Saturday, 10 October 2020 13:11

በሳኡዲ በኢትዮጵያውያን ላይ ስለሚፈፀመው ኢ-ሰብአዊ ተግባር ለአውሮፓ ፓርላማ የውሳኔ ሃሳብ ቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  3 ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት ሞተዋል
                          
          ከሰሞኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ኢ-ሠብአዊ ድርጊቶችን የሚዘረዝር ሪፖርት ማውጣቱን ተከትሎ፣ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት የሳኡዲ አረቢያን መንግስት ተጠያቂ የሚያደርግ የውሳኔ ሃሳብ ለፓርላማው አቅርበዋል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከቀናት በፊት ባወጣው የምርመራ ሪፖርቱ፤ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳውዲ አረቢያ በተለያዩ የማጐሪያ ስፍራዎች ከፍተኛ ኢ-ሰብአዊ ተግባራት እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ አስታውቋል። ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ባለፈው መጋቢት 2012 ከየመን በሁቲ አማፂያን ድብደባና ሌሎች ኢ-ሰብአዊ ተግባራት ከተፈፀመባቸው በኋላ በሃይል ተባረው ሳውዲ የገቡ ናቸው ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
የሰብአዊ መብት ተቋሙ በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የእስር ሁኔታ መመርመሩንና ኢትዮጵያውያኑ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ከሚፈፀሙ ኢ-ሰብአዊ ተግባራት መካከል፤ በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ መላወስ እንኳ በማይችሉበት ሁኔታ በርካቶችን አጭቆ ማሠርና ሽንት ቤት እንዳይጠቀሙ መከልከል የሚጠቀሱ ሲሆን በዚህም እስረኞቹ በሚተኙበት ወለል ላይ እንዲፀዳዱ መገደዳቸውን ሪፖርቱ ያትታል።
አብዛኞቹ እስረኞች ለበርካታ ቀናት እጃቸው በካቴና ታስረው መቆየታቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የምግብ ውሃና የህክምና አቅርቦት በመሠረታዊነት ደረጃ እያገኙ አለመሆኑን አመልክቷል። በዚህ ኢ-ሠብአዊ አያያዝ የተነሳ ሶስት ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ መሞታቸውን ማረጋገጡን፣ ሁለቱ ደግሞ ራሳቸውን የማጥፋት ሙከራ ሊያደርጉ ሲሉ በሰዎች እርዳታ መትረፋቸውን ሪፖርቱ ይዘረዝራል።
የአምነስቲ ሪፖርትን ተከትሎ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት የሳውዲ መንግስት በኢትዮጵያውያኑ ላይ በፈፀመውና እየፈፀመ ባለው ኢ-ሠብአዊ ተግባር ተጠያቂ ሊሆን ይገባል ሲሉ ለአውሮፓ ፓርላማ የውሣኔ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን ጥቂት የማይባሉ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት የውሣኔ ሃሳቡን መቃወማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኢትዮጵያ መንግስት በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ዜጐቹ እንዲደረስላቸው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ ኢትዮጵያውያኑን ለመታደግ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

Read 1164 times