Monday, 19 October 2020 00:00

በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመንና በሳኡዲ ድንበር መሃል ታግተዋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን  ስደተኞች በሳኡዲ መንግስትና በየመን ሀውቲ አማጺያን መካከል ባለው ጦርነት ምክንያት ለእንግልት፣ለእስርና ሞት መዳረጋቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች አስታውቋል።
 አለማቀፍ የሰብአዊ  መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ በሁለቱ ሃይሎች ጦርነት መሀል አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ኢትዮጵያውያንን አነጋግሮ ባዘጋጀው ሰፊ  ሪፖርት፤ በየመን በኩል ድንበር ጠባቂዎች አግተዋቸው ስደተኞች ጭንቀት ውስጥ ከቷቸዋል ብሏል።
  በሁለቱ አካላት ጦርነት መካከል በርካታ ኢትዮጵያውን መገደላቸውን፣ በተለያዩ እስር ቤቶች የተወረወሩም ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ በዝርዝር የገለጸው የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት፤ ኢትዮጵያውያኑ ያሉበት ሁኔታ እጅግ የከፋ መሆኑን ያመለክታል።
  ኢትዮጵያውያኑ በመጀመሪያ ከሰሜን የመን  በሁቲ አማጽያን  ጥቃት ተባረው ወደ ሳኡዲ ድንበር መሸሻቸውን በሳኡዲ ድንብር ያሉ የሀገሪቱ ጠባቂዎች በፊናቸው ወደ ኋላ እንዲመለሱ በማድረግ ጥቃት መክፈታቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፤ኢትዮጵያውያኑ  በአሁኑ ወቅት በዚሁ ጭንቀት   ውስጥ ይገኛሉ ብሏል።
“የሁቲ አማጽያን ከተቆጣጠሩት ስፍራ እንድንወጣላቸው ተኩስ ከፍተውብን እንድንሸሽ ካደረጉን በኋላ እግራችን ወደ መራን ወደ ሳኡዲ ድንበር ስንሸሽ ከፊት ለፊታቸን ያጋጠመን ተራራ ነው ከዚያም ተራራው አናት ላይ ደግሞ የሳኡዲ ወታደሮች ቁልቁል እየተኮሱብን ወደኋላ እንድንመለስ እያደረጉን ነው’’  ሲል አንደኛው ስደተኛ ለሂውማን ራይትስ ዎች የምርመራ ቡድን በስልክ አስረድቷል ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ  መሆናቸውን በመግለጽ አለማቀፍ አካላት እንዲደርስላቸው   ተማጽኖ አቅርበዋል ።
በተመሳሳይ ቀደም ባለው ሳምንት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ                 አመንስቲ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያውያኑ ጭንቀት ውስጥ መሆናቸው ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን   የአውሮፓ ፓርላማ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
የሳኡዲ መንግስት በኢትዮጵያውያኑ ላይ የሚፈጸመው ኢ-ሰብዊ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆምም የአውሮፓ ህብረት ድርጊቱን ባወገዘበት መግለጫው አሳስቧል።   


Read 1004 times