Print this page
Tuesday, 13 October 2020 15:02

ልሂድ ልቅር?

Written by  ሮቤል ሙላት
Rate this item
(1 Vote)

 "--የጭንቅ ጊዜ ማምለጫ ዘዴዎችን መቀየስ፤ ቀልጣፋና ግልጽ የሆነ የመረጃ ስርጭት እንዲኖር ማስቻልም፣ የሥራ ሀላፊዎቹ የቤት ስራ ሳይሆን የክፍል ስራ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ወደ ዩኒቨርሲቲ ስመለስ ተስፋና ስጋት ታቅፌ ነው፡፡--"
              ስነ-ሰብዓዊ ምልከታ
           (Anthropological Perspective) ሮቤል ሙላት

          “በቅርቡ ወደ ካምፓስ ይመለሳል፤ እዚያ የሀገሩ ልጆች ሊገድሉት ይፈልጋሉ”
(እሱባለው አበራ፤ 2012)
“በስተርጅና ያጠላለፍናቸው ሳሮች ራሱ ይናፍቁኛል” ስል የልጅነት ጓደኞቼ ሁሌ ይስቁብኛል፡፡  እከሊትን አደናቅፈን አዲስ የገዛቸውን የሚያበራ ጫማ አቆሸሽንባት፤ እንትናን ጥለን የሚያብረቀርቅ ቦርሳውን አስቀደድንብት፡፡ የተንኮል ቅቤ እዚያው ተነጥራ፣ በዛሬው ኑሯችን ላይ ጣል ተደርጋለች፡፡ ይህን ሸር ወለድ ጣዕም ለማስቀየር፣ እነ ጋሸ አሰፋ፤ እነ እትየ ጸሀይ ስንት የምክር ጎርፍ አርከፈከፉብን? ቢገደብ የራሳችንን ኩራዝ ለማብራት ይበቃስ አልነበር፡፡ ስንት የቁጣ ጠጠር ወረወሩብን? ቢከመር የጭቃ ቤታችንን አያስከነዳም ነበር፡፡ ስንት የልምጭ አሻራ ኣሳረፉብን? ጠባሳው ቢጠራቀም የነጋችንን ጸጸት አይጠርገውም ነበር፡፡ መስከረም ፈክቶ ወደ ት/ቤት የምንሄደው በአደይ አበባ የተቀለመ ደብተር ብቻ ይዘን አይደለም፤ ትናንሽ የክፋት እርሳሶችንም ቀርጸን እንጂ፡፡ ይሄው ዛሬ እዚህና እዚያ ቆመን፣ ተስፋን ለመቅበር እልህ እንዋዋሳለን፡፡
ቢሆንም ከት/ቤት በር መራቅ ትላንቴን፣ ዛሬንና ነገዬን የተቀማሁ ይመስል ይጨንቀኛል፡፡ ባለፈው ዓመት እንኳ “ተው ይቅርብህ" እየተባልኩ ሄጄ ስንቱን አየሁ? በተለይ ዩኒቨርስቲዎች እንደ ፈላ ቡና አንዴ በጠብ ሲገነፍሉ፤ ሌላ ጊዜ በግጭት ሲፈሱና በኋላም የስንቱን ጊዜ፣ ህልምና ጨጓራ ሲያቃጥሉ እንደ ከረሙ ተመልክተናል። Newman J. H. (1982). Idea of a University  በተሰኘ መጣጥፍ፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአለም እውቀት ማከማቻ ስፍራ ብሎ ቢጠራቸውም፤ Kritsiotis D.(2002). Imagining the International community, በሚለው ጥራዙ በምናብ እንደምንስለው፣ የአለምአቀፉ ማህበረሰብ ቀለመ ብዙ ናቸው ሲል ቢገልጻቸውም፤ Derrida J. (1984). Women in the Beehive:  በተባለው ጥናቷ፤ ተቋማቱ የሀገሬውን ማህበረሰብ ያንጸባርቃሉ እንጂ አጥር አበጅተው ራሳቸውን አያገሉም ብትልም፤ እንደ Yonas Ashine (Universities as Contested Terrain፤ 2019) ያሉ ምሁራን ግን በተለይም በአፍሪካ የዩኒቨርስቲዎች ውልደትና እድገት በሀሳብም በተግባርም፣ የምእራባውያን ሁለንተናዊ ጫና ያረፈባቸው ናቸው ይላሉ።  በርግጥ ይህን ሀሳብ ይርጋ ገላውም  Native Colonialism: Education and the Economy of Violence Against Traditions in Ethiopia (2017) በሚለው ጥናቱ ይጋራዋል፡፡ እንደ እርሱ አገላለጽ፤ የቅኝ ግዛት መንፈስ የተጫነው ምዕራብ ቀመስ  የትምህርት ስርዓት፣ ሀገር በቀል የሆነውን የአፍሪካ እውቀት "ኋላ ቀር" ብሎ ገፍቶታል፡፡
ቢሆንም ከክፍል መቅረት ሰማይ የወደቀብኝ ያክል ይከብደኛል፡፡ እዛ ዴስኩ ላይ ሳልጽፈው የቀረሁት ፊደል ያለ ይመስል፤ ጥቁር ሰሌዳው ላይ ያላየሁት የቲቸር ኖት ያለ ይመስል፤ ከቤተ መጽሐፍቱ ተውሼ ያልመለስኩት መጽሐፍ ያለ ይመስል ቅር ቅር ይለኛል፡፡
2012 ዓ.ም ለሀገሬ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምጥ ጊዜ ነበር፡፡ ፖለቲካው ከሚጥለው የጥላቻ እንቁላል የሚፈለፈሉ ግጭቶች በዝተዋል፡፡ “ትዝታሽን ለእኔ፤ ትዝታየ ለአንቺ” የሚል ርዕስ በሰጠው  መጽሐፉ፣ እሱባለው አበራ (2012) ጭምር፤ “ሰዎች እንዴት ሀገራቸውን ሊያጠፉ ዩኒቨርስቲ  ይገባሉ?” ሲል ይጠይቃል። ተሜ ከፊደል ሰራዊትነት ወደ ዱላ ሰራዊትነት እንዴት ተቀየረ? የቀለም ቀንድ መናኸርያ የሆኑት ግቢዎች፤ መቼ የጦር ቀንድ መናኸርያ ሆኑ? የ’የተማረ ይግደለኝን’ ትንቢት ለመፈጸም ለምን ተጣደፍን? ከምር ግን “እማ ተማሬ አሳልፍልሻለሁ” የምትባለው አንጀት መብያ ዜማ ከምኔው cover music ሆና አረፈችው? እንዴት እዚህ ደረስን? በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አበው፣ ዘንድሮ ደግሞ ኮቪድ- 19 የሚሉት ወረርሽኝ ተከስቶ፣ እጅ እግር የሌለውን ትምህርት ይብስ ቅጥ አምባሩን አሳጥቶታል፡፡  ተቋማቱስ በኮሮና መሃል ምን ጠባይ ይኖራቸው ይሆን?
"ተማር ልጄ!"
ከ1928 ዓ.ም የጣልያን ወረራ በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፣ በትምህርት ፊያት ተሳፍረው ወደ ዘመናዊነት ፌርማታ ለመድረስ ያልፈነቀሉት ድንጋይ  አልነበረም፡፡ የእንደራሴ ምክር ቤቱን አሻሻሉ፣ መንገዶችን ገነቡ፤ የግብር ስርዓቱን አሰለጠኑ፣ ጋዜጣ ማሳተም ጀመሩ፤ ትምህርት ቤቶችን አስፋፉ እንዲሁም ሰፋፊ የእርሻ ተቋማትን አደራጁ (Kassim Shehim, 1985)፡፡  ዶናልድ ሌቪን እንደሚለው፤ በ1935 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዘመናዊ ት/ቤቶች ውስጥ ከ6 እስከ 7 መቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ከአስር ዓመት በኋላ በ1944 ዓ.ም በመላ ኢትዮጵያ ከ25 ሺ በላይ ተማሪዎች በመንግስት ት/ቤት ገብተው መማር ችለዋል፡፡  ይህ ቁጥር በ1950 ዓ.ም ወደ 60 ሺ፤ በ1963 ዓ.ም ደግሞ ወደ 234 ሺ ከፍ ብሏል፡፡
ይባስ ብሎ ቤታቻውን ሳይቀር አሳልፈው የሰጡት ንጉሱም፤ አዳዲሶቹ ተማሪዎች ላይ ተስፋም፣ እምነትም አሳደሩ። የአገር ቤቱ አስኮላ አልበቃ ብሏቸው ውቅያኖስ አሻግረው አስተማሩ፡፡ በሀገሪቱ የመጀመርያው ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ሲቋቋም፣ በአሮጌው ሕንፃ ግድግዳ ላይ እንዲህ የሚል ቃል አሰፈሩ፤ “ኩሎ አመክሩ ወሠናየ ግበሩ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ”፡፡ ወጣቶቹ ግን መልካሙን ለመያዝ ወጥተው ከመንገድ ቀሩ፡፡ ቀበጺ ተስፋ የተሞላ የወኔ ባትሪ አንጠልጥለው ዳገቱ ላይ እንደዋተቱ ኖሩ፡፡ ወዲያው ከአባቶቹ ጋር የተጣለ አዲስ ወፍ ዘራሽ ማንነት በቀለ።  እንደ ጉድ ተስፋ የተጣለበት ዘመናዊ ትምህርት፤ ገና በጧቱ ማነከስ ጀመረ፤ ማስነጠስ ቀጠለ፡፡  መሳይ ከበደ (2008). Radicalism and Cultural Dislocation in Ethiopia, 1960-1974 በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደሚሉት፤ ምዕራባዊ ትምህርት የሚቋምጡለትን አዎንታዊ ‹ዕድገትና ቀጣይነት› በቀረው ዓለም እንግዳ ከባቢ ውስጥ አያከናውንም። እንዲያውም በተቀባዩ ባሕል ላይ በሚያስከትለው ሁለገብ ወረራ፣ ውርደትና ብረዛ የቀጣይነትን ጉዳይ ወደ ዐብይ ችግርነት ይቀይረዋል። ለአዘማኝነት የታጨው ትውልድ፤ ከአገርኛ ውርሶችና ቅርሶች ጋር የሚኖረውን ቁርኝት በማላላት፣ የባሕልና አስተሳሰብ ጥገኛ፣ የጋራ ራዕይና ሠላም የሌለው፣ አጉል ተመጻዳቂ፣ ቀላዋጭና መጢቃ ያደርገዋል (ትርጉም፤ ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም)። በተኮረጀ ተምኔት ላይ የተወለደው የነጻነት ችቦም ሳይንቦገቦግ ከሰመ፡፡
በርግጥ ኢኮኖሚ የተጫነው የዘመናዊነት ንድፈ ሀሳብ፣ የባህል ለውጥ እንደሚያመጣ እሙን ነው፡፡ ከዘልማዳዊው እሴት ጋር የሚያስታርቀው የማርያም መንገድ ካላገኘም ትርፉ የባህል ቀውስ (cultural shock) ነው፡፡ ከፍትኛ የትምህርት ተቋማት፣ ይሄን ጉራማይሌ ስሪት የማቃናትና የማዋሃድ አቅሙ አላቸው፡፡ እዚህ ብዝሀ አመለካከት፣ ብዝሀ ቋንቋ፣ ብዝሀ ሀይማኖት ተሰናስለው ይገኛሉ፡፡ በርግጥ የግል የሆኑ እሴቶች እንዳሉ ሁሉ የጋራ የሆኑም ብዙ ትውፊቶች አሉ፡፡ በጊዜ ሂደት፣ በመቀራረብ ውስጥ፣ በመተዋወቅ ዓለም እንዲሁም በመዋደድ ሰዓት፣ የራስን መስጠትና የሌሎችን መቀበል ይኖራል፡፡ በዚህ የመዋሀድ ኬሚስትሪ ውስጥ የስነ-ሰብዕ (Anthropology) ምሁራን “Cosmopolitan” ወይም በጋሽ አሰፋ ጫቦ ተለምዷዊ ትርጓሜ “የሰው ሰው” ይፈጠራል፡፡ Cosmopolitan is about the love of mankind, or about duties owed to every person in the worled, without national or ethnic differentation. For others, the word... connotes the fluidity and evanescence of culture; it celebrates the compromising or evaporation of the boundaries between cultures. (Ben Habib, 2006).
የሰው ሰው የሁሉም ነው፣ ከሁሉም ነው፣ እንደ ሁሉም ነው፡፡ የመጨረሻ ግቡም ሰብአዊነትን ከፍ ከፍ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትምህርት ወሳኝ መሳሪያ ነው፡፡ The proper study of mankind is man እንዲል አሌክሳንደር ፖፕ፡፡ ትምህርት መጀመርያ ሰብአዊ ነው፤ ቀጥሎ መክሊታዊ ይሆናል፤ ከዚያም አዲስ ነገር ወደ ማቡካትና መጋገር ይሸጋገራል፡፡ ዶ/ር እጓለ ገ/ይኃንስ፤ ‘የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ’ በተሰኘ ጥልቅ መጽሐፋቸው፤ ሶስት የትምህርት ዓላማዎች/ጠባዮች እንዳሉ ይገልጸሉ፡፡ እነርሱም Humanistic, professional and scientific “ሰው የሚማረው ከዝቅተኛው እንስሶች ጋር የጋራ ከሆነው ስ-ነፍጥረታዊ ሁኔታ ወጥቶ በሃቡና በምኞቱ መሰረት፣ ከከፍተኛነት የሙሉ ሰውነት ማዕረግ ደረጃ ለመድረስ ነው” ይላሉ ዶ/ሩ ፡፡ በመማር ውስጥ ራስን ማወቅ አለ፤ ሌሎችን መረዳት ይቀጥላል፡፡ በማወቅ ጥረት ውስጥ ትላንትን ማስታወስ አለ፣ ዛሬን መተንተን አለ፤ ነገን መገምት ደግም ይመጣል፡፡ የሰው የሆነ ሰው ፍቅሩ ድንበር የለውም፤ አክብሮቱ አጥር የለውም፤ ችሮታው ወሰን የለውም፡፡ የሰው የሆነ ሰው እጁ ረጅም ነውና ሁሉን ይቀበላል፣ ሁሉን ያቅፋል፣ ሁሉን ያስተናግዳል፣ ለሁሉም ያካፍላል፡፡ የሰው ሆነ ሰው በምናቡ ተጓዥ ነው፣ በሀሳቡ በራሪ ነው፣ በምክኒያት አማኝ ነው፣ ለርዕዮቱ ታማኝ ነው፡፡ ሀቢብ (2006) ሲቀጥል፤ Cosmopolitan in this sense invites us, without rejecting connections rooted in cultural identity and practice or grasping at universalism, to find connection through. within, and beyond cultural diversity.
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ ይህን የሰው ጽንስ በጤና የማዋለድ፣ በሰላምና በፍቅር የማሳደግ ሀላፊነት አለባቸው። አዳዲስ ሀሳቦች የሚቸረቸሩባቸው፤ የሚፈተሹባቸውና እንደ ወርቅ ቀልጠው የሚወጡባቸውም ቤተ-እውቀት መሆን አለባቸው፡፡ ሀሳብ ከግራና ከቀኝ የሚቀበሉ፣ አደባባይ አውጥተው የሚያሰጡ፣ የሚያሹና የሚያስፈጩ ሲሆኑ፤ የሀሜትና የሽክሹክታ ቀዳዳ ይደፈናል፡፡ ባይዘጋ እንኳ ይጠባል። አለበለዚያ የአነብናቢነት፣ የሸምዳጅነትና የኮራጅነት ባህሪ ግቢዎቹን እንደ እንቦጭ አረም ይወራቸዋል፡፡
ስለ ራስ አለመናገር፣ በራስ በሆነ ጉዳይ ላይ አለማተኮር፤ በሌሎች እጅ ባለ ነገር ላይ መጠመድ ትርፉ ድካም ነው፡፡ በርግጥ ድካም ብቻ አይደለም፤ በአብዛኛው ከራስም ጋር ያጣላል፡፡ የማንነት ግጭት የሚባለው ይኸው ነው፤ ቀጥሎ ከማህበረሰቡ ያቃርናል። ይህ ማለት ግን ስለ ሌላው አለም መስማትም፣ ማየትም ሆነ ማወቅ ነውር ነው ማለት አይደለም፡፡ የሰው ሰው ባህሪ ይኮ ይቀበላል ደግሞም ይሰጣል ብለናል፡፡ ነገር ግን ግብ አለው? ያ መንገድ ህልሙን የሚያሳካ ነው? ወይስ ለታይታ (pretend)? የሚለው በትኩረት ሊታይ ይገባዋል፡፡
እውቀት ፈራን?!
ትምህርት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የተስፋም የዕጣ-ፈንታም ጉዳይ ነው፡፡ የአንድ ወጣት መጪ ጊዜም የፈተና ወረቀቱ ላይ በሰፈረችው ውጤት የተመሰረተ ነው። እናም ትምህርት አንድ ለእናቱ የሆነ የድህነት ማምለጫ በር ነው፡፡
"የተማረና የበላ ወድቆ አይወድቅም” የምትል የድሮ አባባል በዘመኑ ቀላል አልነበረችም፡፡ ነገር ግን የ ‘ያ ትውልድ’ ጥላ ያጠላበትና አረፋው ያረጠበው ይሄኛው ትውልድም፣ ጦሱ ደርሶት እንደባከነ አለ፡፡ ፕሮፌሰር መሳይ በጥናታዊ ወረቀታቸው፤ በተለይ የ1960ዎቹን የተማረ ክፍልና የትምህርት ስነ-ስርዓት አምርረው ይተቹታል፡፡ ደግሞም ትክክል ናቸው፡፡ “የትምህርት ሥርዓቱ ሌላው ጎጂ ውጤት ልሂቃዊነት በተፈጥሮው የሌላ ተመልካች፤ የሩቅ ናፋቂ ነው። ሀገር በቀል እውቀቱን በሙሉ በማጣጣል፣ ያለፈውን ሁሉ በማንቋሸሽ የኢትዮጵያ ምሁር፣ ትውልዳዊ ክፍተት ፈጠረ። "የማይጨበጥ የማይደረስበት አዲስ የተምኔት ዓለም ፈጣሪ ነኝ; ብሎ ራሱን አጨ። ዕውቀት ከኛ በላይ ለአሳር ከሚል የተመጻዳቂነት ስሜት ጋር ሲደባለቅ፣ ሥር ነቀላዊ አስኮላውያንን ፈጠረ።
ዘንድሮም ከታች አምናው የሰንሰለት እስር መላቀቅ አልቻለም፡፡ የትዝታ ዜማ እንደ አሸን ፈልቷል፡፡  በትላንት ኩኩሉ ነቅተን፤ በአምና ውኃ ፊታችንን ታጥበን፤ ያለፈ ጠራራ ትርክት እየገፋን፤ ሲመሽ በትውስታ አንሶላ ተጠቅልልን እንተኛለን። የትውልድ መሳዎቼ፣ ሰምና ወርቅ ይህን መስሏል፡፡  “እዚህ ጋ ደግሞ ሌላ ትኩሳት” እንዲል ቴዲ አፍሮ፤ የኮረና ወረርሽኝ ደግሞ ሌላ ስነ ልቦናዊ ቀውስ ይዞ መጥቷል፡፡ የጋራ እንቅስቃሴዎች በሚበዙባቸው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ትምህርትን በቀላሉ ማስቀጠል ከባድ ነው፡፡
ከክፍል እስከ ካፌ፤ ከቤተ መጻህፍት እስከ መዝናኛ ሥፍራዎች፤ ከማምለኪያ ቦታ እስከ አስተዳዳር ህንጻዎች ድረስ ሰዎች በብዛት የሚታዩባቸው ናቸው። በአዘቦቱ እንኳ ውኃ  የሚናፍቃቸው ግቢዎች፤ የሚያጨናንቁ ክላሶች በየካምፓሶቹ ነፍ ናቸው፡፡ ዘመቻ የሚወድ አመራር፤ በአጭር ጊዜ እቅድ ተዋካቢ የትምህርት አስተዳደር እዛም እዚህም ሞልቷል፡፡
መንግስት ለተመራቂ ተማሪዎች ቅድሚያ ሰጥቼ፣ ቀሪዎቹን በሌላ ዙር ትምህርታቸውን አስቀጥላለሁ ብሏል፡፡ ይህ እቅድ ግቢዎቹ በተማሪ ከመጨናነቅ እንደሚተርፋቸው አስባለሁ፡፡ ይሁን እንጂ የአብሮነት ባህል በለመዱና አገልግሎት መስጫ ተቋማቱ ለጋራ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቦ በተሰሩ እንደ ካፌና መኝታ ቤት ባሉ ክፍሎች ተማሪዎች አሁንም መሰባሰባቸው አይቀርም፡፡ ዶርም ብቻዬን ብሆን ምን ይውጠኛል? ካፌ እየተጋፋሁ ካልተሰለፍኩ ምኑን ሰቀልኩት? ክላስ ተራርቄ ስማር ታየኝ? ብዙ ጥያቄዎች ተከታትለው ይመጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ የአዕምሮ መረበሽን ያስከትላል፡፡ አለመረጋጋትና መብሰክሰክ ይቀጥላሉ፡፡ ትምህርት በባህሪው እርጋታን፤ ማሰላሰልንና መመርመርን ይጠይቃል። ከተማውን እዩትና ፍረዱ፡፡ ህይወት ከነ ግሳንግሷ ቀጥላ የለምን፡፡ ዩኒቨርስቲ የዚያ ነጸብራቅ ያርፍበታል፡፡
ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ፣ የመረጃው ወረርሽኝ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የመረጃ ፍሰቱ ከላይ ወደ ታች ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው የጎንዮሽ ስርጭትን የተከተለ ነው፡፡ ይህም የመረጃውን መልክና ጠባይ ጉራማይሌ ያደርገዋል፡፡  ምንጩ የማይታወቅ፤ አካሄዱ የማይገመት፣ መድረሻው የማይወሰን ወሬ ካምፓሱን ሊሞላው ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ጭራ የለሽ ቀዳዳዎች ደግሞ ለረብሻ መወለድ ምክኒያት ሲሆኑ ታዝበናል፡፡ በተጨማሪም በተማሪዎች በመምህራንና በአስተዳዳር ሰራተኞች መካከል ያለው ግንኙነት፤ በቅርጽና በድግግሞሹ ላይ ለውጥ ያስከትላል፡፡ ስለዚህ ትምህርት ሲጀመር ተማሪን ያማከለ እቅዶች እንደሚተገበሩ እጠብቃለሁ፡፡
በጊዜና በሁኔታዎች መካከል ራሱን የሚያሻሽል የመፍትሄ ሀሳቦች ተግባራዊ ይደረጋሉ ብዬም አስባለሁ፡፡  የጭንቅ ጊዜ ማምለጫ ዘዴዎችን መቀየስ፤ ቀልጣፋና ግልጽ የሆነ የመረጃ ስርጭት እንዲኖር ማስቻልም፣ የስራ ሀላፊዎቹ የቤት ስራ ሳይሆን የክፍል ስራ ይመስሉኛል፡፡ ስለሆነም ወደ ዩኒቨርስቲ ስመለስ ተስፋና ስጋት ታቅፌ ነው፡፡
ተስፋዬ እንዲህ ነው፡፡ አጠገቤ ላሉት ሰዎች የምር የምሳሳ ይመስለኛል፡፡ ያለ ዶርሜ ልጅ፤ ያለ ግቢ ተማሪ የእኔ ሙሉነት የት ላይ ነው? ቲከሮቹ አልናፈቁኝም፤ የመምህሮቼ መመለሻ ሰዓት እርቆብኝ በስስት አልተብሰከሰኩም?  የካምፓስ ዘበኞች ቁጣ እንደ ሱስ አላቅበዘበዘኝም? የካፌ እናቶችስ አስር አስር ጊዜ፣ በአይኔ ውል አላሉም? አልዋሽም ብለዋል፡፡
“ቀራንበት ኀቤሁ እንዘ ቅረሩባን
ቀራንበተ ኢይኔጸር ዓይን” የሚል የግዕዝ ቃል አለ፡፡ ትርጉሙም፤ ‘ለአይን እጅግ የሚቀርበው ቅንድቡ ነው፤ ግን እሱን እንኳ አያየውም’፡፡ እኛ እንዲህ ነን! ስለ ሩቁ እንማራለን፤ ስለዛኛው እንጠይቃለን፤ ስለ ወዲያኛው እንፈትሻለን፤ መንገዳችንም ወደዚያው ነው፡፡ ሆኖም ውስጣችንን እንረሳለን፤ በዙሪያችን ያሉትን ደጋግ ሰዎች እንዘነጋለን፤ ለኛ ሲሉ ሌላ ጸጉር ያበቀሉትን ላሽ እንላለን፤ ለኛ ሲሉ ሌላ መልክ ያወጡትን እንርቃለን..፡፡
“አለ በውስጣችን
እውነት ፍጹም ሆና የምታበራበት
ደግሞም ማወቅ ማለት
ከውጭ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ ያበራውን እንዲወጣ ማድረግ”
--ሲል ገ/ክርስቶስ ደስታ፣ የሮበርት ብራውንን ግጥም የተረጎመው ወዶ አይደለም፡፡
ከኮሮና በኋላ እንዲያ የሚሆን ይመስለኛል፤ ወደ ቀልባችን የምንመለስበት። እኔም ወደ ዩኒቨርስቲዬ እሄዳለሁ፡፡
“ትምህርት ቤቴ እናቴ
የዕውቀት ገበታ ፍትፍቴ”
(የህጻናት መዝሙር)


Read 882 times