Sunday, 11 October 2020 00:00

የአለማችን ቢሊየነሮች ሃብት በዘመነ ኮሮና 27 በመቶ ጨምሯል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የኮሮና ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የአለማችን ቢሊየነሮች ሃብት በ27 በመቶ ያህል ጭማሪ በማሳየት 10.2 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን የስዊዘርላንዱ ዩቢኤስ ባንክ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡
በዘመነ ኮሮና የሃብት መጠናቸው በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው በቴክኖሎጂውና በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩት ቢሊየነሮች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ከሚያዝያ እስከ ሃምሌ በነበሩት ወራት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ቢሊየነሮች ሃብት በ44 በመቶ፣ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ባለጸጎች ሃብት ደግሞ በ41 በመቶ ያህል መጨመሩን አመልክቷል፡፡ ከሁለቱ ዘርፎች በመቀጠል ከፍተኛ የሃብት መጠን ጭማሬ ያስመዘገቡት ቢሊየነሮች ደግሞ በመድሃኒትና በህክምና መሳሪያዎች ምርትና ንግድ ዘርፍ የተሰማሩት መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ባለፉት አስር ያህል አመታት የቻይና ቢሊየነሮች በአማካይ የ1ሺህ 146 በመቶ የሃብት ጭማሬ በማስመዝገብ ከአለማችን ባለጸጎች ቀዳሚነቱን መያዛቸውን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ የእንግሊዝ ባለጸጎች ሃብት በአንጻሩ በ168 በመቶ መጨመሩን ገልጧል፡፡ የአሜሪካ ቢሊየነሮች በድምሩ 3.5 ትሪሊዮን ሃብት ሲያፈሩ፣ የቻይናዎቹ በአንጻሩ 1.7 ትሪሊዮን ዶላር ማፍራታቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ጀርመናውያኑ 595 ቢሊዮን ዶላር፣ ፈረንሳውያኑ 443 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም እንግሊዛውያኑ 205 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ማፍራታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
የአለማችን 209 ቢሊየነሮች፣ ከመጋቢት እስከ ሰኔ በነበሩት ወራት፣ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ በድምሩ 7.2 ቢሊዮን ዶላር መለገሳቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ለኮሮና መከላከያ 98 አሜሪካውያን ቢሊየነሮች 4.5 ቢሊዮን ዶላር፣ 12 ቻይናውያን ቢሊየነሮች 679 ሚሊዮን ዶላር፣ ሁለት አውስትራሊያን ቢሊየነሮች ብቻ ደግሞ 324 ቢሊዮን ዶላር መለገሳቸውንም ሪፖርቱ ገልጧል፡፡


Read 4333 times