Saturday, 10 October 2020 12:22

የትግራይ ክልል “የመንግስት ውሣኔ አገር የሚበትን ነው” አለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

 - “የክልሉ ካቢኔና ምክር ቤት ህጋዊ ሰውነት ስለሌለው በጀት አያገኝም”
           - “ውሣኔው ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ክልሉ” የአፀፋ እርምጃ ይወስዳል”
                         
             የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰሞኑን በትግራይ ክልል ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ተቀባይነት የሌለውና አገር የሚበትን ነው ሲል የትግራይ ክልላዊ መንግስት ተቃውሞታል፡፡
የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊያ ካሣ፤ የፌደሬሽን ም/ቤት የሰጠው ውሣኔ ተግባራዊ ከተደረገ የክልሉ ምላሽ እጅግ ከባድና አገሪቱን እስከመበተን የሚያደርሳት ነው ብለዋል፡፡ “በማንም የመንጋ ወሮበላ አመራሮች የተላለፈውን ውሳኔ አንቀበልም” ያሉት ኃላፊዋ፤ “በዚህች አገር ላይ በአንድነት እስከኖርን እስካለን ድረስ ከአገሪቱ ማግኘት የሚገባንን ማንኛውም ጥቅማጥቅም ያለ አድሎ በእኩል ማግኘት ይኖርብናል” ብለዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ  በህገወጥ መንገድ የተቋቋመው የትግራይ ምክር ቤትና ካቢኔ ህጋዊ ሰውነት ስለሌለው፣ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደማይኖረውና የበጀት ድጐማ እንደማያገኝ መግለፃቸው ይታወቃል፡፡
“የመንግስት ዛቻና ቀረርቶ አያሰፈራንም” ያሉት ወ/ሮ ሊያ፤ “ውሣኔው ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ግን የክልሉ መንግስትም በእጁ በሚገኘውና ከትግራይ በሚሰበሰበው ገቢ ላይ ውሣኔውን ያሳልፋል” ብለዋል። “አንድ በህዝቡ ፍላጐት ምርጫን ባካሄደና መንግስት በመሠረተ ክልል ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደጋገሙ ማውጣት፣ የክልሉን ህዝብ መናቅና በበጀት ክልከላ ሰበብ የጀመረውን ትግል ማደናቀፍ ህገወጥ ተግባር ነው” ሲሉ - ኃላፊዋ ተቃውመዋል፡፡
የፌዴሬሽኑን ምክር ቤት ከአባላቱ የክልል መንግስታት ጋር የሚያገናኘው ብቸኛ ጉዳይ “የም/ቤቱ ውሳኔ የበጀት መሆኑን ለቢቢሲ የጠቆሙት የክልሉ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብርሃም ተከስተ በበኩላቸው፤ በጀት አቋርጣለሁ ማለት ከክልሉ ጋር ያለኝ ግንኙነት ይቋርጣል ማለቱ “የም/ቤቱ ውሳኔ ኃላፊነት የጐደለው ነው ትግራይን ከበጀት ውጪ ማድረግ ከፌደሬሽኑ ውጪ ብሎ መግፋት ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል - ምክትል ፕሬዚዳንቱ፡፡
ፌደራል መንግስቱ ገቢን የሚሰበስበው ትግራይን ጨምሮ ከክልሎች ነው ያሉት ዶ/ር አብርሃም፤ በትግራይ የሚሰበስበውን ገቢ ለትግራይ አልከፍልም ማለት እብደት ነው፤ መንግስት የበጀት ውሳኔውን ተግባራዊ ካደረገ ክልሉ ለፌዴሬሽን መንግስቱ ከትግራይ የሚሰበሰበው ገቢ ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
የፌደራል መንግስቱ ባለፈው ዓመት ከትግራይ ክልል 7 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውሰው፤ በ2013 በጀት አመት ደግሞ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነና በዚህ ገቢ ላይ ክልሉ እርምጃ እንደሚወስድ ለቢቢሲ አስታውቀዋል፡፡ የትግራይ ክልል ባለፈው ዓመት 16 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በለላ በኩል የትግራይ ክልል ሰሞኑን በተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች እንዲሁም በመንግስት የኃላፊነት ሥራዎች ላይ ያሉ አባላቱ ሥራቸውን እንዲለቁና ለክልሉ መንግስት ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ክልሉ ያመሩ ተወካዮች እንዳሉና ቀሪዎቹም በሂደት ላይ እንደሆኑ ወ/ሮ ሊያ ለአዲስ አድማስ  ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ “እኛ የህዝብ አገልጋዮች ነን፤ ከፓርቲው በላይ ህዝቡን የማገልገል ኃላፊነት ተጥሎብናል”፤ በሚል ጥሪውን ያልተቀበሉ የህወሓት አባላት እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህን አባላት በተመለከተ የተጠየቁት ወ/ሮ ሊያ ሲመልሱ፤ “እነዚህ ሰዎች የትግራይን ህዝብና ሕወሓትን አይወክሉም፡፡” ለፖለቲካ ፍጆታቸው የሚያሳልፉትን ውሳኔ እንደ አገርና እንደ ህዝብ አንቀበለውም” ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ለ38 የህዝብ ተወካዮችና ለ8 የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዮቹ እንዲሁም በመንግስት የኃላፊነት ላይ ለሚገኙ አባላቱ ጥሪ ማቅረቡን የተናገሩት ወ/ሮ ሊያ፤ እስከ አሁን ምን ያህሉ ወደ ክልሉ እንደተመለሱ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡



Read 4758 times