Saturday, 10 October 2020 12:27

የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

    9 ሚ. ገደማ ህዝብ ለምግብ እጥረት ይጋለጣሉ

              በኬንያና በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን የተስፋፋው የበረሃ አንበጣ እየተራባ መሆኑ የኢትዮጵያን የግብርና ምርት በእጅጉ እንደሚጐዳው የአለም የእርሻ ድርጅት ያስገነዘበ ሲሆን፤ መንግስት በመራባት ላይ ባለው አንበጣ ላይ ከወዲሁ እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል፡፡
የአለም የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ትናንት ይፋ ባደረገው መረጃው አሁን በኢትዮጵያ ከተሠራጨውና በተለያዩ አካባቢዎች በሰብልና በግጦሽ መሬት ላይ ጥቃት እያደረሰ ካለው የአንበጣ መንጋ በእጅጉ የሚልቅ በኬንያ ሳምቡሪ እና ዌስት ፖስት በተባሉ ቦታዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ደቡብ ወሎ እና ባሌ፣ በሶማሊያ ደግሞ በአወዳል፣ ዋቆይ ጋልቤድ፣ ጋልጉዴድ፣ ማዱግ እና ባሪ በተባሉ አካባቢዎች እየተፈለፈለ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
በዚህ በሶስቱ ሀገራት እየተራባ ባለው የአንበጣ መንጋ የመጀመሪያ ተጠቂ የምትሆነው አብዛሃኛውን የሰብል ምርት ለመሰብሰብ በዝግጅት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ መሆኗን ፋኦ በሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡
በአንበጣ መንጋው በቀጣይ ይጐዳሉ ተብለው በሪፖርቱ የተዘረዘሩት አፋር፣ የደቡብ ክልል አብዛኛው አካባቢ፣ ምስራቅ ኢትዮጵያ፣ የመካከለኛው ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያና ዋገህምራ አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ኡጋንዳ እንደቅደም ተከተላቸው የአንበጣ መንጋው ጥቃት ሰለባ ይሆናሉ ብሏል ፋኦ፡፡
በአሁኑ ወቅት በወሎ እና አፋር ሀረርጌ አካባቢዎች የአንበጣ መንጋው ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ የታወቀ ሲሆን መንግስት የፀረ አንበጣ መድሃኒት ርጭት የማድረግ ዘመቻ መጀመሩንና ለዚህም የሚረዱ 5 አውሮፕላኖችን ከውጭ ገዝቶ እያስገባ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ኮቪድ 19፣ የጐርፍ አደጋና የአንበጣ መንጋ የተፈጥሮ ችግሮች የሆኑባት ኢትዮጵያ በዚህ ሳቢያ 19 ሚሊዮን ዜጐቿ ከወዲሁ በምግብ እርዳታ ጠባቂነት መጋለጣቸውንየ አለማቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል፡፡  


Read 5340 times