ነገር ጠንክሮ መሥራት መሆኑንና ውጤቱ ደግሞ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚመጣ ነው፡፡
እንደገና ወደ ለተሰንበት፡- ምናባዊ ዕይታ
ልክ እንደ ኢንሹራንስ ሠራተኛው፣ አንድ የማኀበራዊ ድረ-ገፅ የቴክኖሎጂ አፍቃሪ “ጋዜጠኛ“ ለተሰንበትን ቢያገኛት የመጀመሪያ ጥያቄው "የማኀበራዊ ድረገፅ ተጠቃሚ ብትሆኚ ስንት መቶ ሺህ ተከታዮች እንደሚኖሩሽ ገምተሽ ታውቂያለሽ?" የሚል ይሆን ነበር፡፡
እሷም ትኩር ብላ ከተመለከተችው በኋላ፤ "አላውቅም፡፡ ነገር ግን ትልቁ ሃሳቤ ተከታዬን ማብዛት ሳይሆን የዓለም ክብረ ወሰንን ማሻሻል ነው" ትለው ነበር፡፡

Read 7721 times