Print this page
Saturday, 10 October 2020 12:47

የድርድሩ ተጨማሪ አጀንዳ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ግብጽና ሱዳኝ ከአንድ ስምምነት ሳንደርስ የሕዳሴው ግድብ መሞላት የለበትም ሲሉ የነበሩት እና አሜሪካም የዚህ ሃሳብ ደጋፊ ሆና ግድቡን ከመሙላታቸሁ በፊት  መጀመሪያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ተስማሙ በማለት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ስታሳድር የቆየችው  በእውነት ከስምምነት ለመድረስ ቅንነቱ ኖሯቸው አስበውና ተጨንቀው ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ የእነሱን መስማማት ስትጠብቅ የሕዳሴው ግድብ የውኃ መሙያ ጊዜ እንዲያልፍ ለማድረግ ነበር፡፡ በሚቀጥለውም ጊዜ ይህን መንገድ መከተላቸው ስለማይቀር ከወዲሁ ሊታሰበበት ይገባል፡፡
ግብጽና ሱዳን እንደ ማስፈራሪያ የሚጠቀሙበትን የሁለቱን አገር የጋራ ስምምነት‹፣ አልፎም ግብጽ አለኝ የምትለውን የቬቶ ድምጽ በመስበር ግድቧን የጀመረችው ኢትዮጵያ፤ አሁንም ግድቧን ከስምምነት ውጪ በመሙላት ለእነሱ ፍላጎት እንደማትገዛ በግብር ለማሳየት ችላለች፡፡ ከሞኝ ደጅ ሞፈር መቁረጥ የለመዱት ግብጾች፤ ከኢትዮጵያም ተመሳሳይ ጥቅም ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ ኡጋንዳ ግድብ ላይ ሰው መድበው በየቀኑ የውኃ ፍሰት እንደሚከታተሉ ሁሉ፣ በሕዳሴው ግድብ ላይም አንድ ሰው ማስቀመጥና መቆጣጠር ይፈልጋሉ፡፡ 550 እስኩየር ኪሎ ሜትር መሬቷን ያለ አንዳች ጥቅም ለአስዋን ግድብ ወኃ መተኛ  እንዳስረከበቸው ሱዳን ሁሉ፤ ኢትዮጵያም በገንዘቧ የሠራችው የሕዳሴ ግድብ ለእሷ ፍላጎት ማሟያ ሆኖ እንዲቀር ትመኛለች፡፡ ይህ ምንጊዜም የሚሳካ አይሆንም፡፡
"የሕዳሴው ግድብ የመጨረሻ ምዕራፍ" በሚል ርዕስ አል አህራም ኦን ላይን  ድረገጽ ላይ ከለሞኑ የጻፉት በካይሮ የኒቨርስቲ የኢንጂነሪንግ ፕሮፈሰር የሆኑት፣ የቀድሞው የግብጽ ውኃና መስኖ ሚኒስትር ሞሐመድ ናስ ኢልዲን፤ "የሆነው ነገር ሁሉ የሆነው በግብጽ መዳከምና በሠራችው ስህተት ነው" የሚል መነሻ ሃሳብ ይዘዋል፡፡ ጸሐፊው ግብጽን ያዳከማት የሚሉት እ.ኤ.አ በ1990 የጀመረው የአረቡ ዓለም መዳከም ነው። ችግሩ የተከሰተው በኢራቅ መፍረስ፣ በሶሪያ ሕዝብ መበተን፣ በሊባኖስ በውስጥ ችግር መጠመድ፣ በሱዳንና  በሶማሊያ መዳከም እንዲሁም በየመን መፈራረስ እንደሆነ ይዘረዝራሉ፡፡ ሌላው የግብጽ መዳከም መገለጫ፤ የናይል ትብብር ማእቀፍ መፈረምና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘት መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ‹‹እ.ኤ.አ በ2011 የግብጽ አብዮት መቀጣጠልና የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመር ምን ላይ እንደደረስን ማሳያ ነው›› ይላሉ ሞሐመድ ናስ አዲል፡፡
"ሱዳን አትዮጵያ የፈለገችውን ያህል ግድብ በዓባይ ላይ መገንባት ትችላለች የሚል ሃሳብ ብታቀርብም  ኢትዮጵያ ደግሞ አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ሶስተኛ ወገን በገላጋይነት እንዲገባ የሚፈቅድ  አሰገዳጅ ውል ለመፈረም ፈቃደኛ አይደለችም" የሚሉት በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰሩ፤ ‹‹በእኔ እምነት ወታደራዊ አማራጭ መገፋት የለበትም›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፤ በቅርቡ የሕዳሴው ግድብ የሚገኝበትን አካባቢ ለማንኛውም አይነት የአየር በረራ ዝግ ማድረጉን መግለጹ ይታወቃል፡፡ ውሳኔው ዘግይቷል ካልተባለ በስተቀር ተገቢ እርምጃ መሆኑን በአጽንኦት መግለጥ አወዳለሁ፡፡
ግብጾችና ሱዳኖች እንዲሁም የጀርባ ደጀናቸው አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ውል እንድትገባ ይፈልጋሉ፡፡ በተለይ ግብጽ እዚህ ላይ ያላት ፍላጎት እጅግ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ እንዲህ እንደ ልቧ ያደረጋት ደግሞ  በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሌሎች አገራት በየዋህነት የሰጧት ጥቅም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ‹‹አንድ ኩባያ ውኃ አንቀንስም›› ብላ ቃል ብትገባላቸው  የሚያገኙትን ውኃ ለፈለጉት ጥቅም ሊያውሉት ይችላሉ፡፡ እነሱ ‹‹የምናገኘውን ውኃ አናባክንም፤ አሳልፈን ለሌላ አገር አንሰጥም›› ብለው ግዴታ ቢገቡ ኢትዮጵያ ምን ታተርፋለች? ውኃ ተመልሶ ሽቅብ ስለማይፈስ፣ የግዴታን ጉዳይ አጥብቃ ከእርሷ ማራቅ አለባት፡፡
ግብጽና ሱዳን ዛሬ እንደ ዳዊት የሚያነበንቡትን ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት ኢትዮጵያ ;በጉዳዩ ልሳተፍበት ይገባል; ብላ ጠይቃለች፡፡ የአስዋን ግድብን ግብጽ ስትሠራ አሁንም ተቃውሞዋን ኢትዮጵያ ገልጣለች፡፡ የቶሽካ ቦይ ተሠርቶ የአባይ ውኃ ወደ ሲናይ በረሐ ሲወሰድም ዝም አላለችም። በዚህ ሁሉ  የግብጽን የውኃ ተጠቃሚነት የማስፋት ተግባር ኢትዮጵያ ቅሬታዋን እየገለጸች፣ መፍትሔም እንዲፈለግ አያሳሰበች የቆየች አገር ናት፡፡
ኢትዮጵያ የምትከተለው ‹‹ፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነትና በሌላው ላይ ጉልህ ጉዳት አለማድረስ መርሕ›› መነሻ የሚያደርገው የቱን የውኃ አጠቃቀም ጊዜ  ነው? ይህም ሊታሰብበትና መልስ ማግኘት  የሚገባው ጥያቄ  ነው፡፡ የአባይ ውኃ ዓመታዊ ፍሰት መጠን  የታወቀ ነው፡፡ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከተጀመረ አንስቶ በመላ አገሪቱ በተለይም በዓባይ ተፋሰስ ከፍተኛ የተፈጥሮ እንክብካቤ ሥራ ተሠርቷል፤ እየተሠራም ነው፡፡ ይህ ዓመታትን ያስቆጠረ ሥራ የሀገራችን የዝናብ መጠን እንዲጨምር ማድረጉን የመስኩ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡  ከፍተኛ የዝናብ መጠን ተገኘ ማለት ያንን ያህል ውኃ ወደ ተፋሰሱ ገባ፤ ግብጽና ሱዳን ተጨማሪ ውኃ አገኙ ማለት ነው፡፡ ለዚህስ ግብጽና ሱዳን መክፈል የለባቸውምን? ይህም የድርድሩ ተጨማሪ አጀንዳ መሆን አለበት!!

Read 1410 times