Monday, 19 October 2020 00:00

የትግራይ ፖለቲካና መጪው ምርጫ - ተፎካካሪ ፓርቲዎችስ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  • ሀገሪቱ ለምርጫ ዝግጁ ነች ብለን እንደ ፓርቲ አናምንም
      • የህወኃትን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ለማፍረስ ነው ጥረታችን
      • መንግስት ትከሻ መለካካት ውስጥ ሳይገባ እርምጃ ይውሰድ

         የትግራይ ክልላዊ መንግስት የራሱን ምርጫ አድርጐ መንግስት መመስረቱን በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ ፌደራል መንግስቱ በበኩሉ፤ የተመሠረተው ህገ ወጥ መንግስት ነው፣ ለህገ ወጥ መንግስት በጀት አልመድብም ሲል በጀት በቀጥታ ለህዝብ የሚደርስበትን መንገድ አመቻቻለሁ ብሏል፡፡ 6ኛው አገራዊ ምርጫም በትግራይ እንደሚካሄድ አስታውቋል፤ ፌደራል መንግስቱ፡፡ በእርግጥ በትግራይ ቀጣዩን ምርጫ ማካሄድ ይቻላል? እንዴት? የበጀት እገዳው የክልሉ መንግስት ላይ ምን ተጽእኖ ይፈጥራል? የትግራይ ፓርቲዎች ለምርጫው በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ዕድል ይኖራል? የፌደራል መንግስትና የህወሃት መራሹ ክልላዊ መንግስት ፍጥጫ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚቋጨው መቼ ነው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ም/ሊቀ መንበር አቶ መስፍን ደሳለኝ ጋር በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡

           ፓርቲያችሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚሳተፍበት ምርጫ እንዴት እየተዘጋጀ ነው?
እኛ ባለን አቅም ሁሉ እየተዘጋጀን ነው፤ ነገር ግን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ያለው ችግር ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አይመስለንም። አለመረጋጋት በየቦታው አለ፡፡ የብሔር፣ የፖለቲካ የመሳሰሉ ግጭቶች በየቦታው ይከሰታሉ፡፡ ላለፉት 30 አመታት በሀገሪቱ የተከማቹ ችግሮች አሉ፤ እነሱን ለመፍታት ብዙም ጥረት እየተደረገ አይደለም፡፡ አሁን ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሂደት በሃቅ የሚወስደን መሆን አለበት፡፡ ከአሁን ቀደም እንደነበረው ዓይነት የውሸት ምርጫ ብናደርግ ለህዝቡ የምናመጣው ምንም ውጤት አይኖርም። ስለዚህ አስቀድሞ መፈታት ያለባቸው በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ለምርጫው ሀገሪቱን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
መፈታት ያለባቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?
ከዚህ በፊት ምርጫ ቦርድ ራሱ የዘረዘራቸው ችግሮች አሉ፡፡ ስጋቶች ብሎ ያቀረባቸው ነገሮች በትክክል ተቀርፈዋል ወይ? የሚለው በራሱ አጠራጣሪ ነው። አንዱ የተጠቀሰው የፀጥታ ችግር ነው፡፡ ራሱ ምርጫ ቦርድ የፀጥታ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫውን ማስፈፀም ይችላል ወይ? የሚለው ለኛ ስጋት ነው፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ራሳቸውስ የመፎካከር አቅም ፈጥረዋል ወይ? መገናኛ ብዙሃንና የዲሞክራሲ ተቋማት ምን ያህል ገለልተኛ ሆነዋል? እርግጥ ነው መንግስት የራሱን ጥረት እያደረገ ነው፤ ነገር ግን ይህ ጥረት በሚፈለገው ልክ ውጤት እያመጣ ነው ወይ? የሚለው በአጠቃላይ ሲገመገም በርካታ ጉዳዮች ይቀራሉ። ከፀጥታ ችግሮች፣ ከተቋማት ዝግጁነትና ከመሳሰሉት ጉዳዮች አንፃር ሀገሪቱ ለምርጫ ዝግጁ ነች ብለን እንደ ትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አናምንም። እንደሚታወቀው እኛ የክልል ፓርቲ ነን። ልንወዳደር የምንችለው ትግራይ ውስጥ ነው፡፡ ትግራይ ደግሞ ያለው ነገር ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ እንኳን እኛ እዚያ ገብተን ልንወዳደር ይቅርና ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ራሱ እዚያ ገብቶ መወዳደር የማይችልበት ሁኔታ ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡ የምርጫ ቦርድማ ምንም አይነት ተሰሚነት የለውም በክልሉ፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ነው እውነተኛ ምርጫ ሊደረግ የሚችለው። እንኳን እውነተኛ ምርጫ ሊደረግ ይቅርና እንደ ድሮው የውሸት ምርጫ እንኳ ማድረግ አይቻልም፡፡ የምርጫ መጫወቻ ህጉን በአምባገነንና በፍፁም ስርአት አልበኝነት ህወኃት እየጣሰ ነው፡፡ በትግራይ የፖለቲካ ምህዳሩ ዝግ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምርጫን በትግራይ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ምንም ፋይዳ የለውም፡፡
በእናንተ በኩል በትግራይ መዋቅር ለመዘርጋት ምን ያህል ጥረት አድርጋችኋል?
ከዚህ ቀደም ቢሮዎች ጭምር ከፍተን እየተንቀሳቀስን ነበር፡፡ በምንችለው አቅም አባላት አፍርተን ለመንቀሳቀስ እየሞከርን ነው። ሃሳባችንን ህዝቡ ዘንድ ለማድረስ የቻልነውን ሁሉ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ይሄን የምናደርገው እዚያ ባሉ አባሎቻችን አማካይነት ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ከትግራይ ውጪ ባሉ ከተሞችም የክልሉን ተወላጆች እያወያየን ነው፡፡ አዳማ፣ ጅማ፣ ሀረር፣ ጐንደር፣ አፋር የመሳሰሉት አካባቢዎች እየተንቀሳቀስን በትኩረት እየሰራን ነው፡፡
ከትግራይ ውጪ ያሉ የትግራይ ተወላጆችን ማነጋገሩ ምንድን ነው ፋይዳው? ምርጫው ላይስ ምን ተጽእኖ ይኖረዋል?
በሌላ አካባቢ ያለው የትግራይ ተወላጅ በተነዙበት የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳዎች የተነሳ ብዙ ስጋቶች ነበሩበት፡፡ በህወኃት በኩል በሌሎች ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተደርጐ ነው የሚቀርበው፡፡ ፓርቲና ህዝቡ አንድ ነው እያለ የሚሰብከውም ህዝቡን ከሌሎች ህብረተሰቦች ጋር ለማጋጨት ነበር፡፡ ይሄ አልተሳካላቸውም። እኛም ህዝቡ ያለምንም ስጋት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እንዲኖር ነው እያወያየን ያለነው፡፡ ህዝቡን የማረጋጋት ስራ ነው እየሠራን የምንገኘው። ግንዛቤ ነው እየፈጠርን ያለነው። የተሳሳተ አመለካከትን ማስተካከላችን በራሱ ለምርጫ በምናደርገው ውድድር ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ የህወኃትን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ለማፍረስ ነው ጥረታችን፡፡ ህዝቡ የህወኃትን የሸፍጥና የሴራ መንገድ እንዲረዳ ነው ጥረት እያደረግን ያለነው፡፡
መጪው አገራዊ ምርጫ በትግራይ ምን መልክ ይኖረዋል?
ሁኔታው ከባድ ነው፡፡ ብልጽግና ራሱ ትግራይ ገብቶ ለመንቀሳቀሱ እርግጠኞች አይደለንም፡፡ እነዚህ ሰዎች ህግ ጥሰው ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ "የውሸት ምርጫ" አካሂደዋል፡፡ የፌደራል መንግስት ምርጫው ህጋዊ አይደለም ብሏል፡፡ ስለዚህ ሁኔታው የገመድ ጉተታ ውስጥ ነው ያለው፡፡ በዚህ መሃል ስለ ምርጫ ማውራት ሳይሆን ስለ ሀገር አንድነት ነው ማውራት የሚሻለው፡፡ እንዴት ነው የህዝቡ ደህንነት የሚወሰነው? እንዴት ነው ሠላምና መረጋጋት የሚመጣው? እንዴት ነው የሀገር አንድነት ሊጠበቅ የሚችለው? የሚለው ላይ ነው ማተኮር ያለብን፡፡  
በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው ችግር እንዴት ይፈታል ብላችሁ ታስባላችሁ?
መፍትሔው መነጋገር ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ለውይይት ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው። ችግሩ በድርድርና በንግግር የሚፈታበትን መንገድ በቅድሚያ መፈለግ ያሻል፡፡ በዚህ በኩል ያለው ጥረት ከተሟጠጠ በኋላ ግን ህግን የማስከበር እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ ይሄን የፌደራል መንግስቱ ማረጋገጥ አለበት፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት በጀት የማገድ እርምጃ ወስዷል፡፡ ውሳኔው ለውጥ የሚያመጣ ይመስላችኋል?
ህወኃት በብርጭቆ ውስጥ ያለ አካል ነው፡፡ ብርጭቆው ህዝቡ ነው፡፡ ስለዚህ በብርጭቆው ውስጥ ያለውን አካል ለማግኘት ብርጭቆው መጐዳት አለበት ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ የማይሆን የማይታሰብ ነው። ህወኃትን ለመጉዳት ተብሎ ህዝቡን መጉዳት አያስፈልግም፤ ትኋንን ለማጥፋት ተብሎ ሙሉ ቤት አይቃጠልም፡፡ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሰዎች የህዝቡ መጐዳት የሚያሳስባቸው አይደሉም፡፡ ህዝቡንም ለጦርነት ሊቀሰቅሱት ይችላሉ። ስለዚህ በጣም ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድን መከተል ያስፈልጋል፡፡ ለወረዳ በጀቱን በቀጥታ አደርሳለሁ ማለት ከባድ ነው። መዋቅሩ በሙሉ በህወኃት እጅ ነው ያለው፡፡ 1ለ5 በሚል ህወኃት ሁሉንም ተቆጣጥሮታል። ስለዚህ በጀቱን በቀጥታ ለወረዳዎች በሚል የተቀመጠውን መፍትሔ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡  
ምንድን ነው አስቸጋሪ የሚያደርገው?
አንደኛ፤ፓርቲና ህዝብ አንድ ነው ተብሎ እሳቤ ተይዟል፡፡ የፓርቲው አቋም፤ የህዝቡ ሁሉ አቋም ነው ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ፓርቲና ህዝብ ባልተለየበት፣ ህዝብን ለይቶ መርዳት የሚቻልበት ሁኔታ ጠባብ ነው። የመዋቅርና ስርአት ችግር አለ፡፡ በስርአቱ መዋቅር ውስጥ ያሉት እነሱና እነሱ ብቻ ናቸው፤ ህዝቡን ማን አድርሶት!
ታዲያ ምን ይበጃል ይላሉ?
ይሄን ስራ የሚሠራ ኮሚቴ መቋቋም ነው ያለበት፡፡ ከሁሉም አካላት የተውጣጣ አካል በድርድር መፈጠር አለበት፡፡ ህወኃት ብቻውን ብዙ ነገር ተቆጣጥሯል። ሌላው መፍትሔ የፌደራል መንግስት ከዚህ በኋላ ትከሻ መለካካት ውስጥ ሳይገባ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ የበለጠ ሃይልና የማስፈፀም አቅም ያለው ፌደራል መንግስት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብ በማይጐዳበት መንገድ ፌደራል መንግስቱ ህግን ማስከበር አለበት። አምባገነኖች ዲሞክራሲያዊ ሆነው አያውቁም፤ የህወኃትም ታሪክ እንደዚያው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ሠላማዊ መንገድ ይመጣሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ችግሩ አስተሳሰባቸው ላይ ስለሆነ ነገሩ ከምንጩ ነው መድረቅ ያለበት፡፡ ችግር በመጣ ቁጥር እሳት እያጠፉ የሀገሪቱን ችግር በዘላቂነት መፍታት አይቻልም፡፡
በተደጋጋሚ መንግስት ህግን ያስከብር ይባላል፡፡ ህግን ያስከብር ሲባል እንዴት ነው? የሃይል አማራጭን መጠቀም ማለት ነው
የሃይል አማራጭ የትም አለም ላይ ያለ ነው። አሁን ትልቁ ጥንቃቄ ህዝብ እንዳይጐዳ ነው እንጂ የሃይል አማራጭ መጠቀም የማያዋጣ ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን ህዝቡን ተከልለው ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ህዝቡ በቀጥታ ሊጐዳ ይችላል፡፡ ነገር ግን በሠላም የማይቻል ከሆነ፣ የግድ በሃይል መፍታት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ በተለያዩ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች እየተፎካከሩ በመሃል የህዝቡ ስቃይ እየተጠናከረ የሚቀጠልበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡ ወይ ተባብሮ መኖር ወይም በሃይል ሠላም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
ህዝባችን ግን የማይፈለግ ዋጋ እንዳይከፍል ከወዲሁ ማሰብ ያስፈልጋል። በፉክክር ህዝብ እንዳይራብ፣ ብዙ ችግር እንዳይደርስበት ነው የበለጠ የሚያሠጋው። ቅድሚያ በውይይት በድርድር ለመፍታት መሞከር ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ወደ መሃል የሚመጣበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ነው። ካልሆነ ግን የህዝብን ስቃይ ላለማራዘም፣ የሃይል እርምጃ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡
የፈንቅል እንቅስቃሴ ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት አላችሁ?
ህወኃት የተለየ ሴራ የሚጠቀም ድርጅት ነው። የተደራጀ ህዝብ እንደሚያጠፋው ስለሚያውቅ ህዝብ እንዲደራጅ አይፈቅድም። ህዝቡንም በሌላ ውሸት፣ በተለየ  የፕሮፓጋንዳ  ስልት  ያልሆነ አስተሳሰብ ውስጥ እያስገቡት ነው። በትግራይ ያለውን ነገር የተለየ የሚያደርገው፣ አብዛኛውን ህዝብ በቀጥታ የእነሱ ጥገኛ አድርገውታል፤ በሴፍቲኔት በመሳሰሉት ጥገኛ ሆኗል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ያለ ጠላት መኖር የማይችል ጽንሰ ሃሳብ በመሆኑም፣ ለህዝቡ ጠላት እየፈጠሩለት ጥገኛቸው እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ከዚህ አንፃር ፈንቅልም ሆነ ሌሎች የተለየ አደረጃጀትና ማስተዋልን ካልተከተሉ በስተቀር በቀላሉ ውጤት ማምጣት አስቸጋሪ ነው፡፡ የህወኃትን አቅም አስቀድሞ መገንዘብና የተሻለ ሆኖ ለመውጣት መሬት ላይ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ህወኃት ማለት ሀገር ሙሉ ሲያስተዳድር የነበረ፣ ደህንነት በውስጡ ያለ ነው፡፡ አሁን ያ ደህንነት ትግራይ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሀገር ሙሉ በሴራ ሲመራ የነበረ ሃይል እዚያ ነው ያለው፤ ይሄንንም ማሰብ ያስፈልጋል።
መጪው ምርጫ በትግራይ ሊካሄድ አይችልም እያሉኝ ነው?
አሁን ባለው ሁኔታ በትግራይ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡ በመጀመሪያ ችግሩ እልባት ማግኘት አለበት፡፡ እኛ ትግራይ ሄደን አባላትና መራጭ አደራጅተን እንድንወዳደር ከተፈለገ፣ ፌደራል መንግስትና ምርጫ ቦርድ ዋስትና ሊሰጡን ይገባል፡፡
እነዚህ አካላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ህወኃትን ስርአት ማስያዝ ይችላሉ ወይ? ነው ጥያቄው። ህወኃትን ስርአት የማያሲዙ ከሆነ ግን ስለ ምርጫ ማውራት አይጠቅምም፡፡ በአጠቃላይ አሁን ባለው ሁኔታ የትግራይን ችግር ምርጫ አይፈታውም። ችግሩ በምርጫ የሚፈታ አይደለም፡፡ ሌሎች የህግ መፍትሔዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ህወኃት ከ40 አመት በላይ በሚገባ የተደራጀ ሴረኛ ድርጅት ነው፡፡ ይሄ ድርጅት ባለበት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚታሰብ አይደለም፡፡ እንኳን እኛ የብልጽግና ፓርቲም በትግራይ ያለውን ነገር በምርጫ መፍታት አይችልም፡፡  

Read 2734 times