Monday, 12 October 2020 09:10

ኦነግ ከድርጅቱ የታገዱት ሊቀመንበር ያስተላለፉት ጥሪ አይመለከተኝም አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 ድርጅቱ የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚል አጀንዳ የለውም


           ከስልጣናቸው መታገዳቸው የተገለፀው የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሣ በኦሮሚያ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በእነ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ኦነግ በበኩሉ ከድርጅቱ የታገዱት አቶ ዳውድ ኢብሳ ያቀረቡት ጥሪ እንደማይመለከተውና የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚል አጀንዳ እንደሌለው ገልጿል።
ከድርጅቱ መታገዳቸው የተገለፀው አቶ ዳውድ ኢብሣ 18 ደቂቃ በሚወስደው  የቪዲዮ መግለጫቸው በኦሮሚያ የሽግግር መንግስት መቋቋሙን ያወጁ ሲሆን አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ስልጣኑ አብቅቷል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ የሽግግር መንግስት ስለመቋቋሙም የአፍሪካ ህብረትና አለማቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቅ ይሁን ብለዋል አቶ ዳውድ በመግለጫቸው፡፡
የሽግግር መንግስቱ ሲቋቋምም ኦሮሚያን የመገንባት እንጂ ኢትዮጵያን የማፍረስ አላማ እንደሌለውና ኢትዮጵያውያን ለሽግግር መንግስቱ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኦነግ አስቀድሞ እንዲህ ያለ አላማ እንደነበረው ከአዲስ አድማስ ጥያቄ የቀረበላቸው የግንባሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቀጄላ መርዳሳ ኦነግ ስለሽግግር መንግስት መቋቋም አስቦ አያውቅም ለቀጣዩ ብሔራዊ ምርጫ ነው እየተዘጋጀ ያለው ብለዋል፡፡
የታገዱት ሊቀመንበር መግለጫም ኦነግን እንደማይመለከትና ሊቀመንበሩ ከስልጣን ከታገዱ በኋላ ከሕወኃት ጋር በመቀናጀት የፈጠሩት አላማ መሆኑን ከዚያ በፊት ራሳቸው አቶ ዳውድ በመሩት የኦነግ ስብሰባ ስለሽግግር መንግስት ተነስቶ እንደማያውቅ በመግለጽ አስረድተዋል አቶ ቀጀላ፡፡
ቀደም ብሎ ሊቀመንበሩ በመሩት የኦነግ ስብሰባ የተወሰነው ግንባሩ ለቀጣዩ ምርጫ እንዲዘጋጅ እንጂ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ብሎ እንዲጠይቅ አለመሆኑንም አቶ ቀጄላ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡


Read 10880 times