Tuesday, 13 October 2020 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

   “Where there is no thought, there is chaos” ሞንቴሶሪ
             


            በድሮ ቀልድ እንዝናና፡- ሰውየው መጠጥ አድጐበት ስካርን ኖሯል፡፡ ባለቤቱ ከጓደኞቿ ጋር ስለ ትዳር ሰትጨዋወት በባሏ ድርጊት እየተሸማቀቀች አለቀች፡፡ ችግሯ ካሳሰበው የባለቤቷ ወንድም ጋር ተማክረው ዘዴ ፈየዱ፡፡ አንድ ቀን እንደ ልማዱ ድብን ብሎ ሲመጣ፣ ባዘጋጁት የሬሳ ሳጥን ውስጥ አስገብተው ዘጉበት፡፡ ስካሩ በርዶ የት እንዳለ ሲያውቅ፣ በእፍረት መጠጣት ያቆማል በማለት ነበር፡፡ …ትንሽ ቆይቶ ሳጥኑ መንጓጓት ጀመረ፡-
“አቤት!” አሉ፤ ድምፃቸውን ቀይረው፡፡
“የት ነው ያለሁት?”
“ሙታን ከተማ”
“እ?”
“ሬሳ መሆንህን አላወቅህም?”…ሬሳው ሲያስብ ቆይቶ፣ እንደገና ሳጥኑን ደበደበ፡፡
“ምን ፈለክ?” ሲሉት ምን እንዳላቸው ታውቃለህ? መጨረሻ ላይ መልሱን እነግርሃለሁ፡፡
*   *   *
ወዳጄ፡- ህፃንነት፣ ወጣትነት፣ ጉልምስናና ሽምግልና የአንድ ግንድ አራት አንጓዎች ናቸው፡፡ ልጅነት ውስጥ የወጣትነት ጽንስ፣ ወጣትነት ውስጥ የልጅነት ቅሪት አለ፡፡ በጉርምስናም የጐልማሳነት፣ በጐልማሳነትም የጉርምስና እርሾ ይኖራል። በሽምግልናም ውስጥ የጐልማሳነት ቅሪት ሲኖር፣ የሽምግልና ፍሬ የሚያድገው በጐልማሳነት ውስጥ ነው፡፡ ሽምግልና የሁሉም አንጓዎች አናት ቢሆንም የስረኞቹ ላይደርሱበት ይችላሉ፡፡ ልጅነት ከሌለ ግን ሁሉም አንጓዎች አይኖሩም፡፡ የሁሉም የህይወት አንጓዎች አቅም ልጅነት ነው፡፡
በለጋነቱ የተጣመመ ወጣትነቱ ውስጥ ጠማማነት አለ፡፡ እስከ ሽምግልናውም ሊዘልቅ ይችላል፡፡ በለጋነቱ የተስተካከለ ግን ልከኛ ሆኖ ያድጋል፡፡ ህፃንነት ውስጥ የተለኮሰች ሻማ የምትጨልመው በመጨረሻው የዕድሜ ትንፋሽ ነው፡፡ ዕድሜ ለሰጠው፡፡ በተወለድንበት ሰሞን እናቶቻችን ዓይናችን እንዳይንሸዋረር፣ አናታችን እንዳይሟለል፣ እግራችን እንዳይወላገድና አጥንታችን እንዲጠነክር ይንከባከቡናል፡፡
“እንክብካቤ የህፃናት የልምድ መጀመሪያ ሲሆን ሁለተኛው በነፃነት የተማከለ ትምህርት ነው፡፡ ትምህርት የህይወት ምሰሶ ነው፡፡” ትለናለች፤ታላቋ መምህርትና ፈላስፋ ማሪያ ሞንቴሶሪ!!
ዶክተር ሞንቴሶሪን ማስታወስ የፈለግነው በቀደም ማክሰኞ ኦክቶበር 6 ቀን 2020 ዓ.ም የተከበረውን ዓለም አቀፍ የመምህራን ቀን ያለሷ ለመዘከር ስለማይታሰብ ነው። ማሪያ ሞንቴሶሪ የተወለደችው እ.ኤ.አ በ1870 ዓ.ም አንኮና በተባለች የጣሊያን ግዛት ውስጥ ነበር፡፡ በዛን ዘመን ለሴቶች የሚፈቀደው ክፍት የስራ መስክ መምህርነት ብቻ ስለሆነ የሞንቴሶሪ ወላጆች ልጃቸው መምህርት እንድትሆን ያበረታቷት እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ማሪያ ሞንቴሶሪ ግን ለሴቶች በተከለከሉ ተቋማት ገብታ የምትፈልገውን ለማግኘት የቻለች ብቻ ሳትሆን ለቢጤዎቿ እኩልነት አጥብቃ የታገለች የመብት ተሟጋችም ነበረች፡፡ እንደ ምሳሌም በዘመኑ ለሴቶች ከማይፈቀደው የሮም የህክምና ዩኒቨርሲቲ ገብታ በመማር እ.ኤ.አ በ1896 ዓ.ም የመጀመሪያዋ ሴት ተመራቂ ሆናለች፡፡ በዩኒቨርሲቲው ጥያቄም የት/ቤቱ ሳይካትሪክ ክሊኒክ ስታፍ በመሆን ያገለገለች ሲሆን በቆይታዋ የአእምሮ ሳንካ ስላለባቸው ህፃናት በማጥናት፣ በልዩ የትምህርት አሰጣጥና ሰርቶ ማሳያ ዘዴ የህፃናቱን ችግር ማቃለል እንደሚቻል ፅፋለች፡፡
ማሪያ ሞንቴሶሪ ወደ ለንደንና ፓሪስ በመጓዝም ቀደም ብለው በህፃናት ሳይካትሪክ ዘርፍ ጥናት ያደረጉትን የጂን ኢታርድና ኤድዋርድ ሴግዊን ምርምሮችና ልምዶችን በመቅሰም ወደ አገሯ ተመልሳ የኦርቶፍሬኒክ ት/ቤት ዳይሬክተር በመሆን በሙያው ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች፡፡ የጥናት ወረቀቶቿም በየጊዜው በሚወጣው ቴክኒካል ጆርናል ላይ ሲታተሙ እንደነበር በህይወት ታሪኳ ይጠቀሳል፡፡
ዶ/ር ሞንቴሶሪ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሮም ዩኒቨርሲቲ ተመልሳ ፍልስፍናና አንትሮፖሎጂ በማጥናት እ.ኤአ ከ1904-1907 ድረስ የአንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር በመሆን ያገለገለች ሲሆን በመላው ዓለም ዝና ያተረፈላትን “The Montessory Method” የተሰኘውን የመጀመሪያ መጽሐፏንም የፃፈችው በዚያን ወቅት ነው፡፡
ማሪያ ሞንቴሶሪ በ1912 እ.ኤ.አ ተጋባዥ ሌክቸረር በመሆን ወደ አሜሪካ ያቀናች ሲሆን በኋይት ሃውስም የክብር አቀባበል ተደርጐላታል፡፡ አጅግ ብዙ ታዳሚ በተገኘበት የዴል ካርኒጌ አዳራሽም ፍልስፍናዋን በማብራራት ከፍተኛ አድናቆት ተችራለች፡፡ ሞንቴሶሪ በአሜሪካ ቆይታም የሰነበተችው አክባሪዋ ከነበረው ቶማስ ኤዲሰን መኖሪያ ቤት ነበር፡፡ በዛን ሰሞን የአሜሪካን ሞንቴሶሪ ማህበር የተመሰረተ ሲሆን የአሌክዛንደር ግራሃም ቤል ባለቤት ወ/ሮ ግራሃም ቤል የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ ሲመረጡ፣ የፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰን ልጅ ወ/ት ማርጋሬት ዊልሰን ደግሞ በፀሐፊነት ተመድበዋል፡፡
ሞንቴሶሪያን ት/ቤቶች ምንም እንኳ በአሜሪካ ግዛቶች እየተስፋፉ ቢመጡም፣ የሴትየዋ የትምህርት ፍልስፍና ግን ነቀፌታ አላጣውም፡፡ የትምህርት አባት በመባል የሚታወቀው አሜሪካዊ ፈላስፋ ጆን ዴዊን አስተሳሰብ የሚከተለውና በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ኮሌጅ የተከበረ ፕሮፌሰር የነበረው ዊሊያም ኪልፓትሪክ፤ እ.ኤ.አ በ1904 ዓ.ም ባሳተመው “The Montessory system examind” በተባለው መጽሐፉ፡- #የዶ/ር ሞንቴሶሪ የትምህርት ፍልስፍና ለስልጣኔ አስተዋጽኦ እንዳለው ባይካድም በእኛ አገር ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት ያላደረገ፣ በህፃናት ተፈጥሮ ላይ በቂ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ አዳዲስ ዕውነታዊ ግኝቶችን ያላከተተ፣ ግማሽ ክ/ዘመን ወደ ኋላ የሚመልስ አቀራረብ ነው” በማለት ተችቶታል፡፡
ሞንቴሶሪ ወደ አሜሪካ በመጣችበት ወቅት ከዶ/ር ኪልፓትሪክ ጋር ያደረገችው ውይይትም፤ በአስተርጓሚያቸው የስነ ልቦና ሳይንስ ዕውቀት ችግር ምክንያት እንደታሰበው አልሆነም፡፡ በሞንቴሶሪዝም ላይ የተሰነዘሩት ነቀፌታዎችም ሆኑ በፋሽስት ኢጣሊያና በጀርመን ናዚዎች የተደረጉበት ተጽእኖዎች፣ ሞንቴሶሪያን ት/ቤቶችን በጊዜያዊነት ከማወክ በስተቀር በተሻለ የሃሳብ ለውጥ ሊተኩት ወይም ወደፊት ከመራመድ ሊገቱት አልቻሉም። ሞንቴሶሪዝም ማዕከሉን አምስተርዳም ባደረገው አለምአቀፍ ቢሮው እየታገዘ ት/ቤቶቹን በመላው ዓለም በተለይ በአሜሪካ አውሮፓና ህንድ ማዳረስ የቻለ፣ ለስልጣን ግብዓት በመሆን የአስተሳሰብ ለውጥ ያመጣ ተቋም ነው፡፡ ታላቋ መምህርት ዶ/ር ማሪያ ሞንቴሶሪ እ.ኤ.አ ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ መኖሪያዋን ቋሚ ባደረገችበት ኔዘርላንድስ፤ በተወለደች በሰማንያ ሁለት ዓመቷ ከዚህ ዓለም ተለይታለች፡፡
ወዳጄ፡- አለም አቀፉን የመምህራን ቀን ስናከብር፤ የኛንም የፊደልና የተረት አባቶች፣ የመማሪያ መፃሕፍት አዘጋጆች፣ አስገራሚ ታሪኮችን በመፃፍ የንባብ ፍቅር ያሳደሩብንን ደራሲዎች፣ ስለ ትምህርት ጥቅም ያንጐራጐሩልንን ዘፋኞች፣ በቴአትር መድረክ አዝናንተው ያስተማሩንን አርቲስቶች በአጠቃላይ የልጅነት አንጓችንን ያበረቱልንን ሁሉ በማሰብና በማመስገን ነው፡፡
“Where there is no thought, there is chaos” ትለናለች ሞንቴሶሪ!
*   *   *
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- ሬሳው ለሁለተኛ ጊዜ ሳጥኑንስ እንዳንኳኳ ነግሬያችሁ ነበር፡፡
“ምን ፈለግህ?” ብለው ሲጠይቁት…
“መጠጥ ቤቱ የት ጋ ነው?” በማለት ነበር ተስፋ ያስቆረጠችው፡፡
ሠላም!  

Read 506 times