Sunday, 11 October 2020 00:00

ለብሔራዊ መግባባት ውይይቱ ውጤታማነት

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(2 votes)

  "-የዚህ ሂደት የመጀመሪያው ግብ፣ በፖለቲካ ልሂቃኑ መሃከል ለዘመናት ተኮትኩቶ የተገነባውን አእምሮአዊ አጥር (Mental barriers) ማፈራረስ ነበር። ይህንን ግብ፣ በግለሰብ፣ በቡድንና በስብስብ ደረጃ በተካሄዱ በርካታ ውይይቶችና የተግባር ልምምዶች አማካኝነት በአብዛኛው ለማሳካት እንደቻለ መመስከር ይቻላል።--"
          
           ላለፉት በርካታ ዓመታት በሃገራችን ያለውን የፖለቲካ መመሰቃቀል ለመረዳትና መፍትሄ ለመሻት የብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ሲነሳና ሲጠየቅ መቆየቱ ይታወቃል። ይህንንም እውን ለማድረግ በተለያዩ ዜጎችና የበጎ ፍቃድ ቡድኖች፣ ልዩ ልዩ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ነገር ግን፣ ከእነኚህ ጥረቶች አብዛኞቹ ወይ በጅምር ከሽፈዋል አሊያም በውሱን ውጤታማነት ተጠናቀዋል። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ የሚችሉ ቢሆንም፣ የሂደቶቹ አካታች አለመሆንና በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ለሂደቶቹ የነበረው ፈቃደኝነት ውሱን መሆን በዋነኝነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በቅርቡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አማካኝነት፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ለማካሄድ የተደረሰው ስምምነትና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሃል እየተካሄደ የሚገኘው ውይይት፤ ከላይ የተጠቀሱትን መሰረታዊ ችግሮች በማስወገድ ረገድ የተሻለ እድል ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል። በመሆኑም፣ ሁሉም የዚህች ሃገር የወደፊት እጣ ፈንታ የሚያስጨንቀው ወገን ሊያበረታታውና ህዝባዊና ሙያዊ ድጋፍ ሊቸረው ይገባል። ይህንን ለሃገሪቱ መጻኢ ዕድል ወሳኝ የሆነ ሂደት የሚመሩና የሚያስተባብሩ ወገኖችም ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን፣ ከቀድሞ መሰል ጥረቶች መማርና ለችግሩ ውስብስብነት በሚመጥን ስልታዊ ዘዴ (methodology) ሂደቱን መምራት ይጠበቅባቸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተደረጉ መሰል ጥረቶች መካከል በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችለው የምንፈልጋት ኢትዮጵያ (Destiny Ethiopia) በሚል ስያሜ እየተነቃነቀ የሚገኘው ሃገር በቀል ተነሳሽነት ነው። ይህ ተነሳሽነት በተከተለው ልዩ ስልታዊ አካሄድ የተነሳ፣ ምናልባትም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተሻለ ውጤታማነት የታየበት ሂደት ነበር ማለት ይቻላል። የዚህ ሂደት የመጀመሪያው ግብ፣ በፖለቲካ ልሂቃኑ መሃከል ለዘመናት ተኮትኩቶ የተገነባውን አእምሮአዊ አጥር (Mental barriers) ማፈራረስ ነበር። ይህንን ግብ፣ በግለሰብ፣ በቡድንና በስብስብ ደረጃ በተካሄዱ በርካታ ውይይቶችና የተግባር ልምምዶች አማካኝነት በአብዛኛው ለማሳካት እንደቻለ መመስከር ይቻላል። ከዚህ በመቀጠል የነበረው ግብ የሀገሪቱን መሰረታዊ የፖለቲካ ችግሮች ሊፈታ የሚያስችል አሻጋሪ ቢሆንሶችን (transformational scenarios) መለየት ነበር።  ይህንንም ለማድረግ ከተናጠል ሁነቶችና ዑደቶች ባሻገር በመመልከት መዋቅራዊ ምክንያቶችንና አእምሮአዊ ምስሎችን (models) መፈተሽ አስፈላጊ ነበር። በዚህም መሰረት፣ የሂደቱ ተሳታፊዎች በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ ያሉትን መዋቅራዊ አይገመቴዎች (structural uncertainties) በሚገባ መለየት ችለው ነበር። ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ፣ መዋቅራዊ አይገመቴዎችን ከለዩ በኋላ መሰረታዊ ምንጮቻቸውን መለየትና እነርሱም የሚያስከትሉትን የተለያዩ አንደምታዎች መተንተን ወደ አሻጋሪ ቢሆንሶቹ የሚወስድ መሰረታዊ ሂደት ነው። የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ሂደት በልዩ ልዩ ምክንያት ይህንን መሰረታዊ የሂደት ደረጃ በመዝለል ከመዋቅራዊ አይገመቴዎች በቀጥታ ቢሆንሶቹን ወደ መግለጽ ውስጥ ገብቷል። የዚህም ውጤት በአብዛኛው ህብረተሰብ ሊገመቱ የሚችሉ አንድ የተስፋና ሶስት የስጋት ቢሆንሶችን ማውጣት ሊሆን ችሏል።
እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር፣ ይህንን ሂደት ከሃሳብ ማመንጨት እስከ መጨረሻው ተግባራዊነት የነበረውን እጅግ አድካሚ ሂደት በማስተባበር የመሩት ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ አድናቆት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ሊደነቁና ሊከበሩ የሚገባቸው፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ከልብ አስጨንቋቸው በዚህ የተራዘመ ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉትና አሁንም በማድረግ ላይ የሚገኙት የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ቡድን አባላት ናቸው። በዚህ ፀሐፊ እምነት፤ ይህ ሂደት ለሃገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ ለመሻት ያደረገው አስተዋጽኦ ቢኖርም፣ በሂደቱ የመጨረሻ ክፍል የታየው መሰረታዊ ያካሄድ ግድፈት፣ ለሃገሪቱ የፖለቲካ ችግር አመላካች የሆነ መፍትሄ ለማመንጨት የሚያስችለውን እድል እንዲያመልጠው አድርጎታል። በአሁኑ ሰዓት በመካሄድ ላይ የሚገኘው የብሔራዊ መግባባት ውይይት፤ ከምንፈልጋት ኢትዮጵያ ሂደት ሊማር የሚችላቸው በርካታ ቁምነገሮች ሲኖሩ፣ የሚከተሉትን በዓበይትነት መጥቀስ ይቻላል። የመጀመሪያው፣ ምንም እንኳን በአሁኑ ሰአት በሃገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች እጅግ የተለያየ፣ አንዳንዴም የማይታረቅ የሚመስል አቋም ያላቸው ቢመስልም፣ በጽሞና ለመደማመጥ በሚያስችል ሁኔታ ከተወያዩ መግባባት የሚችሉበት አጋጣሚ ከፍተኛ መሆኑን ነው። ሁለተኛው፤ የብሔራዊ መግባባት ውይይቱ የተሳካ እንዲሆን የሃገሪቱን ውስብስብ ሁኔታ በሚመጥን ስልታዊ ዕውቀት ሊደገፍ ይገባል። ይህንን ዕውቀት ለመሻትም ባህር አቋርጦ ወደ ውጭ መመልከት የሚያስፈልግ ሳይሆን በሃገራችን የሚገኙ ሃገር በቀል የውይይትና  መደማመጥ ሥርዓቶችን፣ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት ከሚያስችሉ የዘመኑ ዕውቀትና ዘዴዎች ጋር በማሰናሰል መጠቀም ይቻላል። ይህንን መሰረት በማድረግ፣ ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ ያለውን የብሔራዊ መግባባት ውይይት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ አንዳንድ መሰረታዊ ነጥቦችን ከዚህ በመቀጠል አካፍላለሁ።
ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ባሁኑ ስዓት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስተባባሪነት እየተካሄደ ያለው የብሔራዊ መግባባት ውይይት፣ በቅርብ ጊዜው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው መልካም አጋጣሚ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን አጋጣሚ ውጤታማ ለማድረግ ቁልፉ መለኪያ አጠቃላይ ሂደቱ ትብብራዊ አስተሳሰብን (collaborative thinking) በሚያጠናክር መልኩ እንዲዋቀር ማድረጉ ላይ ነው። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም፣ ከመወያያ ርዕስ መረጣ እስከ ጽሁፍ ዝግጅት፣ አቀራረብና የውይይት አደረጃጀት ድረስ ያሉትን ሂደቶች በጥንቃቄ መተለምና ማዘጋጀትን ይጠይቃል። የመወያያ ርዕስ መረጣን በሚመለከት ለብሔራዊ መግባባት ውይይት የሚመረጡ ርዕሶች የዲምክራሲያዊ መፎካከሪያ ምህዳሩን ጤናማነት ለማጠናከር አስፈላጊ የሆኑ የመተባበሪያ ርዕሶች ሊሆኑ ይገባቸዋል። የዚህ ዋነኛው ምክንያት፣ የመፎካከሪያ ርዕሶችን ለውይይት መምረጡ ከመግባባት ይልቅ መቋጠሪያ ወደሌለው ንትርክ የሚያስገባ በመሆኑ ነው። ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ለሁለተኛው ዙር ከተመረጡት ርዕሶች አንደኛው ከፓርቲዎች መብዛት ጋር በተያያዘ የፓርቲዎች አደረጃጀትን የሚመለከት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዲሆን መወሰኑን በሚድያ ሲነገር ተሰምቷል። ዛሬ ሃገሪቱ ካሉባት በርካታ የፖለቲካ አጣብቂኞች አኳያ ይህ ርዕስ በምንም አይነት መመዘኛ ለብሔራዊ መግባባት የሚመጥን ካለመሆኑም በላይ፣ አካታች ያለመሆን እድሉም ከፍተኛ ይሆናል። በመሰረቱ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አደረጃጀትና ብዛት በእንደዚህ አይነት ስብሰባ ለመወስን መሞከር የኢ-ዲሞክራሲያዊነት ዝንባሌም ያለው ይመስላል። ይህንን ሁኔታ ባግባቡ ለማስተናገድ ማንኛውም ፓርቲ እንደ ፓርቲ ለመመዝገብና ከምርጫም በኋላ በሚያገኘው የህዝብ ድምጽ ላይ ተመርኩዞ ሊኖረው የሚችለውን ፖለቲካዊ መብት፣ በምርጫ ህጉ ውስጥ በአግባቡ እንዲካተት ማድረግ ተገቢ ነው። ነገር ግን፣ ይህንን ሂደት አካታች በሆነ ሂደት በባለቤትነት መምራት ያለበት ገለልተኛ እንዲሆን የሚጠበቀው የምርጫ ቦርድ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አይደለም።
የብሔራዊ መግባባት ውይይት አንደኛው መሰረታዊ ግቡ፣ በፖለቲካ ተዋንያኖች መካከል ሊኖር የሚገባውን ትብብራዊ አስተሳሰብ ማጠናከር ነው። በዚህ ረገድ፣ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሁፎች የሚዘጋጁበትና የሚቀርቡበት መንገድ ወደዚህ ግብ የሚደረገውን ጉዞ ከሚወስኑት አካሄዶች አንዱ እና ዋነኛው ነው። እስካሁን በተካሄዱት ውይይቶች በተመረጡት ርዕሶች ላይ የመወያያ ጽሁፎች የማቅረቡ ሃላፊነት የተሰጠው ከፓርቲዎች ውስጥ ለተመረጡ ግለሰቦች በተናጠል ነው። እንዲህ አይነቱ አካሄድ፣ በአቅራቢው በኩል ጽሁፉን ምንም ያህል ሚዛናዊ ለማድረግ ቢሞከር፣ በፓርቲው መስመር ለመጠለፍ ወይንም በፓርቲ ወገናዊነት ለመኮነን አደጋ መጋለጡ የበዛ ነው። ከትብብራዊ አስተሳሰብ አኳያ ተመራጩ መንገድ፣ ባንድ ርዕስ ላይ የሚቀርብን የመወያያ ጽሁፍ ከሶስት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ ግለሰቦች በጋራ እንዲያዘጋጁና እንዲያቀርቡ ማድረግ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ፣ አዘጋጆቹ የሚጠበቅባቸው በተሰጣቸው ርዕስ ላይ የሚግባቡባቸውንና የሚለያዩባቸውን አንኳር ነጥቦች ለይተው በማቅረብ፣ በሚግባቡባቸው ነጥቦች ላይ እንዴት አብሮ መስራት እንደሚቻልና የሚለያዩባቸውን ነጥቦች እንዴት ሊስተናገዱ እንደሚችሉ ማመላከት ይሆናል። ይህንን አካሄድ በመጠቀምም፣ የጋራ ሃላፊነት በተሰጣቸው ግለሰቦች መካከል የተሻለ የሃሳብ ግንኙነትና መረዳት ከመፍጠር ባሻገር ለብሔራዊ መግባባት መፈጠር የሚያግዙ መሰረታዊ ጡቦችን (building blocks) ደረጃ በደረጃ ለማስቀመጥ የሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል።
ከርዕስ መረጣና የመወያያ ጽሁፍ አዘገጃጀት ባልተናነሰ ቁልፍ ድርሻ ያለው ሶስተኛው አካሄድ፣ በጽሁፎቹ ላይ የሚካሄዱ ውይይቶች አደረጃጀት ይሆናል። በሚድያ ሲተላለፍ እንደታየው ከሆነ፣ እስካሁን በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ጽሁፎቹ ከቀረቡ በኋላ ሁሉም ተሳታፊዎች ባሉበት ምልዐተ ስብሰባ (plenary) ላይ ውይይቱ ይቀጥላል። እንዲህ አይነቱ አካሄድ፣ ሃሳባቸውን ለማካፈል የሚፈልጉ ተሳታፊዎች የሚኖራቸውን እድል የሚያጠብ ከመሆኑም በላይ በዋነኛ ነጥቦች ላይ ትኩረት ያደረገና ውጤታማ የሆነ ውይይት ለማካሄድ የሚኖረውን እድል እጅግ ፈታኝ ያደርገዋል። ከዚህ ይልቅ ተመራጩና ውጤታማው መንገድ፣ የመወያያ ጽሁፎቹ ከቀረቡና በጽሁፎቹ ላይ ለሚነሱ የማብራሪያ ጥያቄዎች መልስ ክተሰጡ በኋላ ያሉትን ተሳታፊዎች፣ በአነስተኛ ቡድኖች በመከፋፈል በቀረቡት ጽሁፎች ላይ ተወያይተው የሚደርሱበትን ማጠቃለያ፣ ለምልዐተ ስብሰባው ለውይይት እንዲያቀርቡ ማድረግ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የምልዐተ ስብሰባና የቡድኖች ውይይት፤ ቅይጥ አካሄድ ሃሳቦች በደንብ የሚብላሉበትን ሁኔታ ከመፍጠሩም ባሻገር በተሳታፊዎቹ መካከል ሊፈጠር የሚገባውን ግለሰባዊም ሆነ ቡድናዊ መስተጋብር ይበልጥ ስኬታማና ጤናማ እየሆነ እንዲሄድ ያደርገዋል። ይህም፣ ፓርቲዎቹ ይበልጥ እየተሰባሰቡ እንዲሄዱ ሊያግዛቸው ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የብዙ መሰል ጉባኤዎች ልምድ እንደሚያመላክተው፣ እንዲህ አይነት ስብሰባዎች ላይ ቢያንስ በቡድን ተከፋፍለው የሚደረጉ ውይይቶችን ከሚድያ እይታ ውጭ እንዲካሄዱ ማድረግ ይመከራል። ይህም፣ ተሳታፊዎች በፍጹም ነጻነት ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ከማበረታታቱም ባሻገር በደንብ ያልተብላሉ ሃሳቦችን በሚዲያ በማሰራጨት ሊፈጠሩ ከሚችሉ ብዥታዎች ህብረተሰቡን መጠበቅ ያስችላል።
ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት የአካሄድ መርሆች ባሻገር፣ እንዲህ ዓይነት ጉባዔ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ፣ ሁሉም ተሳታፊዎች በተናጠልም ሆነ በጋራ ሊያከብሯቸው የሚገቡ መሰረታዊ የሥነምግባር መመሪያዎች ይኖራሉ። ከዚህ ውስጥ የመጀመሪያውና ዋነኛው ሁሉም ተሳታፊዎች ለሀገራቸው እድገትና ለህዝባቸው ኑሮ መሻሻል ቀና አስተሳሰብ ይዘው የተነሱ ናቸው የሚል ግምት (benefit of the doubt) መስጠት ይሆናል። እንዲህ አይነቱ እምነት፣ በህዝቦች ዳኝነት ከማመን ጋር በጥብቅ የተሳሰረ በመሆኑ ፖለቲከኞቻችን የየትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት ወይንም ፖለቲከኛ የመጨረሻውን ዳኝነት በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለሚወስነው ህዝብ ሊተዉለት ይገባል።  ሁለተኛው፣ በእንዲህ አይነት መድረክ የሚቀርቡ ማናቸውንም ሃሳቦች በሃሳብ መሞገት እንጂ ለምን እንዲህ ተባለ ብሎ፣ ከዚህ በፊት በተካሄዱ አንዳንድ ውይይቶች ላይ እንደታየው፣ ፖለቲካዊ ፍረጃና ቅጥያ (Political labelling) ለመስጠት መሞከር አይገባም። ይህ ፖለቲካዊ ቅጥያ የመስጠት ዝንባሌ ከተማሪው እንቅስቃሴ ጀምሮ ፖለቲካችንን የተጠናወተ በሽታ በመሆኑ በዚህ ዘመን ልናስወግደው ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ለብሔራዊ መግባባት የሚደረግ ውይይት ዘላቂ፣ ሃገራዊና ህዝባዊ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሚደረግ ውይይት እንጂ ለምርጫ መፎካከሪያ የሚሆን የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ እንዳልሆነ ሁሉም ተሳታፊዎች ሊገነዘቡት ይገባል። በመጨረሻም የአህጉራችን ታላቅ ሰው የሆኑት አቶ ኔልሰን ማንዴላ እንደተናገሩት፤ ውስብስብ የፖለቲካ ፈተና ውስጥ ለሚገኙ ሃገራት ብሔራዊ መግባባት፣ ሆኖ እስከሚገኝ ድረስ በጭራሽ የማይቻል መስሎ ይታያል። ነገር ግን ይቻላል፤ ተችሏልም።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።



Read 2806 times