Print this page
Monday, 19 October 2020 00:00

የከሸፈው "የሽግግር መንግሥት" መግለጫ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  የአፍሪካ የሰብአዊ መብት ሊግ፣ ዳውድ ኢብሳ መታገታቸውን ተቃወመ

        የምስራቅ አፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ሊግ የተሰኘው ተቋም ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም በአቶ ዳውድ መኖሪያ ቤት ተከሰተ የሚለውን ጉዳይ በዝርዝር የሚያትት ሪፖርት ያወጣ ሲሆን፤ በአቶ ዳውድና ጋዜጣዊ አመራራቸው ላይ እየተፈፀመ ያለው ወከባ እንዲቆም ጠይቋል።
ሰኞ ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ከኦነግ ሊቀ መንበርነታቸው የታገዱት አቶ ዳውድ ኢብሣ፤ “የኦሮሚያ ብሔራዊ የሽግግር መንግስት” መቋቋሙን አስመልክቶ  ለጋበዟቸው ጋዜጠኞች መግለጫ መስጠት ይጀምራሉ - አስቀድሞ በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት፡፡
በዚህ “የኦሮሚያ ብሔራዊ የሽግግር መንግስት’’ መቋቋሙን በሚያውጁበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ቄሮዎች፣ ቀሬዎች፣ የኦነግ አመራሮችና አባላት፣ የኦሮሞ ነፃነት ድምጽ ጋዜጠኞች መገኘታቸውን ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡
አቶ ዳውድ ኢብሣ መግለጫቸውን እንደጀመሩ ግን ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ፣ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች መግለጫው የሚሰጥበት ክፍል ሰተት ብለው ይገባሉ፣ ጋዜጠኞቹ ቤቱን ለቀው እንዲወጡም ትዕዛዝ ይሰጣሉ፤ ጋዜጠኞቹንም አስረው ይወስዷቸዋል፡፡
የታሠሩት የኦሮሞ ነፃነት ድምጽ ጋዜጠኞች ሁለት ሲሆኑ እነሱም ዋቆ ኖሌ እና ኢብሣ ጋዲሳ ናቸው ይላል ሪፖርቱ፡፡ ሌሎች አራት የስብሰባው ተሳታፊ ጋዜጠኞችም ማለትም፡- አባ ቢሊሱማ፣ ቢቂላ አማኑ፣ ደሶ ብርሃኑ እና ወጋየሁ ንጉሴም አብረው መታሠራቸው ተጠቁሟል፡፡ ሌሎች የመግለጫው ተሳታፊዎች ግን ከቤቱ እንዳይወጡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው ይላል ሪፖርቱ፡፡ ወዲያው በመቶዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ የፀጥታ ሃይሎች የአቶ ዳውድ ኢብሣን መኖሪያ ቤት የከበቡ ሲሆን ከዚያ በኋላ ወደ ቤት መግባትም ሆነ ወደ ውጪ መውጣት መከልከሉን ነው የሰብአዊ መብት ተቋሙ ሪፖርት ያመለከተው፡፡
በዚህም የተነሳ ቤት ውስጥ የቀሩት የመግለጫው ተሳታፊዎች አዳራቸውንም በዚያው ለማድረግ ተገደዋል ይላል። በበነጋው ማክሰኞ እለት፣ በቤቱ ያደሩ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች ቤቱን ለቀው ለመሄድ ሲሞክሩ ወደ ውጪ ይወጣሉ፡፡
በፀጥታ ሃይሎች ተይዘው የተወሰዱ ሲሆን በኋላ ላይ ግን  መለቀቃቸውን ሪፖርቱ አትቷል፡፡
የአቶ ዳውድ ኢብሣ መኖሪያ ቤት ግን ሪፖርቱ እስከተጠናቀረበት ከትናንት በስቲያ ድረስ በፀጥታ ሃይሎች እንደተከበበና ወደ ውስጥ መግባትም ሆነ  መውጣት መከልከሉን የሚያትተው  የሰብአዊ መብቶች ሊጉ፤ መንግስት አቶ ዳውድ ኢብሣን የቁም እስረኛ ማድረጉን እንዲያቆምና የታሠሩ ሁሉ እንዲፈቱም ጠይቋል፡፡
ከአቶ ዳውድ ጋር በቤት ውስጥ ለቀሩ ሽማግሌዎችም አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግና በሀገሪቱ ቀጣይ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ውይይቶች እንዲካሄዱ ሃሳብ  አቅርቧል።  

Read 11343 times