Print this page
Tuesday, 13 October 2020 15:06

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(6 votes)

 ህይወት ካላቸው የድሮ ቀልዶች አንዷን እናስታውስ፡- ሁለት የባለስልጣን ሚስቶች ልብስ ለማሰፋት ጨርቅ ቤት ገቡ አሉ፡፡ “ያንን አምጣ፣ ይኸን መልስ” እያሉ መምረጥ ጀመሩ። ነጋዴውም በመሰላሉ እየተንጠላጠለ የተሰቀለውን ሲያወርድ፣ ያወረደውን ወደ ቦታው እየመለሰ በማስተናገድ ላይ እያለ ድንገት ፈሱ አመለጠው፡፡ ይሄኔ ደንበኞቹ አፋቸውን ይዘው፡-
“ምነው አንተ?...በስማም!” ሲሉት… ምን ብሎ እንደመለሰላቸው ታውቃለህ?
*   *   *
ወዳጄ፡- ኮረና ያደበዘዛቸው አገራዊ ፕሮጀክቶች ቦግ፣ ቀና ማለት ጀምረዋል እንደገና፡፡ የታላቁ የዓባይ ግድብ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ የህዝብና የቤት ቆጠራ፣ የዕርቀ ሠላም ኮሚሽን ጉዳይ ወዘተ፡፡ አገራዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማድረግ መዘጋጀት ደግሞ ዓቢይ አጀንዳ ነው፡፡
ኮረና በአጭር ጊዜ ዓለምን ያዳረሰ ወረርሽኝ ነው፡፡ በሽታውን መመከት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ሆኖብን ነበር። ቆሞ ለማሰብ፣ ለማቀድና ስትራቴጂያዊ መከላከል ለማድረግ በቂ ፋታ እንኳ አልነበረም፡፡ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ የነበሩት ቀናት በጭንቀትና በተስፋ ምጥ የተሞሉ ነበሩ፡፡ “ዛሬ ስንት ሰው ተያዘ? ስንት ሰው ሞተ?” ስንት ሰው አገገመ?” ብሎ መጠየቅ ልማድ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የባለሙያ ምክር ማዳመጥና ራሳችንን መጠበቅ ለብዙዎቻችን እስከዛሬ ድረስ ፈተና ሆኗል፡፡
ኮረና አሁንም አለ፡፡ ከሰሞኑ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታላቅ መምህርና የመብት ተሟጋች ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ህይወታቸው ያለፈው በዚሁ በሽታ እንደሆነ በሚዲያ ሲነገር ሰምተናል፡፡ ነፍስ ይማር! ፕሮፌሰር!
ወዳጄ፡- የየራሳችንን የግል ህይወት በተቻለን መጠን በፈለግነው መንገድ መምራትና በነፃ አስተሳሰብ መዘወር መቻል ታላቅ በረከት ነው፡፡ መሞከር የኛ ኃላፊነት ሲሆን የመሳካትና ያለመሳካት ጉዳይ ግን ከቁጥጥራችን ውጭ የሆኑ ሁኔታዎችን መመቻቸት ይፈልጋል፡፡ ወላጆቻችን፤ “ሰው ያስባል እግዜር ይፈጽማል” እንደሚሉት፡፡
ወዳጄ፡- እንኳንስ የህይወት ጉዟችን፣ በማስመሪያችን የምናሰምረው መስመር መቶ በመቶ ቀጥተኛ ሊሆን እንደማይችል ሳይንስ ይመሰክራል፡፡ በገዛ ፎላጐታችንና ነፃ ፈቃዳችን የምንፈጽመው በጐም ሆነ ክፉ ተግባር ትክክል ነው ብሎ ማሰብ አእምሯዊ ደስታና ህመምን ያስከትላል፡፡ ስለዚህ ከማናቸውም ድርጊት ጀርባ ምክንያት መኖሩን አለመዘንጋት ከስህተት ያድናል። ፍቅርና ጥላቻ፣ ደስታና ሃዘንን ጨምሮ ሁሉም አጋጣሚ የሚታይና የማይታይ ሰበቦች አሉት… ከወላጅ ማህፀን እስከ እናት ምድር ከርስ ድረስ፡፡
There is in the mind no absolute or free will; but the mind is determined in willing this or that by a course, and a course by another course, up to infinity” በማለት የሚያረጋግጥልን ታላቁ ስፒኖዛ ነው፡፡
በልጅነቴ “Whose life is it anyway?” የሚል ሲኒማ ተመልክቼ ነበር፡፡ በፊልሙ ይዘት  የጽንሰ ሃሳብ ትርጉሙ:- “በኔ ህይወት ምን አገባችሁ?” እንደ ማለት ነው፡፡ ፊልሙ የሚያጠነጥነው በአንድ ኢንጅነር የህይወት ታሪክ ላይ ነው፡፡ ሰውየው ያለመታከት ለስራው ጐንበስ ቀና የሚል ነበር፡፡ አንድ ጐዶሎ ቀን ግን ድንገተኛ የመኪና አደጋ ደረሰበትና ሙሉ በሙሉ ፓራላይዝድ ሆነ። ትንሽ፣ ትንሽ ከመናገር በስተቀር ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻለም። የሆስፒታሉ ባለሙያዎች በከፍተኛ እንክብካቤ ሌት ተቀን ቢጠብቁትም፣ ሰውየው በዛ ሁኔታ መኖር ሰቀቀን ሆነበት። ከሆስፒታሉ መውጣት ፈለገ፡፡
ከሆስፒታል መውጣት ማለት “ሞት” ማለት እንደሆነ የሚያውቁት ሃኪሞች ተቃወሙ፡፡ ሰውየው ሆስፒታሉን ከሰሰ። ጉዳዩ ፍ/ቤት ቀርቦ በጉዳተኛው ጠበቃና በዋናው ሃኪም መሃል ከፍተኛ ክርክር ተዳረገ፡፡
ሃኪሞቹ “ሰውየውን በህይወት የማቆየት ስነሙያዊ ኃላፊነት (Ethical Oath) አለብን” በማለት ሲጋፈጡ፤ የኢንጅነሩ ጠበቃ ደግሞ በህይወት ያለመኖር መብቱ እንዲረጋገጥለት አጥብቆ ተሟገተ፡፡ ፍርድ ቤቱም ተዛማጅ ህጐችን ከመብት፣ ከሙያና ከሞራል ሥነምግባር አኳያ ከመረመረና ካገናዘበ በኋላ በቂ ትንታኔ በማቅረብ የኢንጂነሩ ፍላጐት እንዲከበር አዘዘ፡፡ ትዕዛዙም ተፈፀመና ሰውየው ከሆስፒታሉ ወጣ፡፡ ደስ ብሎትም አረፈ፡፡
ታላቁ ካንት፡- “…Placing of duty above beauty, morality above happiness is no worth. Act to treat humanity whether in your own person or in that of another, in every case as an end, never only as a means” በማለት የሰዎችን ህመም ለመረዳት በሰዎቹ ቦታ ሆኖ ስሜታቸውን ሳያውቁ የራስን ስሜትና ኃላፊነት ብቻ ጉዳይ ማድረግ ስህተት መሆኑን ያብራራል፡፡
ወዳጄ፡- በአብዛኛው የአፍሪካና የደቡብ አሜሪካ ህዝቦች ባህላዊ እምነት፤ ወዳጆቻቸው በአካል ቢለዩም መንፈሳቸው አብሯቸው እንደሚኖር በተደጋጋሚ ተጽፏል። በዚህም የተነሳ አንድ ሰው ከህልፈቱ በኋላ እንዲደረግለት የሚፈልገውን ነገር ማድረግ ሟቹን ማስደሰት ነው የሚል ዕሳቤ አላቸው፡፡ እኛ ኑዛዜ እንደምንለው፡፡
የኛን ሀገር ልምድን ጨምሮ አንዳንድ ኑዛዜዎች ምንም እንኳ የሟች ፍላጐት ቢሆኑም፤ ከባህል ከወግና ከልማድ ጋር ስለሚጣረሱ ተግባራዊነታቸው ለቋሚ ወዳጆችና ቤተሰቦች ጭንቅ ይሆናል። ለምሳሌ አንዳንድ ሊቃውንትና ከህብረተሰቡ ቀደም ያለ አስተሳሰብ ያላቸው ምሁራን በሚያልፉበት ጊዜ አካላቸው ለሰብአዊ ጥቅም አገልግሎት ወይም ለሳይንስ ምርምር ግብዓት እንዲሆን ወይም እንዲቀጥል ይናዘዛሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እገሌ በመቃብሬ እንዳይቆም በማለት ወይም መሰል ነገሮችን በመጠቆም ቤተሰቦቻቸውን አደራ ብለው ያልፋሉ፡፡ በእኛ ባህል ይህን ለማድረግ ያስቸግራል፡፡ ቢሆንም የሟችን ፍላጐት ማክበር ተገቢ ነው …Whose life is it anyway?
ታላቁ ፍሬዴሪክ ኢች ለእህቱ፡-
“እኔ ስሞት ከጓደኞቼ በስተቀር ማንም ከሳጥኔ አጠገብ እንዳይቆም፡፡ ፍታትና የውሸት ታሪክ አልፈልግም፡፡ በሰላም ወደ መቃብሬ መውረድ እሻለሁ፡፡ ይሄ ቃሌ እንዲፈፀም ቃል ግቢልኝ” ብሎ ነበር፡፡ እሷም ሃሳቡን ሞልታለች፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ታሪኮች ብዙ ናቸው፡፡ …ከሞትን በኋላ እንኳ የነፃነታችን ነገር አደጋ ላይ እንደሚሆን ያሳስበናል …whose life is it any way?
ወዳጄ፡- ከባለቤት በላይ ባለቤት፣ ከጳጳስ በላይ ቄስ መሆን አይቻልም፡፡ አበሻ “ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” ይላል፡፡ ደግነቱ ዘመኑ የቡዳ ሳይሆን የቡድሃ ይመስላል፡፡ ቡድሂዝም በእያንዳንዱ ሰው ፍላጐትና በነፃ የህይወት መንገድ መራመድን ያበረታታል፡፡
*   *   *
 ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- ነጋዴው ጐንበስ ቀና እያለ ሁለቱን የባለስልጣን ሚስቶች ሲያስተናግድ ፈሱ እንዳመለጠው ተጨዋውተን ነበር፡፡ ሴቶቹ ፈስተው የማያውቁ በመምሰል፡-
“ምነው አንተ እላያችን ላይ?” በማለት አፍንጫቸውን ሲይዙ የበሸቀው ነጋዴ…
“ባሎቻችሁ አፋችንን ዘጉት፤ እናንተ ደግሞ መፍሻችንን መዝጋት አማራችሁ!?” ነበር ያላቸው፡፡
መልካም የኢሬቻ በዓል!
ሠላም!

Read 1703 times