Saturday, 10 October 2020 15:16

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ዋርካው ሲታወስ ---
                         [ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ]

            ..በርግጥ ሀገራችን ካፈራቻቸው ትላልቅ ምሁራን አንዱ ነው ጋሽ መስፍን። አኔ እስከማውቀው ድረስ በሀገራችን ብዙ ከጋሽ መስፍን ያልተናነሱ ምሁራን አልፈዋል። ግን በዚህ ደረጃ ክብር ሰጥተን የሸኘናቸው ያሉ አይመስለኝም። ፕ/ር መስፍንን ከሌሎች ምሁራን የሚለየው ለባለሙያ ስብሰባ የሚያቀርባቸው ፅሁፎች ወይም በአደባባይ የሚያቀርባቸው ሂሳዊ መጣጥፎች ሁሉ ማጠንጠኛ ኢትዮጵያ መሆኗ እና አለ ለሚላቸው የማህበረሰብ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ችግሮች መፍትሄ ለማመላከት ኢላማ ያደረጉ በመሆኖቸው ይመስለኛል።
ጋሽ መስፍንን ቀልቡን የሚስበው እና የሚያብሰለስለው የሀገሪቱ ድህነትና ኋላቀርነት፣ የዜጎች ሰብአዊ መብት፣ አገዛዞች በማህበረሰቡ አባላት ነፃነት ላይ በሚያስከትሏቸው ተፅእኖ ዜጎች ሁሌም መንግስትን እንደፈሩና አንገታቸውን አቀርቅረው የሚኖሩበት ሁኔታ ለዘለቄታው በማህበረሰቡ ስነ ልቦና ይበልጡንም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሚደቅኑት አደጋዎች ናቸው ጋሽ መስፍን ብዕሩን እንዲያነሳ የሚያደርጉት። ጋሽ መስፍን ከሀገሩ ጋር የተወሳሰበ ግንኙነት ነበረው። ሀገሩን ክፉኛ ይወዳል ግን የዛን ያህል ቅጥ የለሽ ድህነት፣ የፍትህ እጦት ፣ የነፃነት ማጣትና በፍርሃት ቆፈን ተይዞ መኖር ሁሌም ያመዋል።
በሀገር ፍቅር በአንድ በኩል፣ የሀገር ዘርፈ ብዙ ውድቀት በሌላ በኩል፣ ነፍሳቸው የምትዋዥቅባቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ እናውቃለን። ብዙዎቹ ይሄን የውስጥ ግጭት ከቤተሰቦቻቸውና የቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር ይነጋገሩበት እንደሆነ እንጂ በአደባባይ በግላጭ ከማህበረሰቡ ጋር ለመናገር ይፈራሉ። ይሄን ሁኔታ ለመቀየር ምንም አይነት ጥረት ሳያደርጉ “ጥሩ ኑሮ” ኖረው ያልፋሉ። እዚ ጋ ነው ጋሽ መስፍን በግልፅ ከሌሎች እንደሱ ምሁራን ከሚባሉ የሚለየው።
ለሱ ሀገርን የሚያክልን ጉዳይ የሚመለከት ነገር፣ በሀገርና በህዝብ ሀብት የተማሩ ምሁራን በየጓዳውና በየማህበሩ ለመበላት ሲገናኙ የሚናገሩትና የሚያሙት ጉዳይ ሳይሆን የተበላሸውን ለማስተካከል በግላጭ ከሚመለከተው አካል ስልጣን ከያዘው መንግስት ጋር ሳይቀር ለመነጋገር የሞራል ድፍረቱ ሊኖራቸው ይገባል የሚል ፅኑ እምነት ስለነበረው ፣ ይሄን እምነቱን ደግሞ በተግባር ለማሳየት በመቻሉ ነው እሱን በተለየ ሁኔታ እንድናየውና እንድናከብረው የሚያደርገን።
ጋሽ መስፍን ለሱ ዘመን እኩዮች ብቻ ሳይሆን በእድሜ በብዛት ለሚያንሱትም ቀጣይ ትውልድ ጭምር የሞራል ዕዳ የሚያሸክማቸው በመሆኑ ነው፣ በተለይም በእድሜ ለሚጠጉት በተለያየ ቁሳዊ ፍላጎት ምክንያት የሀገሪቱን መከራ ከዳር ሆነው ለሚመለከቱ፣ የሱ ግልፅነትና ድፍረት የሚጎረብጣቸው።
ከዚህ አንፃር ዛሬ ልንሸኘው የተሰባሰብነው ሰው ቢያንስ ላለፉት 3 እና 4 ትውልዶች የማህበረሰባችን የሞራል ኩራዝ ሆኖ ያገለገለ ትልቅ ሰው ነው። ይሄን ሚናውን የተወጣው በድንገት ሳይሆን አውቆ ነው። እንዲህ አይነት አስቸጋሪ ሚና ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ትችትን፣ ስድብን፣ ውግዘትን ሊያስከትል እንደሚችል ብቻ ሳይሆን እንደማይቀርለት አውቆ የገባበት ነው።
በአገዛዝ ስርአቶች ታስሮበታል ፤ በጊዜና በተውሶ እውቀት ልቀናል በሚሉ ወጣት አብዮተኞች ተዘልፎበታል ፤ ከብሄርህ ውጪ ለምን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ትላለህ በሚሉ አዳዲስ የጎሳ ብሄርተኞች ተንጓጦበታል። ሁሉም በሀሳቡ ሊሞግቱት ከፈለጉ ክፍት ነበር። ሀሳብን በሀሳብ መሞገት አቅቷቸው ወደ ስድብና አካኪ ዘራፍ ለሚሄዱ ምንም ፍርሃትም ሆነ ክብር የለውም! በተለይም ለማህበረሰብ የሞራል ልእቀት ሃላፊነት ያለባቸው አካላትና ግለሰቦች፣ ለነዋይና ለስልጣን ሲሉ ሳይወጡ ሲቀሩ ፍፁም ይጠየፋቸዋል።
ጋሽ መስፍን ኢትዮጵያውያንን እንደ ዜጎች ከመመልከት በቀር በተለየ የሚወደው ብሄር አልነበረውም። ለኢትዮጵያውያን ዘርና ሃይማኖት ሳይመርጥ ለተበደሉ ሁሉ በአደባባይ ጥብቅና ቆሟል። ሁሌም ወገንተኝነቱ አቅም ለሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ነበር። ለዜጎች ሰብአዊና የዴሞክራሲ መብቶች መከበር ከልቡ ታግሏል። እኔ እስከማውቀው ድረስ የኢትዮጵያና የህዝቧን ጥቅም በሚመለከት ማድረግ ያለበትን፣ ማድረግ እያለብኝ ያላደረግኩት አለ ብሎ የሚቆጭበት ምንም ነገር ያለ አይመስለኝም።
አኔን የሚቆጨኝ ብዙ የደከምክለት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ መጨረሻ ሳታይ ብታልፍም ፤ ምኞትህ እውን እንዲሆን ከልብ እንደምንሞክር ቃል እገባልሃለሁ።
ጋሽ መስፍን የኖረው ኑሮና ህይወቱ ለማህበረሰባችን ትቶ የሄደው ትምህርት ካለ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ላመኑበት አላማ በፅናት መቆም ነው፤ ላላፊ ቁስም ሆነ ስልጣን አለማጎብደድ ወይም አለመሸነፍን ነው። ዝም ብሎ ጎርፍ በሚሄድበት መሄድ ሳይሆን በሁለት እግር ቆሞ በራስ ማሰብንና ባመኑበት መግዘፍን ምንም እንኳ ነዋይ ባያስገኝም በማህበረሰብ ዘንድ በጣም የሚያስከብር እሴት መሆኑን ማህበረሰባችን ለዚህ ሰው ከሰጠው ክብር ትረዳላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
በአጠቃላይ የማህበረሰባችን የሞራል ቁመና እጅግ በተዳከመበት በዚህ ወቅት የጠንካራ የሞራል ልእልና አስፈላጊነት ጋሽ መስፍን በህይወቱ ብቻ ሳይሆን በሞቱም በሰጠነው ክብር የሞራል ልእልና ለማህበረሰብ ሰላምና ጤንነት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ትረዳላችሁ ብዬ እገምታለሁ።
ስሞት አታልቅሱ ፣ ስሞት አትቅበሩኝ ፤ ይልቁንስ አስክሬኔንን አቃጥላችሁ አመዱን አዋሽ ውስጥ በትኑት ፤ በህይወቴ ያልገዛሁት መሬት ስሞት እንዲኖረኝ አልፈልግም ብለሃል። ይህ ፍላጎትህ በሞትህ መሳካቱን አላውቅም፤ ነገር ግን በህይወትህ ግን የምትፈልገውንና የምታምንበትን ኖረሃል። ስንቶቻችን ደረታችንን ነፍተን ይሄን እንለዋለን?
መልካም እረፍት ጋሽ መስፍን፤ አንረሳህም!
(ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የሽኝት ፕሮግራም ከተናገሩት መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም)


Read 1113 times