Tuesday, 20 October 2020 00:00

የአበበ ቢቂላ ያልተነገረ የስኬት ምሥጢር እና “የዘንድሮው ኦሎምፒክ”

Written by  አበበ ገ/ህይወት
Rate this item
(1 Vote)

   አብዛኞቻችን ስለ አበበ ቢቂላ የምናውቀው የማራቶን ጀግና መሆኑን ነው፡፡ እሱ ግን ከዛም በላይ ነበር፡፡ በዓለም ላይ አንዱና ታላቁ የስኬት ምሥጢር ተብሎ የሚታወቀውን፣ ነገር ግን በተግባር ለማስረዳት አስቸጋሪ የሆነውን ሃሳብ በተግባር ያሳየ፤ ሃሳቡን ለማስረዳትም ጥሩ ምሳሌ ሆኖ የቀረበ የማራቶን ሩጫ ጀግና ብቻ ሳይሆን የስኬትን ምሥጢር በተግባር የተረጎመ፣ የጀግኖች ጀግና የሆነ የተለየ ሰው ነበር፡፡
ሃሳቡ
“ባለህበት ሥፍራ ሆነህ፣ አጠገብህ ባለው ነገር ተጠቅመህ፣ የምትችለውን ሁሉ ካደረግክ፤ ከዚያ በኋላ ፈጣሪ ባለህበት አይተውህም፡፡ ያለህ ላይ ጨምሮ ከፍ ያደርግሃል”፡፡
ሃሳቡ ሲተገበር
አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ በማራቶን ሩጫ ለመወዳደር ሲዘጋጅ፣ ስለ እሱ ምንም የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡ ከውድድሩ በፊት በአሰልጣኞቹ ሻለቃ ኦኒ ኒስከንና በንጉሴ ሮባ የተሰጡትን ልምምዶች ከጓደኞቹ ጋር በስነ ስርዓት ተከታትሏል፡፡ የውድድሩ ሰሞንም በይድነቃቸው ተሰማና በፍቅሩ ኪዳኔ ስለ ውድድሩ አጠቃላይ ሁኔታ የተነገሩትን ነገሮች ከልብ አድምጧል።
አቤ አንድ ነገር ብቻ አልተመቸውም። በጫማ መሮጥ፡፡ ጫማ የለኝም በሚል ምክንያት ደግሞ ከውድድሩ ውጪ መሆን አልፈለገም፡፡ ውድድሩ ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ውድድር ቢሆንም፣ በውድድሩ ህግ በባዶ እግር መሮጥ ደግሞ አልተከለከለም፡፡
ስለዚህ አበበ በባዶ እግሩ ከመሮጥ ውጪ ሌላ አማራጭ ስላልነበረው፣ በባዶ እግሩ ለመሮጥ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ወሰነ፡፡ ጥርሱን ነክሶ የሚችለውን ሁሉ ካደረገ፤ ፈጣሪ ጥረቱን እንደሚባርክለት በሙሉ ልቡ አመነ። ስለዚህ ውሳኔውን ለአሰልጣኞቹ አሳውቆ ሰውነት ማማሟቁን ቀጠለ፡፡ ውድድሩ ተጀመረ፤ ከዚያ በኋላ የሆነው ነገር ሁሉ በኦሎምፒክ ታሪክ በወርቅ ቀለም ተዘርዝሮ ሰፍሯል፡፡ ይህንን ጉዳይ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና ፍቅሩ ኪዳኔ ሲያቀርቡት መስማት ልዩ ስሜት ይፈጥራል፡፡ በቅርቡ ሸገር 102.1 ሬዲዮ ላይ ስለ የሮም ኦሎምፒክ ድል የ60ኛ ዓመት መታሰቢያ በፍቅሩ ኪዳኔ ተዘጋጅቶ፣ በተፈሪ አለሙ የተቀናበረው ዝግጅት ብዙ ትዝታዎችን ይቀሰቅሳል፡፡
ወጋችንን ለመቀጠል ያህል፡-
አበበ በባዶ እግሩ ማራቶንን ያህል ሩጫ (42ኪ.ሜ) ሮጦ መጨረሱ ሳይበቃ፣ በውድድሩ የማሸነፉን እንዴትነት አዘጋጆቹና ተመልካቾቹ አሰላስለው ሳይጨርሱ፣ ያስመዘገበው ውጤት አዲስ የማራቶን ክብረወሰን መሆኑ ሌላ ግርምት ፈጠረ፡፡
ይህ ሰው አንዳች ችግር ያጋጥመዋል ብለው በመጠባበቅ ላይ እያሉ፤ እሱ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ሰውነቱን ለማቀዝቀዝና ለማፍታታት የሚረዱትን እንቅስቃሴዎች ማድረጉን ተመለከቱ፡፡ ያዩትን ነገር ማመን ቢያቅታቸውም፣ በልዩ አድናቆት ስታዲየሙን ከዳር እስከ ዳር በጩኸትና በጭብጨባ አናጉት፡፡
የዚያን እለት ምሽት አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ ራሱን፣ አገሩን፣ አፍሪካንና መላውን ጥቁር ሕዝብ የሚያነቃቃ አኩሪ ታሪክ አከናወነ፡፡
ከአራት ዓመታት በኋላ
ከአራት ዓመታት በኋላ አበበ ቢቂላ ሌላ አስደናቂ ታሪክ በቶኪዮ ኦሎምፒክ አሳየ። የቀዶ ጥገና ህክምና በተደረገለት በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በድጋሚ በማራቶን ሩጫ ውድድር አሸነፈ፡፡ በዚህም ወቅት ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የራሱን ሪከርድ አሻሻለ፡፡ ከፍተኛ አካላዊ ብርታትና የመንፈስ ፅናት በሚጠይቅ ውድድር፣ በዚህ ሁኔታ ማሸነፉ እንደ ተዓምር ተቆጠረ፡፡
አበበ ቢቂላ ለአገሩ ኢትዮጵያ የዋለላት ውለታ፤ በሁለት የኦሎምፒክ ውድድሮች፣ በተከታታይ ሪከርድ በማሻሻል የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት፣ የአገሩ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ ብቻ አይደለም፡፡ ታላቁ የአበበ ስኬት ለተተኪዎች የአሸናፊነት ምሥጢርን ያሳየበት መንገድ ነው፡፡ በማራቶን ሩጫ ተወዳድሮ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በባዶ እግርም ሮጦ ማሸነፍ እንደሚቻል፤ አንደኛ መውጣት ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ሪከርድ ማሻሻል እንደሚቻል፤ ከበሽታ ሙሉ ለሙሉ ሳያገግሙም ቢሆን ማሸነፍም ሪከርድ መስበርም እንደሚቻል አሳይቷል፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ በሩጫ ውድድሮች ላይ የሚሰማንን የአሸናፊነት መንፈስ ያላበሰን የአበበ ቢቂላ “ከሚጠበቀው በላይ” (Extra Ordinary) የሆነ የጀግንነት ተግባር ነው፡፡
ከድሉ ጀርባ የነበረው ምሥጢር ለ60 ዓመታት ይዞን ተጉዟል፡፡ ምሥጢሩ የተገለጠላቸው (ምሩፅና የአረንጓዴ ጎርፍ ጓደኞቹ፣ ኃይሌና ዘመነኞቹ፣ ደራርቱ፣ ፋጡማና አቻዎቻቸው፤ የኦሎምፒክ ልዩ ፈርጦቹ ጥሩዬና ቀነኒሳ፤ መሠረት፣ አልማዝ እና ሌሎችም በቅብብል አሁን ያለንበት ጊዜ አድርሰውናል፡፡
“ባለህበት ሥፍራ፣ ባለህ ነገር፣ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፡፡ ቀሪውን ለፈጣሪ ተወው” የሚለውን ብሂል በተደጋጋሚ በተግባር በማሳየቱ አበበ ቢቂላን የማራቶን ጀግና ብቻ ሳይሆን የጀግኖች ጀግና ብለን እንድንጠራው ያስገድደናል፡፡
እግረ መንገድ፡ “የዘንድሮ ኦሎምፒክ”
አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ በማራቶን ካሸነፈ ዘንድሮ 60 ዓመት ሆነው፡፡ ቀጣዩ ኦሎምፒክ በዚህ በያዝነው ዓመት አበበ ቢቂላ ሁለተኛ የማራቶን ድል በተቀዳጀበት በቶኪዮ ከተማ ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በአገራችን የስፖርት መንደር በተለይ ደግሞ ከፍተኛ የህዝብን ስሜት በሚገዙት የእግር ኳስና የአትሌቲክስ ስፖርቶች አካባቢ ያለው ትርምስ አላቋረጠም፡፡
 በቅርቡ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኦሎምፒክ ማኀበር መካከል ተፈጥሮ የነበረው እሰጥ-አገባ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን አስደንጋጭም ነበር፡፡ “እድሜ ለኮሮና” አይባልም እንጂ ውዝግቡ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ከሯጮቻችን የምናገኘውን የደስታ ትሩፋት ሊነጥቀን አይኑን-አፍጥጦ፣ ጥርሱን-አግጥጦ ከፊታችን ተደቅኖ ነበር፡፡
ትንሽ ሰለ ኮሮና፡-
በዓለም ላይ በኮሮና ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን በሙሉ፣ በተለይ ደግሞ በአገራችን ከዚሁ ችግር ጋር ተያይዞ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በህሊና ማሰብ፤ የሞቱትን ነፍስ ይማር ማለት፣ ለታመሙት ምህረትን መለመን ሰብዓዊ ግዴታችን ነው፡፡ ከጥንቃቄ፤ ከሀኪሞች ምክርና እገዛ ጎን ለጎን፣ የፈጣሪን ዕርዳታና ምህረት ለማግኘት በርትቶ መፀለይም ተገቢ ነው፡፡
እንደገና ወደ ኦሎምፒክ፡-
አብዛኛው የስፖርት አፍቃሪ፣ ስፖርትና ፖለቲካ ተቀላቅለው ማየት አይሻም። አስተዳደራዊ ሥራውም ስፖርትንና የኦሎምፒክን መንፈስ የተከተለ ቢሆን ጥቅሙ ለአገር ነው ብሎ ያምናል፡፡ የኦሎምፒክ ማኅበሩ ኃላፊዎች ኢትዮጵያ፣ አትሌቲክስና ኦሎምፒክ ያላቸውን ስሜታዊ ቁርኝት በአግባቡ ሊረዱት ይገባል፡፡በቀድሞ ጊዜ የኦሎምፒክ ማኀበሩ ዋና ሥራ ድጋፍ ማፈላለግና አጠቃላይ ጉዳዮችን ማስተባበር ነበር፡፡ ዘንድሮ ወደ ዝርዝር አጠቃላይ ጉዳዮች ውስጥ ሲገባ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ግጭት ተፈጠረ፡፡
አሁንም ጊዜው አልረፈደም፡፡ ለፌዴሬሽኑና ለአትሌቶቹ ነፃነታቸውን መተው፡፡ እነሱ የአሸናፊነቱን ምሥጢር ከአበበ ቢቂላ ተገንዝበውታል፡፡ የቻሉትን ያህል ይጥራሉ፤ በእጃቸው ባለው ነገር ይጠቀማሉ፤ ባሉበት ስፍራ ጠንክረው ይሰራሉ፣ ቀሪውን ለፈጣሪ ይተዋሉ፡፡ ውጤቱንም በኦሎምፒክ መንፈስ በፀጋ ይቀበላሉ፡፡
እንደ መውጫ፡-
መንግሥት የሚታዩ መልካም አጋጣሚዎችን መረዳት ይሳነዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ ሆኖም ግን መጪውን ኦሎምፒክ ለኢትዮጵያ እንደመጣ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር፣ ኦሎምፒክን ለፍቅርና ለአገራዊ አንድነት መጠቀም ስለሚቻልበት መንገድ የቅርብ ክትትል ማድረግ ብልህነት ይሆናል፡፡
ኦሎምፒክንና አትሌቲክስን በአራት ዓመት አንዴ የምንናፍቀው አገራዊ ጉዳይ እንዲሆን ፋና-ወጊ ለሆነው አበበ ቢቂላ ክብርና ምሥጋና ይሁን!!


Read 943 times