Monday, 19 October 2020 00:00

ለጤና ባለሙያዎች የብቃት ምዘና ሊሰጥ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

     ምዘናው የፊታችን ሰኞ ይጀመራል ተብሏል
                 
           የጤና ባለሙያዎች የብቃት ምዘና ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለአምስት ቀናት እንደሚከናወን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የብቃት ምዘናው በህክምና፣ በነርሲንግ፣ በፋርሚሲ፣ በጤና መኮንን፣ በአንስቴዥያ በህክምና ላብራቶሪ ቴክኖሎጂና በአዋላጅነት ሙያ ዘርፍ ለተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጥ ይሆናል ተብሏል፡፡ ምዘናው የሚሰጠው ከየትኛውም የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመጀመሪያ ድግሪ ለተመረቁ የጤና ባለሙያዎች እንደሆነም ይኸው የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
የብቃት ምዘናውን ለመውሰድ በተጠቀሱት የሙያ ዘርፎች 5991 የጤና ባለሙያዎች መመዝገባቸውንም ለማወቅ ተችሏል። ይኸው የብቃት ምዘናው በመላው አገሪቱ በተመረጡ 20 ጣቢያዎች እንደሚሰጥና ለዚህም ዝግጅቱ መጠናቀቁን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከላይ በተዘረዘሩት ዘርፎች 20ሺ 142 ባለሙያዎች የብቃት ምዘናውን እንዲወስዱ መደረጉንና ከእነዚህ መካከል 61.4 በመቶ የሚሆኑት ምዘናውን ማለፋቸውን  የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዘንድሮ ሰኔ ወር ጀምሮም የጥርስ ህክምናና የራዲዮሎጂ የሙያ ዘርፎች በብቃት ምዘናው እንዲካተቱ ለማድረግ መወሰኑንም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

Read 1150 times